Friday, March 8, 2013

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል አንድ)

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 
የእቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር፦

1. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን አያከብሯትም፣ ምልጃም አይጠይቋትም፣ በዓላቶቿንም አያከብሩም፤ አንዳንድ ቡድኖች ጭራሽ ጫጩት ከተፈለፈለ ወዲያ ዋጋ በሌለው እንቁላል ቅርፊት ሊመስሏት ይወዳሉ። ፕሮቴስታንቶች እመቤታችንን ላለማክበር የሚያደርጉት ይህ ሁሉ ተቃውሞ ምናልባት ካቶሊኮች ለእርሷ ከሚሰጧት የተጋነነና ቅጥ ያጣ ክብር የመጣ ይመስለኛል።

2. አንዳንድ ፕሮቴስታንት አንጃዎች ጭራሹን ደፋር ከመሆናቸው የተነሳ እመቤታችንን “እህታችን ማርያም” ብለው ይጠሯታል።

3. በተጨማሪም ፕሮቴስታንቶች ጌታችንን ከወለደች በኋላ የዮሴፍ ሚስት ሆና ኖራለች፣ ለዮሴፍ “የኢየሱስ ወንድሞች” ወይም “የጌታ ወንድሞች” በመባል የሚታወቁ ልጆችን ወልዳለታለች ይላሉ።

4. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን እንዳያከብሩ ደረጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው “ጸጋን የተሞላሽ” የሚለውን የመላኩን ቃል “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” በሚለው ሐረግ በመለወጣቸው ነው ።

5. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን በ1980 ዓ/ም አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው “አንቺ ጸጋን የተሞላብሽ ሰላም ላንቺ ይሁን እግዚአበሔር ከአንቺ ጋር ነው” ካለ በኋላ በቅንፍ ውስጥ “(አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ)” ብለው ፅፈዋል።
                                             እምቤታችንን ማክበር

ስለ እመቤታችን ክብር በመጽሐፍ ቅዱስ የተፃፈውን የእመቤታች ንግግር መጥቀስ በቂ ነው እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል። ሉቃ 1፥48 እዚህ ላይ ትውልድ ሁሉ የሚለው ሐረግ ከኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እመቤታችንን ማክበር ዓለም አቀፋዊ ባህለ ሃይማኖት እንደሆነ ያረጋግጥልና

በመጽሐፍ ቅዱስ እመቤታችንን ስለማክብር የተፃፉ ብዙ ጥቅሶች አሉ፣ ለምሳሌ በእመቤታችን እናት ዕድሜ የነበረችዋ ቅድት ኤልሳቤጥ እመቤታችንን “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።”  ሉቃ 1፥ 43-44 አለቻት እዚህ ላይ የሚያስደንቀን ነገር ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን ሰላምታ በሰማች ጊዜ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባት” የሚለው ሐረግ ነው። የእመቤታችንን ድምፅ መስማት ብቻ ኤልሳቤጥን መንፈስ ቅዱስ እንዲሞላባት አደረጋት።

እመቤታችን ክብርን ከሰው ልጅ ብቻ የቀበለች አይደለችም ከመላዕክትም ጭምር እንጂ፤ ይህም ቅዱስ ገብርኤል “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ።” /ሉቃ 1፥28/ ሲላት ተረጋግጧል፣ “ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” የሚለውን ሐረግ  ኤልሳቤጥም ለእመቤታችን ሰላምታ ስትሰጥ ደግማዋለች /ሉቃ 1፥42/ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ከእመቤታችን ጋር በተነጋገረበት ሁኔታ ከካህኑ ከዘካርያስ ጋር ከተነጋገረበት ሁኔታ እጅግ የተለየ እንደነበር እናስታሳለን። “ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት።” /ሉቃ 1፥12/  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ባነጋገራት ጊዜ ግን በሚያስፈራ ሁኔታ አልቀረባትም ነበር ይህም ይህም የእመቤታችን ክብር ያሳየናል።

ስለ እመቤታችን የተነገሩ ብዙ ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ፣ እነርሱም “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” በድጋሚ ስለእርሷ “ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው።” /መዝ 45፥9 እና 13/ ይላል ስለዚህ እመቤታችን የንጉሥ ልጅ ንግሥት ነች፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችንም ከጌታችን በስተቀኝ ዘውድ የተቀዳጀች ንግሥት አድርጋ የምትመስላት ለዚህ ነው። ቤተክርስቲያን በመዝሙሯ እመቤታችንን “መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጪያለሽ።” /ምሳ 31፥29/ በማለት ታስመሰግነናለች።

* እመቤታችን የጌታችን የኢየሱስ እናት እንደመሆኗ ለጌታችን የሚሰጡት ስሞች ሁሉ ለእርሷ ሊሰጧት ይችላሉ።

* ጌታ ኢየሱስ እውነተኛ ብርሃን ነው። /ዮሐ 1፥9/ ስለራሱም “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” /ዮሐ 8፥12/ አለ፣ ስለዚህ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የእውነተኛ ብርሃን እናት (እመብርሃን) ነች።

* ክርስቶስ አዳኝ እንደመሆኑ ለእረኞች “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድሐኒት ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋና” /ሉቃ 2፥11/ ተብሎ ተነገረ። ኢየሱስ ማለት መድሐኒት ማለት ነው፣ መድሐኒት የተባለበት ምክንያት ሕዝቡን ከኃጢያታቸው ስለሚያድናቸው ነው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የመደኀኒያለም (የመድሐኒት) እናት ነች።

* ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደመሆኑ /ዮሐ 20፥28 ሮሜ 9፥5 1ኛ ዮሐ 2፥23/ እመቤታችንም የእግዚአብሔር እናት /ወላዲተ አምላክ/ ነች።

* ኤልሳቤጥ እመቤታችንን “የጌታዬ እናት” /ሉቃ 1፥43/ እንዳለቻት እመቤታችን የጌታችን እናት ነች። በተጨማሪም የአማኑኤል እናት ነች፣ /ማቴ 1፥24/ ሥጋ የሆነ ቃል  /የሥግው ቃል/ እናት ነች። /ዮሐ 1፥14/

* ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናት ከሆነች የሁሉም ክርስቲያኖች መንፈሳዊት እናት መሆኗ አያጠያይቅም። ይህንንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ አረጋግጦልታል።  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ  ለተወደደው ደቀመዝሙሩ “እናትህ እነኋት” አለው። /ዮሐ 19፥27/ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ እናቱ ከሆነች ቅዱስ ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ” /1ኛ ዮሐ 2፥1/ ለሚለን ለእኛ ለሁላችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታችን ነች ማለት ነው። ስለዚህ “እኅታችን” የሚለው መጠሪያ ተቀባይነት የለውም፣ አቤት የሚል ምላሽም አያስገኝም።

* በስሙ ለምናምንና ልጆቹ ለሆንን ለኛስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንዴት ብላ እኅታችን ትሆናለች? ለእኛስ የእርሱ ልጆች የእርሷ ወንድምና እኅቶች መሆን እንዴት ይቻለናል?

* እናትን ማክበር ታላቅ ተስፋ ያዘለ ትዕዛዝ ከሆነ /ዘጸ 20፥12 ዘዳ 5፥16 ኤፌ 6፥2/ የጌታችንና የሐዋርያቱን እናት፣ መልአክ፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል” /ሉቃ 1፥35/ ብሎ የተናገረላትና ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት /ሉቃ 1፥45/ ብላ ቅድስት ኤልሳቤጥ የተናገረችላትን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማክበር የለብንምን?

እመቤታችን በዓለም ካሉ ሴቶች ትበልጣለች ቤተክርሰቲያንም ይህንን ክብሯን እያሰበች (መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ) ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ትላታለች። በተጨማሪም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ “ከሴቶች መካክል የተባረክሽ ነሽ” ተብሎ ተነግሮላታል፣ ምክንያቱም ምንም ሴት እመቤታችን የነበራትን ንፅህና አልነበራትምና ነው፣ ይህም የእርሷን ውዳሴና ከፍ ያለ ክብር ያሳያል፤ ስለዚህም ነው ነቢየ ኢሳያስ ስለ ግብፅ የተነገረ ሸክም በተሰኘው ትንቢቱ “ደመና” ብሎ የሰየማት። /ኢሳ 19፥1/

* በሥጋዌ ጊዜ በእመቤታችን ማህፀን ማደሩን በተመለከት ቤተክርስቲያን እመቤታችንን (ዳግማዊት ሰማይ) ሁለተኛ ሰማይ እና የሙሴ ጽላት ብላ ትጠራለች።

* በተጨማሪም ቤተክርስቲያን እመቤታችንን “የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል ... እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።” /መዝ 86/ ትላታለች።

·        ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በና እንደሚመሰል ተናገረ፣ ምክንያቱም እርሱ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነውና። /ዮሐ 6፥58/ ስለዚህ ቤተክርስቲያን እመቤታችንን “የመና ሙዳይ” ብላ ትጠራታለች። ስለ ድንግልናዋም “የለመለመች የአሮን በትር” /ዘኁ 17፥8/ ብላ ትጠራታለች።
·        እመቤታችን በታቦት ትመሰላለች /ዘጸ 25፥ 10-22/ ምክንቱም መጀመሪያ ታቦቱ በውስጥና በውጭ በወርቅ ተለብጧልና፣ በንፅህናዋና በክብሯ ይመሰላል፣ ሁለተኛ ሁለተኛም ታቦቱ በማይነቀዝ የግራር እንጨት ተሰርቷልና በቅድስናዋ ይመሰላል፣ ሶስተኛም ታቦቱ መና ይቀመጥበታለና እርሱም ከሰማይ የወረደ የእይወት እንጀራ በሆነ በክርሰቶስ ይመሰላል፣ እሷ ደግሞ በታቦቱ፣ በመጨረሻም ታቦቱ ሁለቱን የህግ ጽላቶች ይዟል፣ እነርሱም፦ የእግዚአብሔር ቃል የክርስቶስ ምሳሌዎች ናቸው። /1ኛ ዮሐ 1፥1/

·        ሰማያዊውን አምላክ ስለተሸከችውና ስለወለደች ያዕቆብ በህልሙ ከሰማይ እስከ ምድር ያያትን መሰላል ትመስላለች፣ ምክንያቱም በክርስቶስ ሥጋዌ የሰማይና የምድር መገናኘት በእርሷ ተደርጓልና። መንፍስ ቅዱስ ከመለኮታዊ እሳቱ ጋር በእርሷ ባደረ ጊዜ አላቃጠላትምና ሙሴ ሳይቃጠል ባያት ቁጥቋጦ ትመሰላለች /ዘጸ 3፥ 2-4/ የክርስቶስ ሥጋና መለኮት መዋሐድ የእሳትና የከሰልን መዋሐድ ይመስላል፣ ስለዚህም ቅድስት ማርያም ይህንን ውህደት የተሸከመች ማዕጠንትን ትመስላለች፣ በመሆኑም የአሮን የወርቅ ማዕጠንት ትባላለች፣ ይህም ክብሯን ያሳያል።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ርግበ ሰናይት /መልካሟ ርግብ/ ብላ ትጠራታለች። ምክንያቱም፦

1.        በትህትናዋ ርግብን ትመስላለችና፣
2.      በርግብ አምሳል የታየ መንፈስ ቅዱስ /ማቴ 3፥16/ በእርሷ ላይ ወርዷልና፣
3.      ለሰው ለጆች የመዳን /የድህነት/ ብስራትን አምጥታልናለችና፣ በምድር ጥፋት ላይ የሕይወት መመለስን ባበሰረችው ርግብ ትመሰላለች። /ዘፍ 8፥ 10-11/ ለእመቤታችንና ለቤተክርስቲያን ለሁለቱም በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ትንቢቶች ስለተነገሩ እመቤታችን በቤተክርስቲያን ትመሰላለች፣ በቅዱሳን መጻሐፍትና በንዋየ ቅዱሳት ትመሰላለች፣ የእመቤታችን ምሳሌዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።

ይቀጥላል ...
---------------- ይቆየን!!!  --------------

ዋቢ፦ መጽሐፍ  “አንጻራዊ ትምህርተ መለኮት” አዘጋጅ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ  
                                                   ትርጉም ያየህይራድ አስናቀ
 

No comments:

Post a Comment