Tuesday, December 24, 2013

"የክርስቶስ የሆኑትን ጠልቶ የክርስቶስ መሆን የለም"


          "የክርስቶስ የሆኑትን ጠልቶ የክርስቶስ መሆን የለም" (ታምራት ፍሥሐ) የሚለውን ይህንን ድንቅ አባባል ሳነበው እጅግ መሰጠኝና የአባባሉን ፍሬ-ነገር ሳይለቅ፤ ይህቺን አጭር ጹሑፍ እንድጽፍ እግዚአብሔር መንፈን ቅዱስ አነሳሳኝ።

"የክርስቶስ የሆኑትን ጠልቶ የክርስቶስ መሆን የለም" እንዴት ያለ እጅግ እጹብ ድንቅና ምርጥ አባባል ነው። የክርስቶስ የሆኑትማ፥ እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ፦ "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?" ብለው ያመሰግኗታል፣ እንደ ቅዱስ ገብርኤልም በትህትና ቃል በማክበር፥ "ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ" ይላታል። /ሉቃ 128 እና 43 /

ገና በእናታች ማህፀን ሳለን ጀምሮ የእመቤታችንን ሥሟንና ድምጿን መስማት ለሕይወታችን እንደሚያስፈልገን ለማንም ግለፅ ነው። ለምን ቢሉ? የክርስቶስ ከሆኑት አንዱ መጥምቀ ዩሐንስን እጠራላቸዋለን። እነሆ፥ የቅድስት ድንግል ማርያምን የሰላምታ ድምጽ  በቅድስት ኤልሳቤጥ ጆሮ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኗ በደስታ እንደዘለለ፤ ተመዝግቦልናልና! /ሉቃ 144/

እናቶቻችን ባረገዙ (ነፍሰ-ጡር) ጊዜያት ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም፥ የተፃፉ መንፈሳዊ መፅሐፍትን፣ የተዘመሩ ዝማሬዎችን፤ እንዲሁም ደግሞ ሥሟንና ድምጿን ቢሰሙ ታደለዋል። አሁንም፥ ለምን ቢሉ? በቅድስት ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ እንደሞላባት፥ እንነግራቸዋለን። አሁንም፥ እንቀጥላለን ስለ እመቤታችን፤ የስድብ ቃል ያይደለ፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መሰረት ታመሰግናታለህ። እንዲህ እያልክ "አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ" ትላታለህ። /ሉቃ 142/

ምን ይሄ ብቻ፥ የሃገሬ ሠውም ነፍሰ-ጡር የሆኑ እናቶቻችን በመክበብ፤ ማርያም፥ ማርያም፣ በማለት ድንግል ማርያምን ይጠሯታል። እመቤታችንም የጭንቅ አማላጅ ናትና ምጡ ሳይጠና ልጁ ይወለዳል።

ለምን ቢሉ? ስለ እናታችን እመ ብርሃን፣ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብሯንና ጸጋዋን ጠንቅቆ የተረዳ ሁሉ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ከፈጸመቻቸው ከመንፈሳዊ ምግባራት፣ ከብዙዎች አንዱ የሆነውን፤ በተራራማው አገር ፈጥና ወደ ይሁዳ ከተማ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጉዞ በማስታዎስ፥ ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለልጇ ዕልልታና ምስጋና ያቀርባሉ፤ ከዚያም የወለደችውን እናት "ማርያም፥ ከሽልም ታውጣሽ" ይሏታል። /ሉቃ 139/

ሌላው ደግሞ የክርስቶስ ከሆኑት አንዱ፥ ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ ክታቡ ላይ "ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል። አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ።"/2 ዮሐ 14-5/ ይላል።

ታዲያ፥ ትእዛዝን ከአብ እንደሆነ ሁሉ፤ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በተገኙት ሐዋርያት፣ ቅዱስ ዮሐንስ እጅግ ደስ ካሰኘው፣ "እመቤት" ብሎ በጠራት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመዋደድና አንድ የመሆን ፍላጎት እንዲኖረን "እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ።" ካለ፤ የእግዚአብሔር ወዳጆች ሆይ፦ እኛ፥ የቅዱስ ዮሐንስን ደስታንና ልመናውን፤ አጥብቀን እንፈልግ እንጂ!!!

"የክርስቶስ የሆኑትን ጠልቶ የክርስቶስ መሆን የለም!" በተጨማሪም፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ቅዱስ ጳውሎስ፤ እንዲህ ይለናል፦ "በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና" /2 ቆሮ 112/ ብሎናል። እናም፥ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ብቻ የቀረበች ናት፣ ለእርሱ ለራሱ ብቻ የታጨች መሆኗን ሐዋርያ አስረግጦ አስረዳን! በዚህም ላይ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እኛን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቅርቦንና አጭቶን (እንዳጨን) ነግሮናል።

በቃ! ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ብቻ የቀረበች ናት፣ ለእርሱ እና ለራሱ ብቻ የታጨች፤ እመቤታችን ብቻ ናት!!!

Monday, December 23, 2013

ፍቅሬ ሆይ፦


ፍቅሬ ሆይ፥ ቀኑን ሙሉ ሳስብሽ እውላለሁ፤
እንቅልፍ እየነሳኝ ... ሌሊት ሌሊት እባንናለሁ። 

 
ከመኝታዬ ተንስቼ ... መስኮቴን ከፍቼ፤
ፊቴን ... ሽቅብ ወደ ላይ አንጋጥቼ፤
ዓይኖቼን ... ወደ ሠማዩ አንስቼ፤
ጨረቃዋን ... አትኩሬ ተመልክቼ።


የኮከቦች ድምቀት ... በድቅድቅ ጨለማ፤
ከአድማስ አድማስ ... መድረሷማ፤
ብልጭ ድርግም ... ማለቷማ፤
ልዩ ናት አቀማመጧ ... ጨረቃ ውበቷማ።

ጎህ ሲቀድ ... ጨረቃዋ ስትርቅ፤
የሌሊቱ ቅዝቃዜ ... ለማራቅ፤


ቀረበች ፀሐይ ... ምድርን ለማሸብረቅ፤
ዓለምን ... በብርሃኗ ለማሞቅ።

በጨረቃዋ ፍንጣቂ ... ፍቅሬን እንዳያዋት፤
ከሌሊቱ ይልቅ ... ወዳጄን እጅግ ፈለኳት፤
በፀሐይ ጮራ ውስጥ ... በጧት ፍካት፤
ፊቴ በብርሃን ተሞላ ... ፍቅሬን ስላየዋት።

ጨረቃ፥ ለፀሐይ ቦታዋን ... እንደለቀቀች፤
ፍቅሬን በማየቴ ... ልቤ ሐሴት ተሞላች።

ፍቅሬ ሆይ፥ ... ቀኑን ሙሉ ሳስብሽ እውላለሁኝ፤
እንቅልፍ እየነሳኝ ... ሌሊት ሌሊት እባንናለሁኝ።
የኔ ፍቅር፥ ... እወድሻለሁ፣ አፈቅርሻለሁኝ፤
ይህቺን ሌሊት .. ልደግማት እናፍቃለሁኝ።

ከሥንታየሁ ጌታቸው (ታኅሣስ ፲፩/ ፪፻፮ /)

Saturday, December 21, 2013

“ልጃገረዷን በግድ ቢይዛት አፍንጫውን ይፎንኑት (ይቆረጥ)”

                  ለግብረሰዶማውያን ግን ቅጣታቸው ሰይፍ ነው!” አዲስ አድማስ የተወሰደ 

ልጃገረዷን በግድ ቢይዛት አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ለእርሷም ከገንዘቡ ሲሶውን ይስጧት። አስራ ሶስት ዓመት ሳይሆናት አስቀድሞ ልጃገረዲቱን የያዛትን ሰው አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ከገንዘቡም እኩሌታውን ለእርሷ ይስጧት፡፡

ይህ ሕግ ነው፤ ሴቶችን ከእንስሳዊ ጥቃት ለመታደግ 570 ዓመት በፊት የተደነገገ፡፡ ዘመኑ የአገራችን ሥነ ጽሑፍ አብቦበት እንደነበረ የሚነገርለት ነው - የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1434-1468) ዘመነ መንግስት፡፡ ለሥነ ጽሑፉ መዳበር ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ከጉንዳንጉዶ ገዳም የተነሱት የአባ እስጢፋኖስና ደቀመዛሙርታቸው አዲስ ሃሳብ ማቀንቀን ነው፡፡ መነኮሳቱ ለሚያነሱት አዲስ ነገረ መለኮት መልስ ለመስጠት ሲባል በርካታ መጻሕፍት በንጉሱ እና በተቃራኒው ወይም በነባሩ አስተሳሰብ መመራትን በሚሹ መነኮሳት ይጻፉ ነበር፡፡

ፍትሐ ነገሥትየተባለው የሕግ መጽሐፍ ሥራ ላይ የዋለውም ከዚያ የፍትጊያ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ 1923 . በወጣው ሕገ መንግሥት እስከተተካ ድረስም ለአራት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመታት መንግሥትና ሃይማኖት/በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት/ በተግባር ሲያውሉት ቆይተዋል፡፡

ዛሬየሕግ ትምህርት ቤትእንደሚባለው ድሮ ፍትሐ ነገሥት ራሱን ችሎ ወይም ከትርጓሜ መጻሕፍት ጋር በአንድ ጉባኤ ትምህርቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ፍትሐ ነገሥት የተማሩት ሊቃውንትም ከነገሥታቱ የፍርድ አደባባይ ላይ በመገኘት ነገሥታቱ በፍትሐ ነገሥቱ ህግጋት መሠረት የፍርድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያግዙ ነበር፡፡

Friday, December 20, 2013

ሥራህን ሥራ፦ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ



ሥራህን ሥራ፦ ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰቶታል፤ ያንን መስራት የእሱ ፈንታ ነው። ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያብሎስ ሥራ ነው። በርግጥ ሥራውን እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይጥራል። ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፤ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል። የሃሜት ጎርፍ ያስወርድብሃል። ደራሲያን እንዲጠይቁህ፣ እጅግ ስመጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገርብህ ይጠቀምባቸዋል።

ጲላጦስ፤ ሔሮድስ፤ ሐናንያ፤ ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ። ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሰላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል። ይሄ ሁሉ የደረሰብህ ሰይጣን በዚህ ከስራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዝብ አትችልምን?
ሥራህን ሥራ፦ አላማህ እንደ ኮከብ የጸና ይሁን ተወው አለም እንደፈለገው ይነታረክ ይጨቃጨቅ፡፡ አንበሳው ሲያጋራ ፍንክች አትበል የሰይጣንን ውሻዎችን ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎችን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ

ሥራህን ሥራ፦ ዋሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማህበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ፤ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ። አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈፀም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ።

ሥራህን ሥራ፦ ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክህም፣ እንድትበለጽግም አልታዘዝክም፣ ለክብርህ ተከላከል ብሎ አልተነገረህም፤ ሰይጣን አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየቅህም እነኚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሰራ አትችልም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለጌታ አልሰራህም።

ሥራህን ሥራ፦ አላማህ እንደ አለት የፀና ይሁን፣ ጥቃት ይደርስብህ፣ ትበደል፣ ትሰደብ፣ ትታማ፤ ትቆስልና ትናቅ ይሆናል። አንተ ግን በፀና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ፀንተህየሰጠኽኝን ሥራ ፈፀምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ” ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን አላማና የተፈጠርክበትን ግብ ተከትል።

  --------------------------------------------------------------------------------
        (ምንም ብታደርጉ ሠዎች *በአራቱም አቅጣጫ* ከማውራት ስለማይመለሱ ዝም ብላቹ ሥራችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ!!!)
   ---------------------------------------------------------------------------------