በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ሰዎችን ማክበር ትኩረታቸውን ለማግኘት ይረዳናል። እግዚአብሔርን የምናምንና ስላመነውም ምስክርነት የምንሰጥ ሰዎች ሁሉ ሁሉን ማክበር ይጠበቅብናል። ሽማግሌም ሆነ ወጣት፣ የታመመ ሆነ ጤነኛ፤ ድሃም ሆነ ባለጠጋ፤ የተማረም ሆነ ያልተማረ፤ ወንድም ሆነ ሴት፤ ጻድቅም ሆነ ኃጥእ ሁሉን ማክበር ይጠበቅብናል፡፡ እነዚህ ሰዎች አስቀድሞ የነበራቸው ልምድ ምንም ይሁን ምን፣ አመለካከታቸውና ሥነ ምግባራቸውም መልካምም ይሁን መጥፎ እንድናከብራቸው ይጠበቅብናል።
ሰዎችን የምናከብራቸው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፤ በቅድሚያ እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርአያው ስለ ፈጠራቸው እናከብራቸዋለን። ስናከብራቸውም ያከበርነው የተፈጠሩበትን የእግዚአብሔርን አምሳልና አርአያ መሆኑን ማወቅ ይጠበቅብናል። ሰዎችን የምናከብርበት ሁለተኛው ምክንያት እግዚአብሔር ልጁን ለሰው ዘር ሁሉ መሥዋዕት ይሆን ዘንድ ስለሰጠ ነው። ይህን የማዳን ሥራ እግዚአብሔር ከፈጸመላቸው ታላቅ መሥዋዕትነትም ከከፈለላቸው ታዲያ ቢያንስ ይህ የተደረገላቸውን ሰዎች ማክበር አይጠበቅብንም ይሆን? ሦስተኛው ሰው ምንም ያህል ክፋት ወይም መጥፎነት ቢኖርበትም በውስጡ ግን መልካምነት ስለሚገኝበት ሰውን ልናከብረው ይገባል።
ሰውን ማክበር በውስጣችን የሚገኘውን መልካምነት መቀስቀሻ መሣሪያ ነው፤ ይህም ሰው ክርክርንና ራሱን መከላከልን ትቶ ለነገሮች ጆሮ ሰጥቶ ለመስማት ያበቃዋል። ማክበር ሰውን ሳናስገድድና ሳናስጨንቅ ለመስማት የሚችልበት ነጻነት እንድንሰጠውና በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን ወደ ምሥራቹ ወንጌል ለመጥራት ይረዳናል፤ ጥሪያችንን ካስተላለፍን በኋላ የምሥራቹን ወንጌል መቀበልም ሆነ አለመቀበል ግን የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።
ክብር መስጠት ስንል የሰው የግል መብቱን ነፃነቱንና ምስጢሩንም ማክበርንም ያካትታል፤ ስለዚህ ምንም በቅርበት የምናውቃቸው እንኳ ብንሆን ሰዎችን ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ለማቅረብ የምናደርገው ጥረት የሚሳካው በግኑኝነታችን ወይም በንግግራችን ወቅት ክብር ሰጥተን በምንጓዘው መንገድ ርቀት ነው። ክብር መስጠት የሰውን ስሜት የሚጎዱ ቃላቶችን አለመጠቀምን ያካትታል። የሰዎችን ባሕል፣ እሴቶቻቸውን፣ የቀደመ ታሪካቸውን በአግባብ መረዳትና ማወቅ ክብራቸውን የሚጎዳ ስህተት ከመሥራት ይታደገናል። ይህም ማስተዋል የተሞላበት አካሄድ እግዚአብሔር በመንገዱ እንዲመራን ለመጠየቅና ለመጸለይ ይረዳናል፤ ምንም ብናውቅ ሰውን ሊያስቀይሙ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉና።