በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና፣ ድንግልና፣ ቃል ኪዳንና አማላጅነት በሰፊው የታወቀ ነው።
ቅድስናዋ፦
አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፤ /ኢሳ.1፥9/ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ጸጋን ሁሉ የተሞላች ብፅዕት ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡ /መኃ 4፥7፤ ሉቃ 1፥26-44/ ጸጋን ሁሉ የተመላች፣ ብፅዕት፣ ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅዱስተ ቅዱሳን ስለሆነችም “ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ” ተብላ በቅዱሳን መላእክት አንደበት በቅድስናዋ ተመስግናለች፤ ትመሰገናለችም። /ሉቃ 1፥28-30/።
እመቤታችን፥ በውስጥ በአፍኣ፣ በነፍስ በሥጋ፤ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል። ማኅደረ መለኮት እንድትሆን አድርጓታል። አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ፣ ንጽሕናዋ ነው። /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፤ መዝ 132፥13/። ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።
----------------------------------------------------------------------------
No comments:
Post a Comment