ገበሬው በአውድማው እህል ማረስ፤
አፈሩን ይኮተኰተዋል እንዲለስለስ፤
ዘሩን ይዘራዋል በስብሶ እንዲፈርስ፤
ቡቃያው ሲያፈራ ማሳው ሲደርስ።
በዘራው የእህል ዘር መድረስ
በዓይነት፤
እዪ ሐሴት ሲያደርግ ገበሬው ሲደሰት።
አንዳችን ስለ አንዳችን፣ በፍቅር ዓለም ከተዋደድን፤
ልዩነት ከየት ይመጣል፣ በሕይወት ሥር ከሰደድን፤
ዘር ቆጠራ፥ ለእህል እንጂ! ለእኛ ለሠዎች አይኹን፤
በፍቅርና በአንድነት መኖር፣ ቆየን ከተለማመደን።
ገበሬው በዘራው የእህል ዘር ፍሬ መደሰት፤
ያለʼውን፥ አንድነትና ልዩነቱን እንመልከት።
እንዳንኾን፥ ታሪካን ለማፍረስ፤
በልባችን፥ የፍቅር ዘርን እንረስ፤
ኅሊናችን፥ ለሌላው ሲለሰልስ፤
እንደሰታለን፥ ፍሬው ሲደርስ።
የእህል ዘር፥ ዓይነቱ ብዙ ነው፤
የሠው ዘሩ፥ ኧረ ወዴት ነው?።
አፋልጉልኝ፥ የእከሌ ዘር ነኝ ያላለ፤
ይኼ ነው! ልዩ ሠው ለፍቅር የዋለ፤
ፍቅር፥ መተሳሰብና አንድነት ካለ፤
የሠው፥ ልዩ ዘር ኧረ ወዴት አለ?።
ለሃገር አንድነት፥ ኹሌ የሚናፍቀው፤
ባንዲራዋን፥ በፍቅር የሚመለከተው።
ከራሱን ጥቅም ይልቅ ለአንዲት እምዬ ኢትዮጵያችን፤
የወንዙና
የሸንተረሩን ጐጥ ብቻ ያልተመለከተውን፤
አሳዩኝ ይኼን ሠው፥ ለኢትዮጵያዊነቱ ዋጋ የከፈለውን፤
ጀግና ይኼ ነው! ለእናት ሃገሩ አንድነትን የሚሻውን።
በህብረ-ቀለማት ፍቅሩ የረሰረሰና ለሃገር የጸና፤
ለኢትዮጵያችን፥ ይኼ ሠው ነው ታላቅ ጀግና።
ወዳጄ ሆይ፦ ራስህን በመውደድህ፤
ትኖራለህ፥ ሌላውንም ታከብራለህ፤
ለሃገርህም ሠላምና ፍቅርን ትሻለህ፤
ግርማና ክብርበነቷንም
ትናፍቃለህ።
ክብርን ለማግኘት ተቀይሶ የዋለ
የሠው፥ ልዩ ዘር ኧረ ወዴት አለ?
እኔ፥
ከዚህ ዘር ነኝ እንዳንባባል፤
ኹላችን
ከአዳም ዘር ተወልደናል፤
ከማይጠፋው
ዘር ተገኝተናል፤
ክርስቶስ
ፍቅርን አስተምሮናል።
(፭/፲/፳፻፮ ዓ/ም)