(እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!)
ሃይማኖቴ ተዋሕዶ ነሽ እጅግ ድመቂ።
የሠማዕታት ተጋድሎ የጻድቃን ክብር፤
አንድም በምሳሌ አንድም በምስጢር፤
በፍቅር ሁነን በአንድነት እንድንመሰክር፤
ይሄ ነው ታላቁ የመስቀሉ ምስጢር።
ኃያሉ አምላክ ድንቅ መካር አማኑኤል የእኛ ጌታ፤
ከድንግል ተወልዶ ዓለሙን ሁሉ በፍቅሩ የረታ።
ክርስቶስን የምንወድ ትዕዛዙን እንጠብቅ፤
ስለ ጻድቃን ስለ ሠማዕታት እንድንጠነቀቅ፤
ይልቅ ተጋድሏቸውን በአርምሞ እንድናደንቅ፤
ተናግሯል የእኛ ጌታ መስክረን እንድንመረቅ።
የዓለሙ በግ የመስቀሉ ምስጢር፤
ተቤዥቶ ወደደን ሰጠን ፍፁም ፍቅር፤
ድንግል ያን ጊዜ ያን ጊዜ ከአጠገቡ፤
ዐይኖቿ አረፈ ወደ ልጇ ጣምራ እያነቡ፤
ልቧ ተከፈለ በአምስቱ ኅዘናት ተመታ፤
እንዴት ቻለቺው ያን የአንጀት መንሰፍሰፍ፤
የተንቢቱን ፍፃሜ የኅዘኗ ታላቅ ሠይፍ።
ጻድቅ ዮሴፍ ዕንባውን ረጨ ወደ አዶናይ፤
እጅግ ተደነቀ መልአከ ዑራኤል ከሠማይ፤
የወልድ ዋሕድ የፍቅሩ ጥጉ እንዲታይ፤
አፉን አልከፈተም በሸላቾቹ ስቃይ።
የመስቀሉ ምስጢር እንደተጻፈ ተፈፀመ፤
ተፈጥሮ ተናገረ ዓለም በፍቅሩ ተደመመ።
በአዲስ መቃብር አካሉ ተቀብሮ፤
ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን መዝብሮ፤
ሠላምን አውጀ ሰይጣንን አስሮ፤
በእባብ ገላ የገባው ዲያብሎስ ተሽሮ፤
ትንሣኤውን አሳየን የሞት ሞትን ሽሮ፤
ለአዳም ልጆች ሠላምን ተናግሮ፤
እውነት ትመስክር ትናገር ተፈጥሮ።
(ማስታወሻነቱ፦ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያገለገሉና ለቤተክርስቲያን ብዙ መምህራንን ያፈሩ፣ በጣሊያን ሀገር በፊሬንዜ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ፅዋ ማሕበርን በማጠናከር ብዙ ለደከሙ ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዲያቆን አምሳሉ ተፈራ ይሁንልኝ። /ኃይለ ኢየሱስ፤ ፳፪/፰/፳፻፰ ዓ/ም)
No comments:
Post a Comment