Showing posts with label ነገረ ማርያም. Show all posts
Showing posts with label ነገረ ማርያም. Show all posts

Monday, June 29, 2015

ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና፣ ድንግልና፣ ቃል ኪዳንና አማላጅነት በሰፊው የታወቀ ነው።

ቅድስናዋ

አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፤ /ኢሳ.19/ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ጸጋን ሁሉ የተሞላች ብፅዕት ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡ /መኃ 47 ሉቃ 126-44/ ጸጋን ሁሉ የተመላች፣ ብፅዕት፣ ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅዱስተ ቅዱሳን ስለሆነችምምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽተብላ በቅዱሳን መላእክት አንደበት በቅድስናዋ ተመስግናለች፤ ትመሰገናለችም። /ሉቃ 128-30/

እመቤታችን፥ በውስጥ በአፍኣ፣ በነፍስ በሥጋ፤ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል። ማኅደረ መለኮት እንድትሆን አድርጓታል። አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ፣ ንጽሕናዋ ነው። /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፤ መዝ 13213/ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።

----------------------------------------------------------------------------

Saturday, April 11, 2015

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፬) መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


          በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

                                                                      (ክፍል ፫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)
 

ቅዳሴ ማርያምን በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭነት የደረሰ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብህንሳ ነው። ሕርያቆስ ማለት፦ ለሹመት መርጠውታልና፥ ኅሩይ (ምርጥ) ማለት ነው። አንድም፦ ረቂቅ ምሥጢረ ሥላሴን ይናገራልና፥ ረቂቅ ማለት ነው። እርግጥ ከሊቃውንት ምሥጢረ ሥላሴን ያልተናገረ ባይኖርም፥ እርሱ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል። አንድም፦ አብ ፀሐይ፥ ወልድ ፀሐይ፥ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ብሎ ጽፏልና ፀሐይ ማለት ነው። አንድም፦ የምዕመናንን ልቡና በትምህርቱ ብሩኅ ያደርጋልና፥ ብርሃን ማለት ነው። አንድም፦ ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ፥ እርሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለምና ንብ ማለት ነው።

ሹመትን በተመለከተ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት፦ በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይረታ ዘንድ የተማረ ይሾም፤ ይህም ባይሆን በጸሎቱ ስለሚጠብቅ፥ በትሩፋቱ ስለሚያጸድቅ፥ ባይማርም ግብረ ገብ የሆነ ሰው ይሾም ብለዋል። ይኸውም ትህትናው እስካለ ድረስ ውሎ አድሮ ተምሮ ምሥጢር ያደላድላል ብለው ነው። በዚህ መሠረት አባ ሕርያቆስ ትምህርት ባይኖረውም ግብረ ገብነት ነበረውና እልፍ መነኮሳትና እልፍ መነኮሳይት መርጠውታል። ግብረ ገብ በመሆኑም ሥርዓት ስላጸናባቸው መልሰው ጠልተውታል፥ ትምህርት ስላልነበረውም ንቀውታል። ከዕለታት በአንዳቸው ቀን በምን ምክንያት እንደሚሽሩት አስበው፥ «ቀድሰህ አቊርበን፤» አሉት። ትምህርት ስለሌለው አይሆንለትም ብለው በተንኰል ነው።

የአባ ሕርያቆስ ተምኔቱ (ምኞቱ) እንደ ቅዱስ ኤፍሬም፥ የእመቤቴ ምስጋና፦ እንደ ባሕር አሸዋ፥ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ፥ እንደ ምግብ ተመግቤው፥ እንደ መጠጥ ጠጥቼው፥ እንደ ልብስ ለብሼው የሚል ነበር። የጠሉት እና የናቁት ሊቃውንት፥ «ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን የቱን እናውጣለትእያሉ፥ በኅሊናቸው ሲያወጡ ሲያወርዱ፥ ሥርዓተ ቅዳሴውን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴ ደረሰ። በዚህን ጊዜ፦ የለመኗትን የማትነሳ፥ የነገሯትን የማትረሳ እመቤት ገልጣለት «ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ከሚለው አንሥቶ፥ ወይእዜኒ ንሰብሖ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤» እስከሚለው ድረስ ሰተት አድሮጎ ተናግሮታል።

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ «ክፉ ሰው የሚለውን አያጣም፤» እንዳሉ፥ እነዚያ የሚጠሉትና የሚንቁት ሊቃውንት፦ «ይህ፦ የተናገሩትን ቀለም እንኳ አከናውኖ መናገር የማይቻለው፥ ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እድርሳለሁ ብሎ አገኝ አጣውን ይቀባጥራል፤» ብለው አጣጣሉበት። የሚወዱት እና የሚያከብሩት ግን፦ «እንዲህ ያለ ምሥጢር ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ ከእሩቅ ብእሲ የሚገኝ አይደለም፤» ብለው አጸደቁለት። በዚያውም ላይ «ጽፈን ደጉሰን እንያዘው፤» አሉ። የጠሉት ግን ከንቀታቸው ብዛት «ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለንብለው ተቃወሙ። የሚወዱትና የሚያከብሩትም መልሰው «እንደ ልማዱ አድርገን አንይዘውምንአሉ። በሀገራቸው ልማድ እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ፥ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል፥ ከእሳት ደህና የወጣ እንደሆነ ከውኃ ይጥሉታል፥ ከውኃ ደህና የወጣ እንደሆነ ከሕሙም ላይ ይጥሉታል፥ ታማሚውን የፈወሰው እንደሆነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል። የአባ ሕርያቆስንም ድርሰት ከእሳት ቢጥሉት በደህና ወጣ፥ ከውኃ ቢጥሉት በደኅና ወጣ፥ ከሕሙምም ላይ ቢጥሉት ፈወሰው፥ ይልቁንም ሙት አንሥቷል። በዚህን ጊዜ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው አሥራ አራተኛ ቅዳሴ አድርገው ጠርዘውታል። አባ ሕርያቆስ በዚህ ድርሰቱ ያልተናገረው ምሥጢረ ሃይማኖት የለም። ምሥጢረ ሥላሴን፥ ምሥጢረ ሥጋዌን፥ ምሥጢረ ጥምቀትን፥ ምስጢረ ቊርባንን፥ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል።