ደራሲ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዩሐንስ ከጻፉት መፅሐፍ ስለ “ሞራል ድቀት” ብፁዓን ንጹሐነ ልበ ስለ ክርስቲያን ምግባር መሠረት በሚል ለንባብ ካበቁት የተወሰደ።
ሀገር፣ መንደር፣ ቤት ንብረቱን ትቶ ወደ ሩቅ የሄደ ሰው ባይተዋር ይባላል። ይህ ስያሜ በኑሮ አድራሻ መለወጥ ብቻ ምክንያቱን የሚያገኝ አይደለም። የመንፈስ ባይተዋርነትም አለ። ሰው ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ ሳይዘዋወርም ለአዲስ አስተሳሰብ፣ ፈሊጥና የኑሮ መልክ ሊጋለጥ ይችላል። አንደኛው እስኪያይል ወይም ሁለቱም እስኪዋሐዱ ድረስ የወትሮው እና የአሁኑ በሕሊና ውስጥ የባላንጣዎች ተቃርኖ ይፈትራሉ።
እንዲህ ያለ ሰውነት ሲታገል ይቆይና ሲሰለቸው፦ የቸልተኘነት፣ የግዴለሽነት ኢንዲፈረንቲዝም መንፈስ ይሰፍንበታል። ይህ በተለይ የሚገለጸው በሥነ ምግባር መስክ ነው። ሥለታም የነበረው ሥነ ምግባራዊ በሕሊናው ይሰንፋል። የሚመቹ፣ የማይቆረቁሩ፣ የማይጋጩ እንደ ዘዴኝነት፣ ጮሌነት፣ ብልሃተኝነት፤ ያሉ የማይጨበጡ የቀልጣፋ ሰውነት ጠባዮች ያይላል። “አስመሳይ፣ አድር ባይ፣ እንደ እምነቱ የማያምን፣ እንደ ኑሮው የማይኖር፣ የሕሊናውን ብኵርና ለምስር ንፍሮ የለወጠ” ሌላም ሌላም። እንደ አለንጋ የሚጋረፉ ተግሣጾች ወቅታዊነታቸውን የሚያገኙት በዚህ ሳቢያ ይመስለናል። “የሞራል ድቀት” የሚባለው ይህ ሳይሆን ይቀራል? የመነሳቱ፣ የመቆሙ፣ ከራሱ ጋር ተስማምቶ ሚዛን ጠበቆ የመራከመዱ፤ ነገርስ እንዴት ይሆን? ቅን ሕሊና የማያልፈው ጥያቄ ነው።
+++++++++++++++++ +++++++++++++++++