Saturday, April 11, 2015

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፫) መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


        በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

          ፪፦ በውዳሴ ማርያም ትሰብከዋለች። (ካለፈው የቀጠለ . . . ክፍል ፪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)

 ፪፥፫፦ ነፃነትን ሰበከላቸው

      አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን በግብርናተ ዲያብሎስ ተይዘው (የዲያብሎስ ባሮች ሆነው) ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን፥ እስከ ልጅ ልጆቻቸው በሲኦል ኖረዋል። ኑሮውም የሥቃይና የፍዳ ነበር፥ ይህም ያን ዘመን፥ ዘመነ ፍዳ፣ ዘመነ ኲነኔ አሰኝቶታል። ጊዜው ሲደርስ (እግዚአብሔር፦ አምስት ቀን ተኲል ሲፈጸም፥ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ለአዳም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ዘመን ሲደርስ) ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ፥ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወለደ። ቀስ በቀስ አድጎ በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ፥ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተማረ፥ ተአምራትንም አደረገ፥ በመጨረሻም በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ (ሥጋውን በመቁረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ በመስጠት) የሰውን ልጅ አዳነ። በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስን መቃብርን አጠፋ፥ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፥ ሲኦልን ባዶ አስቀረ። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሞቷልና፤ ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር (ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ፥ ወደ ራሱ እና ወደ ባሕርይ ሕይወቱ ወደ መንፈስ ቅዱስ) ያቀርበን ዘንድ ስለእኛ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፤ (በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ኹኖ ሞተ) በመንፈስ ግን (በመለኰት) ሕያው ነው። በእርሱም (ሥጋን ተዋሕዶ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር እንደወረደ፥ ነፍስንም ተዋሕዶ በአካለ ነፍስም) በወኅኒ (በሲኦል) ወደአሉ ነፍሳት ሄዶ ነጻነትን ሰበከላቸው።» በማለት ገልጦታል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰-፲፱። ይኽንን ታላቅ የነገረ ድኅነት ምሥጢር ይዘን ወደ ውዳሴ ማርያም ስንሄድ፦ «ፈቀደ እግዚህ ያግዕዞ ለአዳም ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ወያግቦዖ ኀበ ዘትካት መንበሩ፤ ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞው ቦታው (ወደ ጥንተ ርስቱ ገነት) ይመልሰው ዘንድ ወደደ፤» ይለናል። (የሰኞ . ) በተጨማሪም፦ «በዳዊት አገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ነፃ አደረጋቸው፤» እያለ ይሰብከናል። (የሰኞ . )

   ፪፥፬፦ ጌትነቱ፥ አካላዊ ቃልነቱ፥ አምላክነቱ፥ ልጅነቱና ስሙ

      በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፦ ነገረ ክርስቶስ (ምሥጢረ ድኅነት) ከስብከት አልፎ ጸሎት፥ መዝሙር፥ ቅዳሴ፥ ማኅሌት ሆኗል። የሰባቱን ዕለታት ውዳሴ ማርያም በግዕዝም ሆነ በአማርኛ የምንደግም (የምንጸልይ) ሰዎች፥ እግዚአብሔር የሚለውን ስም ሠላሳ አምስት ጊዜ፥ ጌታ የሚለውን ሃያ አንድ ጊዜ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ሠላሳ ሰባት ጊዜ፥ መድኃኒት የሚለውን ሠላሳ ሰባት ጊዜ፥ አማኑኤል የሚለውን አምስት ጊዜ፥ መለኮት የሚለውን ዘጠኝ ጊዜ፥ ንጉሥ የሚለውን ዘጠኝ ጊዜ፥ ፈጣሪ የሚለውን አራት ጊዜ፥ ብርሃን የሚለውን አሥራ አራት ጊዜ፥ ሕይወት የሚለውን አምስት ጊዜ እንጠራለን። ኃይለ ቃሉ ትርጓሜው እና ምሥጢሩ በትክክል ነገረ ድኅነትን የሚሰብክ፥ ቀራንዮን የሚያሳይ ነው።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፪) መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

                በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

                                                                                          (ክፍል ፩ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ) 


፪፦ በውዳሴ ማርያም ትሰብከዋለች

ውዳሴ ማርያም፦ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፥ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች ሆና  ለምትከብር ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ያቀረበው ምስጋና ነው። ሊቃውንት የቤተክርስቲያንን ትምህርት ገና በሕፃንነት የሚጀምሩት ከውዳሴ ማርያም ነው። (ንባቡን ቃል በቃል ማጥናት የሚጀምሩት በአምስት እና በስድስት ዓመታቸው ነው) የዜማውንም ትምህርት እስከ ድጓ ድረስ የሚዘልቁት፦ «ሰላም ለኪ፤» ብለው ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምረው ነው። የዚህንም ጣዕሙን የሚያውቁት በውስጡ ያለፉ ሰዎችና ሲነገራቸው የሚገባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ግን አይገባውም። በውስጡ አልፈውም በዕውቀት ብቻ የቀረባቸው፥ ከሰውነታቸው ያልተዋሐዳላቸው፥ ምሥጢሩ የተሰወረባቸው፥ ማሩ  የመረረባቸው፥ ወተቱ የጠቆረባቸው፥ «ነአኲተከ» እንኳ ካላሉት መናፍቃን፥ ዕድል ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው የሆነባቸውም ጥቂቶች አይደሉም። የጥንቶቹ መናፍቃን ቢያንስ የተማሩ ናቸው፥ ነገር ግን በዕውቀታቸው ሲመጻደቁ አጓጉል ፍልስፍና ውስጥ እየገቡ በትዕቢት ምክንያት፦ ትርጓሜው፥ ምሥጢሩ እየተሰወረባቸው ተስነካክለዋል።

የውዳሴ ማርያም ድርስት የመንፈስ ቅዱስ ድርሰት ነው፤ በትርጓሜው መቅድም ላይ፥ ስለ ደራሲው ስለ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል። ቅዱስ ኤፍሬም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው። ያዕቆብ ዘንጽቢን ቊጥሩ ከሠለስቱ ምእት (ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ነው። እነዚህም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው፥ «ወልድ ፍጡር ነው፤» (ሎቱ ስብሐት) ያለ አርዮስን በአ ፍም በመጽሐፍም ረትተው እርሱን እና ትምህርቱን አርዮስን አውግዘው የክርስትናን ሃይማኖት ያጸኑ ናቸው። ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስም ሦስት መቶ አሥራ ዘጠነኛ እየሆነ በመካከላቸው ይገኝ ነበር። ይኸውም  ይታወቅ ዘንድ ጉባኤውን ከመጀመራቸው በፊት ሦስት መቶ አሥራ ስምንት የነበሩት፥ ጉባኤውን በጸሎት ሲከፍቱ ሦስት መቶ አሥራ ዘጠኝ ይሆኑ ነበር። ጉባኤውን በጸሎት ከዘጉ በኋላ ደግሞ ተመልሰው ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ይሆኑ ነበር። «በዚህም፦ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት፥ እኔ በዚያ በመካከላቸው እኖራለሁና።» ያለውን ቃሉን ፈጽሞላቸዋል። ማቴ ፲፰፥፳። ከዚህም ሌላ፦ «እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ።» በማለት ለአባቶቻቸው ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸውን ቃል ኪዳን አጽንቶላቸዋል። ማቴ ፳፰፥፳። ዘመኑም ፫፻፳፭ / ነው።