ጠርጠሉስ የተባለውና በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (160 AD - 220
AD) የነበረው ታላቅ ፀሐፊና የክርስትና ጠበቃ ስለ ሰማዕታት ደም በተናገረበት ሥፍራ ያስቀመጠው ነው። ተርቱሊያን/ Tertullian ወይም በእኛ አጠራር ጠርጠሉስ የሚባለው ሊቅ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አባቶች ጋር የሚቆጠር እንዲያውም የላቲኖች (በላቲን የምትናገረው፣ የምትጽፈው) ቤተ ክርስቲያን ወይም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ መጠራት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ሊቅ ነበር። በእኛ በኦርቶዶክሳውያንም ሆነ በካቶሊኮቹ ዘንድ ብዙም ስሙ ሲጠቀስ የማይሰማው ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጡ ስላሉበት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ሊቅ በዚህ ሥፍራ መጥቀስ የፈለግኹት አገሩና ምንጩ የሰሜን አፍሪካ (የዛሬዋ ቱኒዚያ) አካል በሆነችው በካርቴጅ የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነው። [፩]
እንዴት ዓይነት መከራ ይቀበሉ እንደነበረ፣ እንዴት ዓይነት ሰማዕታት ይቀበሉ እንደነበረ፣ በነገሥታቱ ፊት፥ ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ አሉ፦ አውግዙን፣ አሰቃዩን፣ ስቀሉን፥፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ክፋት ለእኛ እውነተኝነት ምስክርነት ነው!። የእናንተ እንዲህ ክፉ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ አረመኔ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ ደካማ መኾን፤ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። [፪]
አሰቃዩን፥ ስቀሉን፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ይኼ ክፋታችሁ፥ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። በእናንተ በተሰቃየን ቁጥር፥ እየበዛን እንኼዳለን፤ የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው። ባሰቃያችሁን ቁጥር እየበዛን እንኼዳለን። የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው። እኛ ሁላችን በሰማዕታት ደም የተዘራን ነን!። [፫]