ውድ ወንድሞቻችንንና መምህራኖቻችን፥ ሠላምና ፍቅር በድንግል ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከመላው ቤተሰባችሁ ጋር ይብዛላችሁ።
አንድ ነገር ለማለት ፈልጌ ነበር፥ እርሱም፦ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ስለ መጠቀም> ጠቀሜታው ምንድን ነው? ጉዳቱስ እስከምን ያህል ነው? በሚል የግንዛቤ መስጫ ትምህርት እንዲሰጡን ከማሰብ የመነጨ ነው።
ምክንያቱም፦ እነ "ቀሲስ" ትዝታውና እነ "ቀሲስ" መላኩ ሠሞኑን
በፒያኖ (በኦርጋን) ስለመዘመር የሚያጣቅሱስ የዶክተር ኢሳያስና አለሜ ሥራዎችና አንዳንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር በፒያኖ (በኦርጋን) የዘመሩትን እንደነ ዘማሪ ኪነጥበብ፣ እንደነ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ፣ እንደዘመሩ ይናገራሉ።
ነገር ግን ይህ እውነት በዚያን ጊዜ በፒያኖ (በኦርጋን) የተዘመሩ ዝማሬዎች በነባራዊው ኹናቴ ነው ወይንስ ለቤተክርስቲያን የመዝሙር ማሳሪያ ተደርጎ ለመንፈሳዊ ልዕልና፣ ለመንፈሳዊ አርምሞ የሚሰጠው ጠቀሜታ ታምኖበት ነው ወይ?
ይህንን አርዕስት በዋቢነት የሚጠቀሙት እነ "ቀሲስ" መላኩ ቢኾኑም ከዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ በመነሳት ነው፤ ይህም ሃሳብቸው እንዲህ ይላል፦ <ይኽውም የተደከመበት አጭር መዝሙረ ጸሎት የዜማው ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ ተስማሚ መሆኑን ለመዝሙር አፍቃሪዎቼ አስገነዝባለሁ> (መዝሙረ ጸሎት ገፅ ፱/9፤ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ የፃፉት) ይላል እንጂ በንጉሡም ይሁን በጊዜው የነበረ ቅዱስ ሲኖዶስ፦ በፒያኖ (በኦርጋን) ስለ መዘመር ስለ ጥቅሙና ስለ ጎጂንቱን አይገልፅም፣ አያብራራም!።
የኾነው ኾኖ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ
<የዜማው
ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ምን ያህል በጥልቀት ተገንዝበውት ይሆን ወይ?
በእርግጥ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ በዚሁ በፒያኖ (በኦርጋን) የሚያቆሙ አይመስሉም፣ ምክንያቱ፦ <ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> ያሉትን የዶክተር ኢሳያስን ጽንሰ ሃሳብ> በመያዝ ዛሬ በፒያኖ (በኦርጋን) የተጀመረ ነገ
ይቀጥልና ድረም፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ትራምሬት፣ ጊታር፣ ቫዮሊን ወዘተ . . . እያሉ ይቀጥላሉ።
ስለዚህ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ መሳሪያ> ስለ መጠቀም ስንነጋገር በሕዝብ ብዛትና በፐርሰንት ሳይኾን ለመንፈሳዊ አምልኮና ለመንፈሳዊ ዝማሬ አርምሞ (ተመስጦ) የቱ ነው ወደ መንፈሳዊ ልዕልና የሚመራን? መሠረታዊና ቀና መንፈሳዊ መንገድ የሚመራን የቱ ነው? በኦርጋን ወይንስ በክራር፣ በሳክስፎን ወይንስ በዋሽንት፣ ጃዝ ወይንስ ከበሮ፣ ቫዮሊን ወይስ ማሲንቆ፣ በኦርኬስትራ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚይዙት ዘንግ ወይንስ መንፈሳዊ አባቶቻችን ለምስጋና የሚይዙት መቋሚያ፤ የቱ ነው ለመንፈሳዊ ዝማሬና ለአርምሞ (ለተመስጦ) የሚኾነው?