“ልጃገረዷን በግድ ቢይዛት አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ለእርሷም ከገንዘቡ ሲሶውን ይስጧት። አስራ ሶስት ዓመት ሳይሆናት አስቀድሞ ልጃገረዲቱን የያዛትን ሰው አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ከገንዘቡም እኩሌታውን ለእርሷ ይስጧት፡፡”
ይህ ሕግ ነው፤ ሴቶችን ከእንስሳዊ ጥቃት ለመታደግ ከ570 ዓመት በፊት የተደነገገ፡፡ ዘመኑ የአገራችን ሥነ ጽሑፍ አብቦበት እንደነበረ የሚነገርለት ነው - የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1434-1468) ዘመነ መንግስት፡፡ ለሥነ ጽሑፉ መዳበር ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ከጉንዳንጉዶ ገዳም የተነሱት የአባ እስጢፋኖስና ደቀመዛሙርታቸው አዲስ ሃሳብ ማቀንቀን ነው፡፡ መነኮሳቱ ለሚያነሱት አዲስ ነገረ መለኮት መልስ ለመስጠት ሲባል በርካታ መጻሕፍት በንጉሱ እና በተቃራኒው ወይም በነባሩ አስተሳሰብ መመራትን በሚሹ መነኮሳት ይጻፉ ነበር፡፡
“ፍትሐ ነገሥት” የተባለው የሕግ መጽሐፍ ሥራ ላይ የዋለውም ከዚያ የፍትጊያ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በ1923 ዓ.ም በወጣው ሕገ መንግሥት እስከተተካ ድረስም ለአራት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመታት መንግሥትና ሃይማኖት/በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት/ በተግባር ሲያውሉት ቆይተዋል፡፡
ዛሬ “የሕግ ትምህርት ቤት” እንደሚባለው ድሮ ፍትሐ ነገሥት ራሱን ችሎ ወይም ከትርጓሜ መጻሕፍት ጋር በአንድ ጉባኤ ትምህርቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ፍትሐ ነገሥት የተማሩት ሊቃውንትም ከነገሥታቱ የፍርድ አደባባይ ላይ በመገኘት ነገሥታቱ በፍትሐ ነገሥቱ ህግጋት መሠረት የፍርድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያግዙ ነበር፡፡