Saturday, July 6, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ወይስ ተማላጅ ?



    ኢየሱስን ክርስቶስ ክብር ይግባውና አማላጅ ነው የሚሉ ወገኖች የሚከተሉትን ጥቅሶች ማስረጃ ነው ብለው ያቀርባሉ።

                  “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።ዮሐ 146 ይህን በመጥቀስ አማላጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ይላሉ። ነገር ግን ይህን ጥቅስ የሚያስረዳን ስለ አማላጅነቱ ሳይሆን አብን ለማወቅ ክርስቶስን በቅድሚያ ማወቅና ማመን እንደሚገባ ነው። ዛሬ የይህዋ ምስክሮች ነን እንደሚሉት እንደ ጆቫዊትነሶች ወይም እንደ አሕዛቦች ክርሰቶስን ሳያምኑና አምላክነቱንና ፈጣሪነቱን ሳንቀበል አምላካችን አብ ብቻ ነው እያልን ብናወራ ዋጋ እንደሌለው የሚገልፅ ቃል ነው። ይህንንም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያረጋግጥልን በዚሁ ጥቅስ ቀጥሎእኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።”  ዮሐ 147 ብሏል።

            “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።ስላለ ወደ አብ የሚወስደን አማላጅ ክርሰቶስ ነው የምንል ከሆነ፦አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” /ዮሐ 637/ “አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” /ዮሐ 644/ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም። /ዮሐ 665/  ሲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯናልና እዚህ ጋር ደግሞ አማላጁ አብ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተትና ኑፋቄ ነው። በሌላ ጥቅስ ላይ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለእኛመንፈስ ቅዱስይቃትታል የሚል ፅፏልናመንፈስ ቅዱስንም አማላጅልንለው ይሆን? ታዲያ አብንም፣ ወልድንም፣ መንፈስ ቅዱስንም፤ አማላጅ እያሉ እንዴት ይዘልቁታል?