እግዚአብሔር ባዘጋጀልን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መማር እንጀምራለን።
ስለ ጌታችን፣
አምላካችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ትምህርቱ የሚዳስሳቸዉ
ነጥቦች፦
•
ቀዳማዊ ወድኅራዊ ሕያዉ ዘላለማዊ አምላክ ስለመሆኑ፤
•
ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት ስለመወለዱ (ስለ ሁለቱ ልደታት፤
• ስለ ድንቅ ልደቱና የልጅነት ህይወቱ፣ ስለ ጥምቀቱ፣ ስለ ትምህርቱና ስለ ተዓምራቱ፣ ስለ ህማሙ፣ ስቅለቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤዉና ዕርገቱ፣ ዳግመኛም ለፍርድ ስለ መምጣቱ፤ ወዘተ… ይሆናል።
በቅድሚያ አንድን
አካል "አምላክ" ነው ለማለት የአምላክነት ባህርያት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። የሁሉ ነገር
የማንነቱ መገለጫ ወሠን ባህርዩ ነውና። ሰለዚህ
የአምላክነት ባህርያት የሚባሉትና የየትኛዉንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም ፍልስፍና አራማጅ የሚያስማሙት፡-
- ሕያዉነት (ዘላለማዊነት)
- ሁሉን
ቻይነት (Omnipotent)
- ሁሉን
አዋቂነት
(Omniscient)
- በሁሉ
ስፍራ መገኘት፣ በቦታ አለመወሰን (Omnipresent)
- ተወካፌ
ጸሎት ወአኮቴት (የፍጡራንን ሁሉ ጸሎትና ምስጋና ለመቀበል የተገባው)
- ዘሥሉጥ ላዕለ ኵሉ (በሁሉ ላይ የሠለጠነ፣ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው)
ሕያውንት(ዘላለማዊነት):- የዘላለማዊነት ጫፍ ከመገኘት በኋላ (ድኅረ ህላዌ) የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከፊትም የሚኖር ነው። የዘላለም
ጫፍ ፊተኛ እና ኋለኛ መሆን ማለት ነው። በዚህ
ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም "ኣልቦቱ ጥንተ ወኢተፍፃሜት" እንዲል በቀዳማዊነት ባይሆንም በድህራዊነት ግን ሰውና መላዕክት ይመስሉታል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሠው ምሳሌ ሆኖ የባርያውን መልክ ይዞ በመካከላችን ቢገለጥም እርሱ ዘላለማዊ ህያው አምላክ መሆኑን ከዚህ በታች የተጠቀሰበት ምንባባት ያስረዳሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች፦
- መዝ 110፥3 “ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።”
- ምሳ 8፥2-36 "…እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ በቀድሞ ሥራዉ መጀመሪያ፣
ከጥንቱ ከዘላላም ጀምሮ ተሾምሁ
ምድር ከመፈጠርም አስቀድሞ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ።”
- ትን ኢሳ 48፥16 "…ወደ እኔ
ቅርቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስዉር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል"
- ትን ሚክ 5፥2 "አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንደ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን
አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። (ከማቴ
2፥5-6 ጋር
ይገናዘብ)
- ዮሐ 1፥1-3 "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአበሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር…ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳንች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም"
- ዮሐ 1፥30 :- "አንድ ሰው ከኃላዬ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል" መጥምቁ ዮሐንስ ጌታን በሥጋ ልደት 6 ወር እንደሚቀድመዉ በግልፅ የታወቀ ሲሆን እንዴት እንዲህ አለ ቢሉ በቅድምና መኖሩን ማኅፀነ ማርያም የህላዌው መጀመርያ መገኛ አለመሆኑን ለማመልከት ነው።
- ዮሐ 8፥55-59 "… ገና ሃምሳ አመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ኢየሱስም እዉነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" አላቸዉ።
- ዮሐ 17፥5 “… አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንደ በነበረኝ ክብር አክብረኝ”
- ዕብ 1፥10 "… ስለ ልጁ ግን ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናፀፍያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጠማ፣ አንተ ግን
አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም" ቅዱስ ጳዉሎስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት አንዱ ለመሰላቸው እርሱ የመላእክት ጌታ አምላክ እንጂ መልዐክ አለመሆኑን ሲያስረዳ የፃፈው ነው።
- ራዕ 5፥6-8
"…እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትን ያዩታል… ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።
- ራዕ 1፥17-18
"… አትፍራ ፊተኛዉና መጨረሻዉ ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያዉ ነኝ።”
- ራዕ 22፥12
"… እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራዉ መጠን እከፍል ዘንድ ወጋዬ ከአኔ ጋር አለ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው መጀመሪያዉና መጨረሻው እኔ ነኝ።"
ተጨማሪ ጥቅሶች፦ ሉቃ 1፥31-36፤ ዮሐ 10፥30፤ ዮሐ14፥8-11፤ ቈላ 1፥15-20።
ወስብሐት
ለእግዚአብሔር! ይቀጥላል ,,,,,
(ነገረ ክርስቶስ፦
ስለ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በሚል የቀረበልን ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ከክፍል አንድ ጀምሮ እስከ ክፍል ሰባት ያሉትን
ለማንበብ ከፈለጉ ወደ ቀሲስ ታምራት ውቤ ድረ-ገጽ ጎራ ይበሉና ያንብቡ!)
No comments:
Post a Comment