እነዚህ ራሳቸውን “ተሐድሶ” ብለው የሚጠሩ አካላት ለራሳቸው ከማመን አልፈው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ያልሆነ መልክ በመስጠት ፕሮቴስታንታዊ የሆነውን የራሳቸውን አዲስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በግድ ለመጫን እየተንቀሳቀሱ ነው። የእነዚህ አካላት ዋና ዋና ስልታቸው ሦስት ናቸው። እነሱም፦
1፤ አንደኛው ስልት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና አስተምሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከቀደምት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተለየ እና የራቀ አስመስሎ ለማሳየት መሞከር ነው። ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንናችንን አስተምህሮዋንና እምነቷን፣ ምስጢራቷንና ሥርዓቷን፣ ይትበሃሏንና ትውፊቷን፤ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሕወቷን በሙሉ ከጥንቱ ከጌታችንና ከሐዋርያት እንዲሁም ከሊቃውንት ትምህርት የራቀና የሚቃረን አስመስሎ ማሳየት ነው። ይህም ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልኳ ያልሆነውን ሌላ መልክ በመስጠት ሰዎች ከልቦናቸው ውስጥ እንዲያወጧትና እንዲጠሏት ለማድረግ የረዳናል በሚል ነው። ለዚህ ዓላማቸውም ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታምነውን እንደማታምን፣ የማታምነው ደግሞ እንደምታምን፣ የምትለውን ደግሞ እንደማትል፣ የማትለውን ደግሞ እንደምትል እያስመሰሉ ያለ ይሉኝታና ያለ ኃፍረት ደጋግመው ጽፈዋል።
ተሐድሶዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐዋርያዊ እና ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ጥላሸት ለመቀባት ይረዳናል ያሉትን ነገር ሁሉ አንዳችም ሳያስቀሩ አሟጠው ለመጠቀም ሞክረዋል። ጽሑፋቸው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን በመንቀፍና በማጥላላት ላይ ያተኮረና ያመዘነ ነው። ለዚህም እነርሱ ሌሎችም የሚነቅፉበትን ነገር ሳይቀር ለራሳቸው ሲሆን ደግሞ በአዎንታ ተቀብለው ተጠቅመውበታል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ብዙ ምንጮችንና ነገሮችን ከመጠቀማቸውም ባሻገር ባለቤትነታቸው ከሚታወቁት ሆነ ከማይታወቁ ተረቶችና ወጎችን እንኳ ሳይቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመንቀፍ የሚጠቅም መስሎ እስከታያቸው ድረስ ለመጠቀም ሞክረዋል። አንድን ነገር ደግመው ደጋግመው በመመላለስና ስድቡና ነቀፋውም ቢሆን መልኩን ከመለወጥ በስተቀር ያለቀባቸው መሆኑን አፍ አውጥቶ እስኪናገር ድረስ ያንኑ ነገር በየመጣጥፎቻቸውና በየገጹ ያቀርባሉ።
ተቀባይነታቸውን ለማስፋት ሲሉም “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ከሁለት በመክፈል ራሳቸውን “የጥንቱ ኦርቶዶክስ” ብለው ሲመድቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምታምነውና የምታደርገውን ደግሞ ከጥንቱ የተለየ ነው ለማለት “የአሁኑ ኦርቶዶክስ” የሚል ታርጋ ሊለጥፉላት የሞከሩም አሉ። ይህም ራሳቸውን ፕሮቴስታንት አይደለንም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነን ለማለት ነው። ይህን መጠቀም የሚፈልጉትም ቤተ ክርስቲያኒቷን ከውስጥ ሆነው ሙሉ በሙሉ ቀስ በቀስ በሂደት በመሸርሽር ኦርቶዶክሳዊ ማንነቷን በማሳጣት ፕሮቴስታንት የማድረግ ስውር ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስ እንዲረዳቸው ነው።
ሁሉተኛ፦ ተሐድሶዎች ራሳቸውን በየመጣጥፎቻቸውና በየገጹ፣ በንግግራቸው ሁሉ “የጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” እንደሆኑ ለማሳየት እንዴት እንደሚዳክሩ “መድሎተ ጽድቅ” (የእውነት ሚዛን ቅጽ ፩) በሠፊው ያትታል። ወዘተ. . .
ሦስተኛ፦ ስልታቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አስተምህሮ ላይ ያቀረቡት ነቀፋና ማሳጣት እውነት ለማስመሰል ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ትምህርቶች መካከል ለሃሳባቸው ድጋፍ ይሆናል ያሏቸውን የተወሰኑ ነገሮች ለመጠቃቀስ መሞከር ነው። ወዘተ. . .
-----------------------------------------------
ምንጭ፦ “መድሎተ ጽድቅ” (የእውነት ሚዛን ቅጽ ፩) ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፤ መጋቢት ፳፻፯ ዓ/ም
-----------------------------------------------
((የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ስውር ደባቸውንና ማንነታቸውን [በዩቱብ ክፍል 1 እና ክፍል 2 እዚህ ተጭነው ይመልከቱ] እንዲሁም ደግሞ "የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ሀራ ጥቃ" ስውር ደባቸውንና አጠቃላይ ስራቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያስቃኝና ሊነበብ የሚገባ እጹብ ድንቅ ምላሽ፣ እጅግ ምጡቅ፣ በጥልቀትና በምርመራ፣ በመረጃና በማስረጃ የተደገፈና የተጻፈ ልዩ መጽሐፍ “መድሎተ ጽድቅ” የእውነት ሚዛን! አንብቡ፣ ለሌሎችም ያስነብቡ!።)
No comments:
Post a Comment