(ከሰባኪው ማስታወሻ በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በኅትመት ላይ ካለ መጽሐፍ የተወሰደ።)
*********ዮሐ. 3፥16 “እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፡፡ እኛም ስለወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል፡፡” ብዙ ጊዜ የሚጎዳን ሰው ያደረገብን አይደለም፡፡ ሰዎች ላደረጉብን ነገር የምንሰጠው ምላሽና የበቀል ስሜት የበለጠ ይጎዳናል፡፡ ከምንወዳቸው ስዎች ጋር ከኖርንበት ዘመን ይልቅ ከምንጠላቸው ሰዎች ጋር የምንኖርበት ዘመን ይበዛል፤ ምክንያቱም የምንወዳቸውን ሰዎች ለማግኘት ቀጠሮ ያስፈልጋል። ይቅርታ ያላደረግንላቸው ጠበኞቻችንን ግን ሁል ጊዜ ለበቀል ስልምንፈልጋቸው ስንበላ በምግቡ ውስጥ አሉ፣ ስንተኛ ምኝታችን ላይ ይመጣሉ፣ ስንጸልይ እንኳን በጸሎት ውስጥ ብቅ ይላሉ። የእግዚአብሔር ቃል ግን “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፋ አትሸነፍ፡፡” ይላል። (ሮሜ 12፥21)**********
“ ….ግጭት ሁሉ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም፤ እንዲሁም አብረን እየኖርን ግጭትን ማስቀረት አይቻልም። ቤተክርስቲያን ነን ካልን ግጭትና ፈተና ይጠፋል ብሎ መገመት የዋህነት ነው። ችግሩ የግጭቱ መኖር ሳይሆን የግጭት አፈታት ብስለት ማጣታችንና ለታላቁ ተልዕኮ ስንል በቁጥጥር ሥር ማዋል አለመቻላችን፣ ወይንም አለማወቃችን ነው። ይህ ማለት ችግሩን ማስቀረት ባይቻልም ችግሩ ሲከሰት ግን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ችግሩን የምንፈታበት ጥበብ ሊኖረን ይገባል።*******
ቀሲስ ደረጀ ሥዩም |
“…እኛም የምንቀርብበት ሌላ ችሎት የለንም። ቃሉ የመዳኘት ሥልጣን ያለው ነው። የሥነ-ምግባር የአስተምህሮና የሰይጣን ፈተና የተመለሰው በቃሉ ሥልጣን ነው፡፡”
ቤተክርስቲያን ከዓለምና ከዓለማውያን ጋር ማድረግ የሚገባት ትብብርና ስምምነት ሊኖር አይገባም። ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች ዛሬ እንደጊዜው ይኖራሉ። ለመንፈሳውያኑም “የጊዜውን መንፈስ ውሰዱና እንደጊዜው ኑሩ” ይላሉ። ቤተክርስቲያን በሊቢራሊዝም በሌጋሊዝም በኢሞራሊቲ፣ በማቲሪያሊዝምና በድምፅ አልባ ዶክትሪኖች ተከባ በመንገዳገድ ላይ ትገኛለች። ከራሷ ውስጥ በተነሱ መንፈስ ቅዱስ ያልነካቸው አገልጋዮች፥ የሥልጣን ጥመኞችና ፍቅረ ነዋይ ባሰከራቸው ትታመሳለች፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሥራችን የዘመኑን መንፈስ መዝለፍና የጊዜውን መሳዮች ሳንታክት መገሰጽ ይገባል።************
******የኖኅ መርከብ ፍጥረትን ለማትርፍ አንዲትና ብቸኛ እንደነበረች ሁሉ ዛሬም በእግዚአብሔር አምኖ ለመዳን ብዙ ቤተክርስቲያን የለም:: ቤተክርስቲያን አንዲት ናት።
*******ስለ ቅዱስ መቃርዮስ ሰይጣን ሲመሰክር፦ “መቃርዮስ ሆይ፥ አንተ ትጾማለህ እኔ ጭርሱኑ እህል አልበላም፤ አንተ በትግሃ ሌሊት ታድራለህ እኔ ግን ጭርሱኑ አልተኛም፤ በአንተ ክፉ ላደርግብህ ያልቻልኹት በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ አንተ እኔን ያሸነፍኸኝ በትሕትናህ ነው” አለው ይባላል፡፡ ቅዱስ እንጦንስም የሰይጣን ወጥመድ እስከ ሰማይ ድረስ ተዘርግቶ የሰውን ልጆች እንወጣለን ሲሉ ጠልፎ ሲጥላቸው በማየቱ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበ፤ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የሰይጣን ወጥመዱ እንዲህ ብርቱ ከሆነ ታዲያ ሰው እንዴት ሰይጣንን ማምለጥ ይችላል?” ብሎ ቢጠይቀው "በትሕትና" ብሎ መልሶለታል።********
********እግዚአብሔር በመካከላችን ለመኖሩና ሲጎበኝን ለማየት እንዳንችል ልባችን በብዙ መንፈሳዊ ውድቀቶቻችን ምክንያት በሐዘን ስለተሰበረ ሥራውን ማስተዋልና መገንዘብ የምንችልበት ጊዜ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ኋላ ተመልሰን ከአባቶቻችን የተረከብናትን ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ውበትና መልክ፣ ቅድስናና ግርማ ምን ትመስል እንደነበር ማስብ ብንችልና ብናስተውል ቤተክርስቲያን ውብና የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች፤ ባለቤትዋ እግዚአብሒር እንደማይተዋት፣ እንደማይለያት፣ ሊገባንና ሊታየን ይችላል ብዬ ደግሞ አምናለሁ፡፡************
******….ድኅነትን የሚሻ ያለ ክርስቶስ ጸጋ ሕግን ብቻ በመፈጸም የሚድን የለም፡፡ ስለዚህ ጸጋና ሕግ በክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ውስጥ ሚዛን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ….በጸጋ መዳን ማለት ኃጢአት ለመሥራት ፈቃድ ማግኘት ማለት አይደለም፡፡ በጸጋው ጉልበት ሕግን ለመፈጸም እንጂ።፤*******
No comments:
Post a Comment