Monday, May 19, 2014
Wednesday, May 14, 2014
የሠው፥ ልዩ ዘር ኧረ ወዴት አለ?
ገበሬው በአውድማው እህል ማረስ፤
አፈሩን ይኮተኰተዋል እንዲለስለስ፤
ዘሩን ይዘራዋል በስብሶ እንዲፈርስ፤
ቡቃያው ሲያፈራ ማሳው ሲደርስ።
በዘራው የእህል ዘር መድረስ
በዓይነት፤
እዪ ሐሴት ሲያደርግ ገበሬው ሲደሰት።
አንዳችን ስለ አንዳችን፣ በፍቅር ዓለም ከተዋደድን፤
ልዩነት ከየት ይመጣል፣ በሕይወት ሥር ከሰደድን፤
ዘር ቆጠራ፥ ለእህል እንጂ! ለእኛ ለሠዎች አይኹን፤
በፍቅርና በአንድነት መኖር፣ ቆየን ከተለማመደን።
ገበሬው በዘራው የእህል ዘር ፍሬ መደሰት፤
ያለʼውን፥ አንድነትና ልዩነቱን እንመልከት።
እንዳንኾን፥ ታሪካን ለማፍረስ፤
በልባችን፥ የፍቅር ዘርን እንረስ፤
ኅሊናችን፥ ለሌላው ሲለሰልስ፤
እንደሰታለን፥ ፍሬው ሲደርስ።
የእህል ዘር፥ ዓይነቱ ብዙ ነው፤
የሠው ዘሩ፥ ኧረ ወዴት ነው?።
አፋልጉልኝ፥ የእከሌ ዘር ነኝ ያላለ፤
ይኼ ነው! ልዩ ሠው ለፍቅር የዋለ፤
ፍቅር፥ መተሳሰብና አንድነት ካለ፤
የሠው፥ ልዩ ዘር ኧረ ወዴት አለ?።
ለሃገር አንድነት፥ ኹሌ የሚናፍቀው፤
ባንዲራዋን፥ በፍቅር የሚመለከተው።
ከራሱን ጥቅም ይልቅ ለአንዲት እምዬ ኢትዮጵያችን፤
የወንዙና
የሸንተረሩን ጐጥ ብቻ ያልተመለከተውን፤
አሳዩኝ ይኼን ሠው፥ ለኢትዮጵያዊነቱ ዋጋ የከፈለውን፤
ጀግና ይኼ ነው! ለእናት ሃገሩ አንድነትን የሚሻውን።
በህብረ-ቀለማት ፍቅሩ የረሰረሰና ለሃገር የጸና፤
ለኢትዮጵያችን፥ ይኼ ሠው ነው ታላቅ ጀግና።
ወዳጄ ሆይ፦ ራስህን በመውደድህ፤
ትኖራለህ፥ ሌላውንም ታከብራለህ፤
ለሃገርህም ሠላምና ፍቅርን ትሻለህ፤
ግርማና ክብርበነቷንም
ትናፍቃለህ።
ክብርን ለማግኘት ተቀይሶ የዋለ
የሠው፥ ልዩ ዘር ኧረ ወዴት አለ?
እኔ፥
ከዚህ ዘር ነኝ እንዳንባባል፤
ኹላችን
ከአዳም ዘር ተወልደናል፤
ከማይጠፋው
ዘር ተገኝተናል፤
ክርስቶስ
ፍቅርን አስተምሮናል።
(፭/፲/፳፻፮ ዓ/ም)
Friday, May 9, 2014
ዝክረ ቅዱሳን፦ ማርያምን!!!
በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን!
ወዳጄ ሆይ፦ አንተ አመልከዋለሁ የምትለው አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኾነ፦ ትንቢት የተነበየለት፣ "የዘመኑ ፍፃሜ" ከሴት ብሎ ከእናቱን ከቅድስት ድንግል ማርያምን በሥጋው እንደተወለደ፣ በጌታ ዘንድ ጻድቅና ትጉህም የነበሩ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር አብረው እንደባረኳት፤ እናነባለን እንጂ ክርስቶስን ብቻ እንባርክ አላሉም!። /ሉቃ ፪፥፳፭፤ ገላ ፬፥፬/ ማርያምን!!!
በጌታ ዘንድ ጻድቅና ትጉህም የነበሩ ከባረኳት፣ ለጌታችን፣ ለመድኃኒታች፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ለሥም አጠራሩ ክብርና ልዕልና፣ ውዳሴና ምስጋና፤ ይገባውና አንድ ጊዜ የመረጣቸውን ሐዋርያት እንዲኾኑ ወስኗል። ለዚኽ ነው፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፤ በሮሜ መልዕክቱ፦ "ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?" /ሮሜ ፰፥፳፱-፴፩/ ሲል አንድ ጊዜ የመረጣቸውን እስከመጨረሻው እንዳከበራቸው ይገልጽልናል። ማርያምን!!!
እራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።" ያለበት ያለ ምክንያት አይደለም! ክርስትና መምሰልና መኾኑ እንዳለብን ሲያስገነዝበን ይህን ተናገረ። /፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩/ አንድ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን አምላኬ ነው ካልን፤ መምሰል ደግሞ ግድ ይላል! ያውም፥ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ መምሰልና ኾኖ መገኘት!። ማርያምን!!!
እንደዚህ ዓይነቱ መምሰል ደግሞ የቅዱሳንና የፃድቃንን መትጋትና ተጋድሎ አይቃወምም!፤ ቅዱሳንን ማክበር ከዚኽ ይጀምራል። ዓይነ-ሥውራኖች (ዓይነ-ለሞች) እኮ መዳን ቢፈልጉ "የዳዊት ልጅ ማረን" እንዳሉ ልብ ማለት ይገባል!። /ማቴ ፱፥፳፯፤ ፲፭፥፳፪/ "የዳዊት ልጅ" የሚለው የመጠሪያ ሥም በመንፈሳዊ ዕይታ እንዴት እንደቀደመ ማገናዘብ ይጠይቃል። ለዚኽም ነበር ቅዱስ ማቴዎስ የቅዱሳንን ተጋድሎ ከመናገሩና ከመፃፉ በፊት፤ የወገናቸውንና የአባታቸውን ሥም በማስቀደም በመጥራት ይጀምራል። ለዚኽም አንድ ማሳያ እንዲኾነን፦ "ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች" ይላል። /ሉቃ ፪፥፴፮/ ማርያምን!!!
እንዲኹ ደግሞ፦ በቅዱሳን መንፈስና ክርስቶስን በመምሰል፤ የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናትና አባቷ የነበራቸው መንፈሳዊ ተጋድሎና ሕይወት፣ ስለ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ፅንሰትና ውልደት፣ ሕይወቷና አጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎዋ ቢሰበክና ቢፃፍ፤ የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፦ እግዚአብሔር፥ የጠራቸውን፣ ያጸደቃቸውን፣ ቅዱሳንን ማክበርና ተገቢ መኾኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስረግጦ ገልፆ አስተምሮናል። (በነገራችን ላይ፥ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያናችን ለሌሎችም ቅዱሳን በዓላቸውን ታከብራለች) ስለዚኽ፦ እግዚአብሔር፥ የጠራቸውን፣ ያጸደቃቸውን፣ ቅዱሳንን አለመቃወማች አስረግጠን እንገልጽለን እንጂ! አንቃወምም!። ማርያምን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወድንግል ማርያም ክብር፤ አሜን! (፩/፲/፳፻፮ ዓ/ም)
ልዩ ናት!
ሰይጣን፥ በፈጣሪ መኖር ያምናል፤
ስቶ፥ ለማሳሳትም ቡዙ ይደክማል፤
ከቅዱስ ቃሉም፥ ጥቅስ ይጠቅሳል፤
ቅሉ፥ ይጐለዋል የሃይማኖት ኃይል።
እኔ ሰይጣንን እንዴት ልምሰለው፤
በኤልሻዳይ፥ መኖር የማምነው።
ቅዱሳኑን፥ ለማጥላላት፣ ያለ አግባብ ቃሉን መወርውር፤
ከአምላኬ ነጥዬ፣ እናቱን ላለመቀበል ኅሊናን ማስነውር፤
ላልተገባ ነገር፥ ጥቅስ መጠቃቀስ፣ ብዙ ጊዜ መዳከር፤
ሰይጣን፥ ይለየኛል ከሕይወት ቃሉ፣ ከክርስቶስ ፍቅር።
ዲያብሎስ፥ ይጎለዋል፣ የሃይማኖት እምነት፤
ለምን? ልምሰለው፥ ከእርሱ ጋር በሕብረት።
ሰይጣን፥ ቃሉን ያውቃል ኃይሉን ይክዳል፤
እንደተባለው፥ እጅግም ይንቀጠቃጥማል፤
ያኔ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ተብሎ ተነግሯል፤
ዛሬማ፥ ይኼ እጹብ ድንቅ ቃል ይናፍቀናል።
ዓይኑ እንዲያይ የዳዊት ልጅ ብሎ፤
የአባቶቹን ፈለገ-መንገድ ተከትሎ።
ሕያው ቃሉ፥ ማርያም እናቱ እንደኾነች፤
ያስረዳናል፥ በአምላክ እንደተመረጠች፤
ልዩ ናት! ድንግል እናታችን ለምስራች፤
ከመልአኩ ገብርኤል ሥሙን የሰማች።
እናንተ ሰይጣናት ከእኔ ተፋቱኝ፤
ስለ እናቱ ልዕልና መስካሪ ነኝ።
እኔስ የምለየው፥ ከሰይጣን ምስክርና ማህበር፤
የዳዊት ልጅ፣ የድንግል ልጅ ስል ነው በፍቅር፤
ቃሉ ያስገድደኛል፥ ስለ ቅዱሳኑ እንድመሰክር፤
እንዲከብሩ እርሱ ለመረጣቸው እግዚአብሔር።
ከሕይወት ምንጭ፥ በቃሉ ነፍሴ እንዲኖር፤
እመስክራለሁ፥ በሕያው ጥላ ሳልጠራጠር።
እስኪ ንገሩኝ፥ ጥፋቴ ምኑ ላይ ነው?፤
ምንድን ነው ኃጢያቴ? እኔስ እላለው፤
የድንግል ልጅ ኢየሱስ፥ በሥጋ የተወለደው፤
ክርስቶስ፥ የተዋሕደው በቀረልን ዘር ነው።
<<ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወድንግል ማርያም ክብር፤ አሜን>>
(፩/፲/፳፻፮ ዓ/ም)
Thursday, May 8, 2014
"በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው።" /ምሳ ፲፬፥፲፫/
ይኼንን ለመፃፍ ያነሳሳኝ ባየኹትና በሰማኹት፣ ጉንጭ አልፈ በሳቃቸው ምክንያት ነው። ሳቁም፥ በፓርላማ
ውስጥ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ፤ በክቡራን የፓርላማ ሠዎችና ለአፈ ጉባኤው ያቀረቡትን ሐሳብ ንግግራቸውን ሲጨርሱ፦ "እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በበረከት ይጎብኛት" በማለታቸው፤ አፈ ጉባኤዉን አባ ዱላን ጨምሮ የፓርላማ አባላቱ እንደሳቁና እንደተሳለቁ የሚያሳየዉን ድምፀ ወምስል (ቪድዮ) ስመለከት እጅጉን ነበር ያዘንኩትና ግራም የተጋባው።
ሳቅ፥ መልካምና ደስ የሚያሰኘው፤ መሳቅ ያለበት፦ ጊዜ፣ ወቅት፣ የተሰበሰቡበትና ያሉበትን ኹናቴ ቀድሞ ማጤን መልካም ነው። እንደ ዐማርኛ መጥፎ አባባሎቻችን "እንደ ንጉሡ ያጎንብሱ፣ ለንጉሡ ያጎንብሱ" ዓይነት ዘወትር ባለ-ሥልጣን በኾነው በልኾነው ነገሮች ሲስቅ፣ ካጠገቡና ከኋላው የሚያጅቡት ሠዎች አብሮ መሳቅ፣ ማሳለቅና ማጉበድበድ፤ የተፃፈ ሕግ እስኪመስል ድረስ፣ ከባለሥልጣኑ፣ ከንጉሠ ጋር አብሮ ያልሳቀና ያላሳለቀ ከፓርላማውና ከሥልጣኑ የሚባረሩ የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም። ይኼ፥ የአሽሙር ሳቅና ስላቅ መቅረት የሚገባው ተግባር ነው! በዛ ላይ የሃገሪቱ ባለ-ሥልጣን ኾነው!
ሥልጣናቸውን ቢለቁ መኖር የማይችሉ የሚመስላቸው፤ በኾነው በልኾነው ነገሮች ለማጎባደድ ሲሉ ብቻ ይስቃሉ። ይኼ ሳቅ ደግሞ፥ ለእነርሱ የተደሰቱ የሚመስላቸው፣ ለሌላው ሕዝቡና ለሰሚው ግን የሚያሳዝን ይኾናል!። የሳቁና የተሳሳቁ፣ መገባደጃቸውና ፍፃሜያቸው፦ ልቅሶ፣ ዋይታ፣ ጩኸት፤ እንደሚኾ ልብ ማለት አለባቸው!። አንተ ወዳጄ፥ ባለ-ሥልጣን ሆይ፦ ይኼን "ሳቅ"ህን በአምላካዊ ቃል ሲታይ፣ ለሥልጣንህና ለሕይወትህ ስንቅ እንድታደርገው እንዲህ ይልሃል፦ "በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው።" /ምሳ ፲፬፥፲፫/
የእግዚአብሔር ስም መጠራቱ እንዲህ የሚያስቅ ከኾነ፤ እነርሱ የሚያመልኩት ምን ይሆን? የእኛ ሃገር መሪዎች ሥልጣኔነት መስሏቸው ነው እንዳልል ያደጉ አገራት መሪዎች ከንግግር በኋላ "እግዚአብሔር ሃገራችንን ይባርክ" ብለው ሲናገሩ አንድም ቀን ሰው ሲስቅ አይቼ አላቅም። ታዲያ ምን የሚሉት ይኾን? የእኛ ሃገር መሪዎች እንዲህ ድዳቸው እስኪታይ መሳቃቸው፥ ከምን የመነጨ ነው?
እኔ ግን፥ አንድ ኢትዮጵያዊ/ት የኾነ/ች፣ አልያልም፥ ኢትዮጵያዊ/ት ባይኾን እንኳን ለሃገራችን ኢትዮጵያ መልካምን ነገር በማሰብ በሚያመልከው አምላክ ስም ጠርጦ "አምላክ ይርዳን" ማለቱ፤ ስለ ኢትዮጵያ ያለው ጥልቅ የኾነ ፍቅር እንዳለው ያስገነዝበናል፤ በተጨማሪም፥ ፈሪሐ አምላክ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር፤ መኾኑንም እንረዳለን እንጂ! ሊላገጥበትና ሊሳለቅበት አይገባም፤ ባይ ነኝ!!!
እኔ አምናለኹ እስካለኩኝ ድረስ በማምንበት እምነትና ሃይማኖት ቃል መሠረት፦ እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያንን እና ህዝቦቻን ይባርክ! እላለው። አሜን! ወዳጆቼ ሆይ፦ እናንተም ይኼንን ድምፀ ወምስል (ቪድዮ) ተመልከቱና ታዘብ!።
Subscribe to:
Posts (Atom)