(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣
ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ/ም(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ/ም) ) በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ስመ እግዚአብሔር ቀዳማዊ ዘእንበለ ትማልም፤ ወማዕከላዊ ዘእንበለ ዮም፤ ወደኃራዊ ዘእንበለ ጌሰም ፤ብሉየ መዋዕል ዘእንበለ ዓም፤ ፈጣሬ ኩሉ ዓለም ዘእንበለ ድካም፤ ባህረ ምሕረት ዘእንበለ አቅም፤ ብኁተ ሕሉና እስከ ለዓለመ ዓለም አሜን። "ወባህቱ ለእልክቱሰ ጸላእትየ እለ ኢይፈቅዱ እንግሥ ላእሌሆሙ አምጽእዎሙ ዝየ ወርግዝዎሙ በቅድሜየ= ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው ።" /ሉቃ 19፥27/
መግቢያ፦
“አንተ ደግሞ
እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።”(ምሳ 26፥4)
ክርስትና
ከሰብአዊነት ይልቃል፣ መንፈሳዊነትም ከባለአእምሯዊነት ይበልጣል፤ ሃይማኖትም
ከስሜት በላይ ነው።
በቅርቡ ኢትዮጵያውያንና
ግብጻውያን ቅዱሳን ሰማዕታተ ሊቢያ ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ በተመለክተ ድርጊቱ የእምነቱን መርኅና የቁርአንን አስተምህሮ አይወክልም በሚል ዘውግ ከመሟገትና ከማውገዝ ይልቅ "መጽሐፍ ቅዱሳችሁም ቢሆን :- ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። ይላል እኮ" በሚል ቅዱሱን ቃል ጠቅሶ ለመክሰስና ነቅሶ ለማርከስ የሚዳክሩ በዝተዋል:: እንኳን ቁርአኑ መጽሐፍ ቅዱሱም ቢሆን እንዲህ ይላል የሚለው፦
አንደኛ
ቁርአኑ እረዱ ግደሉ ይላል ብሎ ማመን ሲሆን፤ ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስን ብልጫ ማመናቸውን ያሳየ ነው። ለኛ
ግን መጽሐፍ ቅዱስ ልክ ለመሆኑ ማረጋገጫችን የቁርአን ምስክርነት ወይም የሙስሊሞቹ ቃሉን ማጣቀስ አይደለም ይህንንም ፈጽሞ ከምስክርነትም የምናገባውና ጠቅሰውልናል ብለን የምናመሰግናቸው ዓይደለም:: በአንጻሩ የረከሰውን ሲቀድስና የበደለውን ሲወቅስ ማየቱ፤ በቅዱሳን መጻፉን ተፈትኖ ማለፉንመረዳቱ፤በአዝማናት ጅረት ማለፉንለትውልድ መትረፉን መመልከቱ ብቻ ለኛ አምኖ መቀበል አክብሮ መከተል በቂ ምክንያት ነው:: በስንፍናቸው ለሚኖሩ እንደድክመታቸውና በእነርሱ አመክንዮ ቁርአንማ እንዲህ ይላል እያሉ መመለስ ለቤተክርስቲያናችን የሚያቅት አይደለም ሆኖም ከስንፍናቸው ላለመተባበር የመጡበትንም የጥፋት መንገድ በመናቅ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ብቻ እንናገራለን:: ጠቢቡ እንዲህ ሲል እንደነገረን "አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።" (ምሳ. 26:4) እንግዲህ በዓይነ ሥጋ እያነበበ በዓይነ ህሊና መረዳቱን ለሚሻ ግን በመጀመርያ ቃሉን አብራርቶ ከማስረዳትና ፈቶ ከመግለጥ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በምን መንገድ መረዳት እንደሚገባ ጥቂት ነጥቦች እናስቀምጥ።