Sunday, July 24, 2016

«ምን እናድርግ?» (ሉቃ ፫፥፲፬)

ልጆቼ ሆይ «ምን እናድርግብላችሁ ራሳችሁን ስትጠይቁ በመጽፍ ቅዱስ ላይ በመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ የተነገረውን ቃል አስቡ! ይህን ኃይለ ቃልም ታገኛላችሁ፦ «ጭፍሮችም ደግሞ፥ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ» እንደተባሉ ልብ በሉ!

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ይህ እውነተኛና የታመነ ቃል ነው የምነግራችሁ! በማንም ላይ ግፍ አለመሥራት፣ በማንም ላይ በሐሰት አለመመስከርና አለመክሰስ፣ በማንም ላይ ያልተገባ ጉቦና የተለየ ጥቅማ-ጥቅም አለመጠየቅ፣ በማንም ላይ በሥልጣንህ ተመክተህ ፍርድ አለማጓደል፣ በማንም ላይ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደህ ራስህንም ሌሎች ሠዎችንም በገንዘብ አለመደለል፤ ለሀገርህና ከአንተ አገልግሎት ለሚጠብቅህ ሕዝብ ታማኝ መሆንን አለመዘንጋት፤ በላብህ ዋጋ ሕይወትህን ማጣጣም እንዳለብህም ተረዳ፤ ግፍን፣ ተንኮል፣ ሸርን፣ አሻጥርን፣ ሤራን፣ ምቀኝነትን፣ ከሕይወትህ አስወግድ፤ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ የዋህነትን፣ መልካምነትን፣ ሠናይ ምግባርን፣ አርቆ አሳቢነትን፣ ልበ ሠፊነትን፣ ገርነትን፤ ገንዘብህ አድርግ።

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ከትንሹ እስከ ትልቁ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሕግ አውጪ እስከ ሕግ አርቃቂ፣ ከወታደር እስከ ባለሥልጣናት ድረስ፤ ከቀራጮች እስከ ጭፍሮች፣ አጠቃላይ ሕዝቡ ሁሉ ይሄ አማናዊ ቃል ለራሱ ገንዘብ ሊያደር ይገባል፤ ከላይ የተጠቀሱ እኒህን ነገሮች ስትፈፅሙ የመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ሕይወታችሁን በሐሴት ያረሰርሰዋል፤ እናንተም «ምን እናድርግብላችሁ ለጠየቃችሁት ጥያቄም እግዚአብሔር ምላሽ ይሄ ነው።

(ኃይለ ኢየሱስ ፲፯/፲፩/፳፻፰ /)

Saturday, April 30, 2016

የመስቀሉ ምስጢር፦

(እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!)

ድንቅ ሥነ ስዕል
ክርስቶስ ክርስትና ፋና ፈንጣቂ፤
ሃይማኖቴ ተዋሕዶ ነሽ እጅግ ድመቂ።

የሠማዕታት ተጋድሎ የጻድቃን ክብር፤
አንድም በምሳሌ አንድም በምስጢር፤
በፍቅር ሁነን በአንድነት እንድንመሰክር፤
ይሄ ነው ታላቁ የመስቀሉ ምስጢር።

ኃያሉ አምላክ ድንቅ መካር አማኑኤል የእኛ ጌታ፤
ድንግል ተወልዶ ዓለሙን ሁሉ በፍቅሩ የረታ።

ክርስቶስን የምንወድ ትዕዛዙን እንጠብቅ፤
ስለ ጻድቃን ስለ ሠማዕታት እንድንጠነቀቅ፤
ይልቅ ተጋድሏቸውን በአርምሞ እንድናደንቅ፤
ተናግሯል የእኛ ጌታ መስክረን እንድንመረቅ።

የዓለሙ በግ የመስቀሉ ምስጢር፤
ተቤዥቶ ወደደን ሰጠን ፍፁም ፍቅር፤

ድንግል ያን ጊዜ ያን ጊዜ ከአጠገቡ፤
ዐይኖቿ አረፈ ወደ ልጇ ጣምራ እያነቡ፤
ልቧ ተከፈለ በአምስቱ ኅዘናት ተመታ፤
ልጇ ወልደ አምላክ በስቃይ ሲንገላታ።

እንዴት ቻለቺው ያን የአንጀት መንሰፍሰፍ፤
የተንቢቱን ፍፃሜ የኅዘኗ ታላቅ ሠይፍ።

ጻድቅ ዮሴፍ ዕንባውን ረጨ ወደ አዶናይ፤
እጅግ ተደነቀ መልአከ ዑራኤል ከሠማይ፤
ወልድ ዋሕድ የፍቅሩ ጥጉ እንዲታይ፤
አፉን አልከፈተም በሸላቾቹ ስቃይ።

የመስቀሉ ምስጢር እንደተጻፈ ተፈፀመ፤
ተፈጥሮ ተናገረ ዓለም በፍቅሩ ተደመመ።

ስለ ሠውነቱ የሦስት ቀን ቀጠሮ፤
በአዲስ መቃብር አካሉ ተቀብሮ፤
ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን መዝብሮ፤
ሠላምን አውጀ ሰይጣንን አስሮ፤

በእባብ ገላ የገባው ዲያብሎስ ተሽሮ፤
ትንሣኤን አሳየን የሞት ሞትን ሽሮ፤
ለአዳም ልጆች ሠላምን ተናግሮ፤
እውነት ትመስክር ትናገር ተፈጥሮ።



(ማስታወሻነቱ፦ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያገለገሉና ለቤተክርስቲያን ብዙ መምህራንን ያፈሩ፣ በጣሊያን ሀገር በፊሬንዜ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ፅዋ ማሕበርን በማጠናከር ብዙ ለደከሙ ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዲያቆን አምሳሉ ተፈራ  ይሁንልኝ። /ኃይለ ኢየሱስ፤ ፳፪/፰/፳፻፰ ዓ/ም)

Wednesday, January 27, 2016

ይድረስ ለመንፈሳዊ መምህራኖቻችን (ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ)፦

       ውድ ወንድሞቻችንንና መምህራኖቻችን፥ ሠላምና ፍቅር በድንግል ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከመላው ቤተሰባችሁ ጋር ይብዛላችሁ።

አንድ ነገር ለማለት ፈልጌ ነበር፥ እርሱም፦ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ስለ መጠቀም> ጠቀሜታው ምንድን ነው? ጉዳቱስ እስከምን ያህል ነው? በሚል የግንዛቤ መስጫ ትምህርት እንዲሰጡን ከማሰብ የመነጨ ነው።

ምክንያቱም፦ እነ "ቀሲስ" ትዝታውና  እነ "ቀሲስ" መላኩ ሠሞኑን በፒያኖ (በኦርጋን) ስለመዘመር የሚያጣቅሱስ የዶክተር ኢሳያስና አለሜ ሥራዎችና አንዳንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር በፒያኖ (በኦርጋን) የዘመሩትን እንደነ ዘማሪ ኪነጥበብ፣ እንደነ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ፣ እንደዘመሩ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህ እውነት በዚያን ጊዜ በፒያኖ (በኦርጋን) የተዘመሩ ዝማሬዎች በነባራዊው ኹናቴ ነው ወይንስ ለቤተክርስቲያን የመዝሙር ማሳሪያ ተደርጎ ለመንፈሳዊ ልዕልና፣ ለመንፈሳዊ አርምሞ የሚሰጠው ጠቀሜታ ታምኖበት ነው ወይ?

ይህንን አርዕስት በዋቢነት የሚጠቀሙት እነ "ቀሲስ" መላኩ ቢኾኑም ከዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ በመነሳት ነው፤ ይህም ሃሳብቸው እንዲህ ይላል፦ <ይኽውም የተደከመበት አጭር መዝሙረ ጸሎት የዜማው ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ ተስማሚ መሆኑን ለመዝሙር አፍቃሪዎቼ አስገነዝባለሁ> (መዝሙረ ጸሎት ገፅ /9 ዶክተር ኢሳያስ አለሜ የፃፉት) ይላል እንጂ በንጉሡም ይሁን በጊዜው የነበረ ቅዱስ ሲኖዶስ፦ በፒያኖ (በኦርጋን) ስለ መዘመር ስለ ጥቅሙና ስለ ጎጂንቱን አይገልፅም፣ አያብራራም!

የኾነው ኾኖ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ  <የዜማው ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ምን ያህል በጥልቀት ተገንዝበውት ይሆን ወይ?

በእርግጥ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ በዚሁ በፒያኖ (በኦርጋን) የሚያቆሙ አይመስሉም፣ ምክንያቱ፦ <ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> ያሉትን የዶክተር ኢሳያስን ጽንሰ ሃሳብ> በመያዝ ዛሬ በፒያኖ (በኦርጋን)  የተጀመረ ነገ ይቀጥልና ድረም፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ትራምሬት፣ ጊታር፣ ቫዮሊን ወዘተ . . .  እያሉ ይቀጥላሉ።

ስለዚህ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ መሳሪያ> ስለ መጠቀም ስንነጋገር በሕዝብ ብዛትና በፐርሰንት ሳይኾን ለመንፈሳዊ አምልኮና ለመንፈሳዊ ዝማሬ አርምሞ (ተመስጦ) የቱ ነው ወደ መንፈሳዊ ልዕልና የሚመራን? መሠረታዊና ቀና መንፈሳዊ መንገድ የሚመራን የቱ ነው? በኦርጋን ወይንስ በክራር፣ በሳክስፎን ወይንስ በዋሽንት፣ ጃዝ ወይንስ ከበሮ፣ ቫዮሊን ወይስ ማሲንቆ፣ በኦርኬስትራ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚይዙት ዘንግ ወይንስ መንፈሳዊ አባቶቻችን ለምስጋና የሚይዙት መቋሚያ፤ የቱ ነው ለመንፈሳዊ ዝማሬና ለአርምሞ (ለተመስጦ) የሚኾነው?