‹‹ሰሙነ ሕማማት›› መጽሐፍ
ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በርካታ
ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ
ቅዱስ ውጭ የምትጓዝ አካል
አድርገው ሊገልጧት ይሞክራሉ፡፡ ይህ
እጅግ አላዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ
ያልተገኘና በሥጋዊና በደማዊ ዕውቀት
ላይ የተመሠረተ ሥርዓት የላትም፡፡
ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ
‹‹ከሕማማቱ በኋላ›› በማለት ስለ
ሰሙነ ሕማማት የሚያወሳ ቃል
ተጠቅሟል፡፡ (የሐዋ1.3)
ሰሙነ ሕማማት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ ‹‹ሰሙን›› የሚለው ቃል ‹‹ሰመነ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስምንት ቀኖች ወይም ሳምንት ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የሚለው ቃልም እንደዚሁ ‹‹ሐመመ›› ወይም ‹‹ሐመ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መከራዎች ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የምንለው ለብዙ ሲሆን ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ደግሞ ‹‹ሕማም›› እንላለን፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ቃላት በማናበብ ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ስንል ‹‹የመከራዎች ሳምንት›› ማለታችን ነው፡፡