(ሪፖርተር፥ ግንቦት
፳፯/፳፻፮ ዓ/ም 04 June
2014)
‹‹ጉዳዩ ውስብስብ ነው፣ ጎሳንና ማኅበራዊ ሕይወትን ይነካካል፤ በመሆኑም የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ አይሆንም›› የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ አብዱላህ አል አዝራቅ
ከእስልምና ወደ ሌላ ዕምነት መቀየር ፍፁም የተከለከለ ነው፡፡ ዕምነት የሚፀናውም በአባት ነው፡፡ ልጆች ከሙስሊም አባት ከተወለዱ የእናታቸው ዕምነት እስልምና ካልሆነ በስተቀር የፍላጎታቸውን ዕምነት መከተል አይችሉም፡፡
ለዕምነት የሚከፈል ዋ ከ70 በመቶ በላይ ሕዝቧ የእስልምና ዕምነት ተከታይ በሆነባት ሱዳን የሌላ ዕምነት ተከታይም ቢሆን ትዳሩን ሲመሠርት የሚዳኘው በእስልምና ሕግ ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ሙስሊሟን ቢያገባ ልጁን የማሳደግ መብት አይኖረውም፡፡ ሚስቲቱም ሃይማኖቱ የሚያዛትን እንደጣሰችና ዕምነት እንደቀየረች ተቆጥራ በወንጀል ሕግ ትዳኛለች፡፡
በሱዳን የእስልምና ሃይማኖትን በሌላ ዕምነት የቀየረ የሚፈረድበት ሞት ነው፡፡ በአፍጋኒስታንና በሌሎችም የእስልምና መንግሥት ያላቸው አገሮች እስልምናን ከመቀየር ጋር በተያያዘ የሚወስኑት የሞት ፍርድ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሙስሊም አስተምርሆ ውስጥ ሆነው ባህላዊ አካሄድ ነው በማለት ቅጣቱ ሞት መሆን እንደሌለበት ከሚናገሩ፣ እንዲሁም ከሌሎች ዕምነት ተቋማት ጋር ሁሌም እንዳወዛገባቸው ነው፡፡
በመንግሥት ተቋማት ደረጃ ብቻም ሳይሆን የእስልምና እምነቱን የቀየረ ወይም የቀየረች ሲገኝ ወይም ስትገኝ በመደበኛ ፍርድ ቤት ደረጃ ሳይደርሱ በአካባቢያቸው ነዋሪዎች ፍርዱ የሚፈጸምባቸውም ቀላል አይደሉም፡፡ በተለይ ደግሞ ሴቶች የብትሩ ሰለባዎች ናቸው፡፡
ሰሞኑን በሱዳን ካርቱም አከራካሪና አነጋጋሪ ሆኖ የከረመው አጀንዳም ይኼው ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊት ክርስቲያን እናትና ከሱዳናዊ ሙስሊም አባት የተወለደችው ማርያም ያህያ ኢብራሂም ክርስቲያን ማግባቷ ከስህተት ተቆጥሮባት እስር ቤት እንድትገባ፣ 100 ጅራፍ እንድትገረፍና በሞት እንድትቀጣ እንዲወሰን ምክንያት ሆኖባታል፡፡