Sunday, July 24, 2016

«ምን እናድርግ?» (ሉቃ ፫፥፲፬)

ልጆቼ ሆይ «ምን እናድርግብላችሁ ራሳችሁን ስትጠይቁ በመጽፍ ቅዱስ ላይ በመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ የተነገረውን ቃል አስቡ! ይህን ኃይለ ቃልም ታገኛላችሁ፦ «ጭፍሮችም ደግሞ፥ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ» እንደተባሉ ልብ በሉ!

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ይህ እውነተኛና የታመነ ቃል ነው የምነግራችሁ! በማንም ላይ ግፍ አለመሥራት፣ በማንም ላይ በሐሰት አለመመስከርና አለመክሰስ፣ በማንም ላይ ያልተገባ ጉቦና የተለየ ጥቅማ-ጥቅም አለመጠየቅ፣ በማንም ላይ በሥልጣንህ ተመክተህ ፍርድ አለማጓደል፣ በማንም ላይ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደህ ራስህንም ሌሎች ሠዎችንም በገንዘብ አለመደለል፤ ለሀገርህና ከአንተ አገልግሎት ለሚጠብቅህ ሕዝብ ታማኝ መሆንን አለመዘንጋት፤ በላብህ ዋጋ ሕይወትህን ማጣጣም እንዳለብህም ተረዳ፤ ግፍን፣ ተንኮል፣ ሸርን፣ አሻጥርን፣ ሤራን፣ ምቀኝነትን፣ ከሕይወትህ አስወግድ፤ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ የዋህነትን፣ መልካምነትን፣ ሠናይ ምግባርን፣ አርቆ አሳቢነትን፣ ልበ ሠፊነትን፣ ገርነትን፤ ገንዘብህ አድርግ።

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ከትንሹ እስከ ትልቁ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሕግ አውጪ እስከ ሕግ አርቃቂ፣ ከወታደር እስከ ባለሥልጣናት ድረስ፤ ከቀራጮች እስከ ጭፍሮች፣ አጠቃላይ ሕዝቡ ሁሉ ይሄ አማናዊ ቃል ለራሱ ገንዘብ ሊያደር ይገባል፤ ከላይ የተጠቀሱ እኒህን ነገሮች ስትፈፅሙ የመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ሕይወታችሁን በሐሴት ያረሰርሰዋል፤ እናንተም «ምን እናድርግብላችሁ ለጠየቃችሁት ጥያቄም እግዚአብሔር ምላሽ ይሄ ነው።

(ኃይለ ኢየሱስ ፲፯/፲፩/፳፻፰ /)