ይኼንን ለመፃፍ ያነሳሳኝ ባየኹትና በሰማኹት፣ ጉንጭ አልፈ በሳቃቸው ምክንያት ነው። ሳቁም፥ በፓርላማ
ውስጥ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ፤ በክቡራን የፓርላማ ሠዎችና ለአፈ ጉባኤው ያቀረቡትን ሐሳብ ንግግራቸውን ሲጨርሱ፦ "እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በበረከት ይጎብኛት" በማለታቸው፤ አፈ ጉባኤዉን አባ ዱላን ጨምሮ የፓርላማ አባላቱ እንደሳቁና እንደተሳለቁ የሚያሳየዉን ድምፀ ወምስል (ቪድዮ) ስመለከት እጅጉን ነበር ያዘንኩትና ግራም የተጋባው።
ሳቅ፥ መልካምና ደስ የሚያሰኘው፤ መሳቅ ያለበት፦ ጊዜ፣ ወቅት፣ የተሰበሰቡበትና ያሉበትን ኹናቴ ቀድሞ ማጤን መልካም ነው። እንደ ዐማርኛ መጥፎ አባባሎቻችን "እንደ ንጉሡ ያጎንብሱ፣ ለንጉሡ ያጎንብሱ" ዓይነት ዘወትር ባለ-ሥልጣን በኾነው በልኾነው ነገሮች ሲስቅ፣ ካጠገቡና ከኋላው የሚያጅቡት ሠዎች አብሮ መሳቅ፣ ማሳለቅና ማጉበድበድ፤ የተፃፈ ሕግ እስኪመስል ድረስ፣ ከባለሥልጣኑ፣ ከንጉሠ ጋር አብሮ ያልሳቀና ያላሳለቀ ከፓርላማውና ከሥልጣኑ የሚባረሩ የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም። ይኼ፥ የአሽሙር ሳቅና ስላቅ መቅረት የሚገባው ተግባር ነው! በዛ ላይ የሃገሪቱ ባለ-ሥልጣን ኾነው!
ሥልጣናቸውን ቢለቁ መኖር የማይችሉ የሚመስላቸው፤ በኾነው በልኾነው ነገሮች ለማጎባደድ ሲሉ ብቻ ይስቃሉ። ይኼ ሳቅ ደግሞ፥ ለእነርሱ የተደሰቱ የሚመስላቸው፣ ለሌላው ሕዝቡና ለሰሚው ግን የሚያሳዝን ይኾናል!። የሳቁና የተሳሳቁ፣ መገባደጃቸውና ፍፃሜያቸው፦ ልቅሶ፣ ዋይታ፣ ጩኸት፤ እንደሚኾ ልብ ማለት አለባቸው!። አንተ ወዳጄ፥ ባለ-ሥልጣን ሆይ፦ ይኼን "ሳቅ"ህን በአምላካዊ ቃል ሲታይ፣ ለሥልጣንህና ለሕይወትህ ስንቅ እንድታደርገው እንዲህ ይልሃል፦ "በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው።" /ምሳ ፲፬፥፲፫/
የእግዚአብሔር ስም መጠራቱ እንዲህ የሚያስቅ ከኾነ፤ እነርሱ የሚያመልኩት ምን ይሆን? የእኛ ሃገር መሪዎች ሥልጣኔነት መስሏቸው ነው እንዳልል ያደጉ አገራት መሪዎች ከንግግር በኋላ "እግዚአብሔር ሃገራችንን ይባርክ" ብለው ሲናገሩ አንድም ቀን ሰው ሲስቅ አይቼ አላቅም። ታዲያ ምን የሚሉት ይኾን? የእኛ ሃገር መሪዎች እንዲህ ድዳቸው እስኪታይ መሳቃቸው፥ ከምን የመነጨ ነው?
እኔ ግን፥ አንድ ኢትዮጵያዊ/ት የኾነ/ች፣ አልያልም፥ ኢትዮጵያዊ/ት ባይኾን እንኳን ለሃገራችን ኢትዮጵያ መልካምን ነገር በማሰብ በሚያመልከው አምላክ ስም ጠርጦ "አምላክ ይርዳን" ማለቱ፤ ስለ ኢትዮጵያ ያለው ጥልቅ የኾነ ፍቅር እንዳለው ያስገነዝበናል፤ በተጨማሪም፥ ፈሪሐ አምላክ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር፤ መኾኑንም እንረዳለን እንጂ! ሊላገጥበትና ሊሳለቅበት አይገባም፤ ባይ ነኝ!!!
እኔ አምናለኹ እስካለኩኝ ድረስ በማምንበት እምነትና ሃይማኖት ቃል መሠረት፦ እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያንን እና ህዝቦቻን ይባርክ! እላለው። አሜን! ወዳጆቼ ሆይ፦ እናንተም ይኼንን ድምፀ ወምስል (ቪድዮ) ተመልከቱና ታዘብ!።