ጠርጠሉስ የተባለውና በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (160 AD - 220
AD) የነበረው ታላቅ ፀሐፊና የክርስትና ጠበቃ ስለ ሰማዕታት ደም በተናገረበት ሥፍራ ያስቀመጠው ነው። ተርቱሊያን/ Tertullian ወይም በእኛ አጠራር ጠርጠሉስ የሚባለው ሊቅ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አባቶች ጋር የሚቆጠር እንዲያውም የላቲኖች (በላቲን የምትናገረው፣ የምትጽፈው) ቤተ ክርስቲያን ወይም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ መጠራት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ሊቅ ነበር። በእኛ በኦርቶዶክሳውያንም ሆነ በካቶሊኮቹ ዘንድ ብዙም ስሙ ሲጠቀስ የማይሰማው ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጡ ስላሉበት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ሊቅ በዚህ ሥፍራ መጥቀስ የፈለግኹት አገሩና ምንጩ የሰሜን አፍሪካ (የዛሬዋ ቱኒዚያ) አካል በሆነችው በካርቴጅ የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነው። [፩]
እንዴት ዓይነት መከራ ይቀበሉ እንደነበረ፣ እንዴት ዓይነት ሰማዕታት ይቀበሉ እንደነበረ፣ በነገሥታቱ ፊት፥ ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ አሉ፦ አውግዙን፣ አሰቃዩን፣ ስቀሉን፥፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ክፋት ለእኛ እውነተኝነት ምስክርነት ነው!። የእናንተ እንዲህ ክፉ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ አረመኔ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ ደካማ መኾን፤ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። [፪]
አሰቃዩን፥ ስቀሉን፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ይኼ ክፋታችሁ፥ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። በእናንተ በተሰቃየን ቁጥር፥ እየበዛን እንኼዳለን፤ የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው። ባሰቃያችሁን ቁጥር እየበዛን እንኼዳለን። የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው። እኛ ሁላችን በሰማዕታት ደም የተዘራን ነን!። [፫]
እናም ይህ አፍሪካዊ ሊቅ እንዲህ አለ፦ “ …. የበለጠ በገደላችሁን መጠን የበለጠ እንኖራለን (አለን)። የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው። … ጭካኔያችሁ የሚያሳየው እኛን ከምትከሱበት ወንጀል ነጻ መሆናችንን ነው። … እናም ዓላማችሁን ከንቱ ታደርጋላችሁ። ምክንያቱም ስንገደል/ ስንሞት የሚመለከቱ ሰዎች ለምን እንደምንገደል ይገረማሉ። እንደ ወንጀለኛ እና እንደ ተናቀ ሰው ሳይሆን እናንተ እንደምታከብሯቸው ሰዎች በክብር እንሞታለንና። [ስንገደል/ ስንሞት የሚመለከቱ ሰዎች] እውነቱን ሲረዱ ደግሞ እኛን ይመስሉናል/ ከእኛ ጋር አንድ ይሆናሉ (ይቀላቀሉናል)።” [፬]
ለዚህም ነው እስካሁን ድረስ (ሰማዕታተ ዘሊቢያ፤ በዕለተ ቀን ፲፩/፰/፳፻፯ ዓ/ም።) ያለማቋረጥ የሰማዕታት ሱታፌ ክርስቲያኖች የሚቋደሱት። በዘመናችን፥ በክርስትና ሃይማኖታቸው ምክንያት ክርስቲያኖች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፦ በኢራቅ፣ በሶርያ፣ በፓኪስታን፣ በግብጽ፣ በናጄሪያ፣ በኬንያ፣ በሊቢያና በብዙ ሥፍራዎች ደማቸው እየፈሰሰ፣ አጥንታቸው እየተከሰከሰ፣ አንገታቸው በሰይፍ እየተቀላ ነው። [፭]
በጌታችንና በመድኃኒታችን በክርስቶስ ፍቅር «ኃይልን በሚሰጠን በክርስቶስ ሁሉን እችላለን።»[፮] እንዲኹም ደግሞ በአጸደ ሥጋ ኾነ በአጸደ ነፍስ ብንኾን እንኳ፦ «በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።» [፯]፤ ከክርስቶስ ጋር ለመኖር ደግሞ ለእኛ በክርስቶስ ክርስቲያኖች ለተባልን፦ «ልንሄድ ከክርስቶስም ጋር ልንኖር እንናፍቃለን፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና» [፰]፤ ለክርስቶስ መሞታችን የሕይወት መንገዳችንና፣ አክሊላችን ነውና!። ይኼ ሥም ከድንቆችም በላይ ድንቅ ሥም ነው፣ አጋንንት ሥሙን ሲሰሙት ይረበሻሉ፣ ይንቀጠቀጣሉ፣ ይሸበራሉ፤ እኮ ይኼ ስም ማነው? በነቢያት ትንቢት የተተነበየለት፣ በመዝሙራትና በምሳሌ ስለ እርሱ የተነገረ፣ ስሙንም ድንግል ማርያም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ተብሎ የተነገረለት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!!። [፱]
-----------------------------------------------------
ምንጭ፦
[፩] የኤፍሬም የፊት ክታብ (FACEBOOK)፤
[፬] የኤፍሬም የፊት ክታብ (FACEBOOK)፤
[፭] በዘመናችን እየተካኼደ ያለ' ተጨባጭ የዓለም እውነታዎች፤
[፮] (ፊል ፬፥፲፫)፤
[፯] (ሮሜ ፲፬፥፰)፤
[፰] (ፊል ፩፥፳፫)፤
[፱] (ኢሳ ፯፥፲፬፤ ማቴ ፩፥፳፫፤ ሮሜ ፲፬፥፲፩)።
No comments:
Post a Comment