Saturday, July 6, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ወይስ ተማላጅ ?



    ኢየሱስን ክርስቶስ ክብር ይግባውና አማላጅ ነው የሚሉ ወገኖች የሚከተሉትን ጥቅሶች ማስረጃ ነው ብለው ያቀርባሉ።

                  “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።ዮሐ 146 ይህን በመጥቀስ አማላጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ይላሉ። ነገር ግን ይህን ጥቅስ የሚያስረዳን ስለ አማላጅነቱ ሳይሆን አብን ለማወቅ ክርስቶስን በቅድሚያ ማወቅና ማመን እንደሚገባ ነው። ዛሬ የይህዋ ምስክሮች ነን እንደሚሉት እንደ ጆቫዊትነሶች ወይም እንደ አሕዛቦች ክርሰቶስን ሳያምኑና አምላክነቱንና ፈጣሪነቱን ሳንቀበል አምላካችን አብ ብቻ ነው እያልን ብናወራ ዋጋ እንደሌለው የሚገልፅ ቃል ነው። ይህንንም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያረጋግጥልን በዚሁ ጥቅስ ቀጥሎእኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።”  ዮሐ 147 ብሏል።

            “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።ስላለ ወደ አብ የሚወስደን አማላጅ ክርሰቶስ ነው የምንል ከሆነ፦አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” /ዮሐ 637/ “አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” /ዮሐ 644/ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም። /ዮሐ 665/  ሲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯናልና እዚህ ጋር ደግሞ አማላጁ አብ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተትና ኑፋቄ ነው። በሌላ ጥቅስ ላይ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለእኛመንፈስ ቅዱስይቃትታል የሚል ፅፏልናመንፈስ ቅዱስንም አማላጅልንለው ይሆን? ታዲያ አብንም፣ ወልድንም፣ መንፈስ ቅዱስንም፤ አማላጅ እያሉ እንዴት ይዘልቁታል?


            ነገር ግን ልብ ልንለው የሚገባን፣ በሁሉም ጥቅሶች ላይ ጌታችን የሚመጣ እንጂ የሚሄድ አለማለቱን ነው፣ ይህም ከአብ በአንድነትና በእኩልነት ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው።የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው (የሚፈርደው) ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” /ሮሜ 833-34/ ይላል። አሁን እኮ ግልጽ ነው የሚኮንነው ክርስቶስ ከሆነ መኮነን ደግሞ በፍርድ ውስጥ የተጠቃለለ ነው፣ የመኮነን ሥልጣን ያለው እንዴትና ወዴት ለማንስ ያማልዳል፣ ለማታለል ሲሉ በግዕዝ ይማልዳል ብለው ጽፈውታል ቃሉ ግዕዝ ነው ግዕዝና ፍቺውን የማያውቅ ሊታለል ይችላል። እነርሱ ግን ግዕዝን ይቃወማሉ ለማወናበጃ ግን ሊጠቀሙበት ይሞክራሉ። ቅዱስ ዳዊት ግንየቃልህ ፍቺ ያበራል” /መዝ 119130/ እንዳለ ፍቺው ይመሰክርባቸዋል። ምክንያቱም፦ ይማልዳል የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን ፍቺው ይፈርዳል ነው።

             አማላጅ ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በግልጽ አማርኛያማልዳልብሎ በጻፈ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የሚኮንን ክርስቶስ እየሱስ ነው አለ እንጂ የሚያማልድ አላለም። ከመፍረድ አለፎ የሚኮንን ጌታ አማላጅ እንዴት ይሆናል? እስቲ ፍረዱኝ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ዝቅ ብሎ /በሮሜ 95/ ላይክርስቶስ በሥጋ (በችመቤታችን) በኩል መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን። እንዲሁም ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ /1 ዮሐ 520/ “ክርስቶስ እየሱስ የተባረከና የዘላለም አምላክ ነውብሏል፤ ቶማስም ጌታዬ አምላኬ ሲል መስክሯል፣ እነ ኢሳያስም አማኑኤልነቱን ወይም እግዚአብሔርነቱን ተናግረዋል ታዲያ እንዴት አማላጅ ይሉታል?

            “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” /ዕብ 724-25/ ማዳን እየቻለ አድንልኝ ብሎ ወዴት ይለምን ይሆን? ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ።ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” /1 ዮሐ 21/ እነዚህን እና የመሳሰሉትን ጥቅሶችን በመጥቀስ አማላጅ ነው ይኸው በግልጽ ተጽፏል በማለት ክርስቲያኖችን ለማሳሳት የሚሞክሩ አሉ።

            በእርግጥም ለአዲስ አንባቢ (ለወጣኒነት) በግልጽ የተጻፈና የማያጠራጥር መስሎ ይታየው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስና ትርጓሜው ሕይወቱ ስለሆነ ክርስቲያን ግን የቃሎቹ ትርጉም ይገለፅለታል። የሦስቱ ጥቅሶች አጠቃላይ ትርጉማቸው ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በስጋው ወራት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ደሙን አፍስሶና ስቃይ ተቀብሎ እኛን ከእግዚአብሔር (ከራሱ) ጋር ያስታረቀን (የማለደን) በመሆኑ የማስታረቅ ሥራ አሁንም በቋሚነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሕያው ሆን ይኖራል ማለት ነው።

            ከላይ የተጠቀሱስ ጥቅሶች ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ የፈፀመው የማስታረቅ አገልግሎት ዛሬም ነገም እንደሚያገለግል (መሐሪነቱን፣ ታራቂነቱን፣ ይቅር ባይነቱን፣ ቂም በቀል የሌለበት) መሆኑን የሚመሰክሩ እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ፦ አብን እና መንፈስ ቅዱስ እባክህ ወይም እባካቹ ይቅር በሏቸው (በላቸው) እያለ ያማልዳል ማለት አይደለም። ይልቁኑ ራሱ ጌታችን /በዮሐ 1626/ ላይበዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ እንጂ እኔ ስለ እናንተ አብን ማርልኝ፣ ይቅር በልልኝ፤ ብዬ እንድለምን አይምሰላችሁሲል አስተምሮናል። ስለዚህ ስለእኛ ዘወትር ሊማልድ ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ጌታ አንድ ጊዜ ዓለሙን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የፈጸመው የማስታረቅ ሥራ ዘወትር ያገለግላል (ቃሉ ሕያውና የታመነ) ሆኖ ይኖራል ሲል እንጂ ክርስቶስ አሁን ስለእኛ ይቅር በላቸው እያለ ይለምናል ማለት አይደለም።

            * ጠበቃ አለን ያለውም ጌታችንሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ እኔ ከርሱ እኖራለሁ” /ዮሐ 656/ ባለው ቃል መሰረት የበላነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና የጠጣነው ክቡር ደሙ በፍርድ ወቅት (በእለተ መፅዓት) እንደሚቆምልን ለማመልከት ነው። አንዳንድ ወገኖቻችን (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት ክርሰቶስ ራሱ ጠበቃ ነው ቢባልማ ዳኛው (ፈራጁ) ማን ሊሆን ነው?

                              * መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?

            መጽሐፍ ቅድስ ብዙ ይላል፣ ብዙም ይናገራል (ያስተምራል) ታማሪ ብቻ ሳይሆን አስተዋይ ከተገኘ። እየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅን ሥራ አንድ ጊዜ ስለፈፀመ አሁን አማላጅ ነው እንደማይባል ቅዱስ ጳውሎስ አበዝቶ ጽፏል።

            “እርሱም (ክርስቶስ) በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ” /ዕብ 57/ ይላል። ይህ አባባል በለበሰው ሥጋ ስለመከራውና ስለደረሰበት እንግልት ቢጮኸም ማርልኝ፣ ይቅር በልልኝ ማለቱ ለእኛ አርአያውንና  ምሳሌውን ሲተውልን ነው። እናንተም መከራ ሲበዛባቹ ወደ እኔ ጩኹ ስለሚያሳድዷችሁ እንኳ ጸልዩ ማለቱ አንጂ ከእርሱ ሌላ አምላክ ወይም ይቅር ባይ ኖሮ መጮኹ አይደለም።

            “እንደሌሎቹ ሊቃነ ካህናት... ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” /ዕብ 727/ እንዲሁምእርሱ ግን ስለ ኃጢያታችን አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ (በአንድነትና በሦስትነት በመለኮት፣ ክቡሩ በአምላክነቱ፣ በፈራጅነቱ፣ በአፅዳቂነቱና በኮናኝነቱ )ተቀመጠ።” /ዕብ 1012/

            ክርስቶስ እየሱስ በሥጋው ወራት ስለእኛ ያቀረበው ምልጃ እንደ ፍጡራን ዓይነት ምልጃ (እንደ ቅዱሳን ፀሎትና ምልጃ) አይደለም፤ ትህትናን፣ ጸሎትን፣ ፆምን አብነት ሆኖ ለእኛ እንዳስተማረን ሁሉ ምልጃንም እንዲሁ አስተምሮናል እንጂ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው። እሱም ልክ ከጌታው (ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ) እንደተማረው እኛን ለማስተማርየሚያደርጉትን አያቁምና ይቅር በላቸውሲል ምልጃ አቅርቧል። በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የደሙን መስዋዕት አቅርቦ የደም መስዋዕት ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያስታርቀን እንጂ እንዳንድ ወገኖች (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት ክርሰቶስ ዕለት ዕለት ይቅር በላቸው እያለ ስለእኛ አይለምንም (አያማልድም)

            እንዲያማ ቢሆን እኛ ኃጢያት በሰራን ቁጥር ከሰማይ እየወረደ (እየተወለደ) መከራንም እየተቀበለ፣ ዕለት ዕለትም ደሙን እያፈሰሰ፣ የሾህ አክሊል ደፍቶ በጦር አየተወጋ፣ በጅራፍም እየተገረፈ፤ ሊሰቃይልን ነው ማለት ነው። ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ ሲያረጋግጥክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር።ሲል /ዕብ 924-26/ ላይ ይገልጻል።

            የበሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሰውችን ኃጢያት ለማስወገድ በየዕለቱ የእንስሳ ደም እየያዘ ደወ መቅደስ በመግባት ለእግዚአብሔር ይሰዋ ነበር። እየሱስ ክርስቶስ ግን የራሱን ደም አንድ ጊዜ ወደ ማትታይ ቤተ መቅደስ ይዞ ገባ፣ ታዲያ አንድ ጊዜ የፈሰሰ ደም እስከ ዓለም ፍፃሜ ያድናል እንጂ በየዕለቱ ኃጢያት በሰራን ቁጥር እየመጣ (እየተወለደ) ደሙን አያፈስልንም። ስለዚህም ክርስቶስ አማላጅ ነው አይባልም። በደሙ ድነናል ስንልም በእኛ ሥራ ሳይሆን በእሱ ቸርነት፣ እሱ በስጠን ፀጋ፣ በመስቀል ሞት፤ አዳነን ማለታችን እንጂ እንዳንድ ወገኖች (አሰተኞች ወንድሞች) እንደሚሉት በፀጋው ድነናል ብለን፦ ከፆም፣ ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከምጽዋት፣ ከቅዳሴ፤ በአጠቃለይ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት ተቆጥበን ጌታ ጾሞልናል በማለት ብቻ እጅ እግራችንን አጣጥፈን እንቀመጥ ማለት አይደለም። ሐዋርያው ያዕቆብ አባቻችን ሥራ ወይም በጎ ምግባር የሌለው እምነት የሞተ ነው ይለናል። /ያዕ 217/ ይልቁንም በብዙ ቦታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱየሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” /ዮሐ 635 እና 48/  “እናንተ ሸክማቹ የከበደ ወይም ኃጢያታችሁ የበዛ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” /ማቴ 1128/ “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” /ዮሐ 1414/ አለ እንጂ እኔ አብን፣ መንፈስ ቅዱስን ለምኜ አስደርገላችኋለሁ (አማልዳችኋለሁ) አላለም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ (ተለማኝ) እንጂ አማላጅ (ለማኝ) እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል። ስለ ቃሉ የተመሰገነ ይሁን። አሜን!!!

ዋቢ መጽሐፍ፦ "ማንም እንዳያስታቹ ተጠንቀቁ!" ከመምህር ደምሰው ዘውዴ /ገፅ 29-31/ 2001 /

3 comments:

  1. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  2. አታመሳስል ከአቭ ዘንድ ጠበቃ አለ ማለት ምን ማለት ነው ?

    ReplyDelete