Saturday, May 25, 2013

የዶ/ር እጓለ ገብረ ዩሐንስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ደራሲ / እጓለ ገብረ ዩሐንስ ከጻፉት መፅሐፍ ስለ ሞራል ድቀት ብፁዓን ንጹሐነ ልበ ስለ ክርስቲያን ምግባር መሠረት በሚል ለንባብ ካበቁት የተወሰደ። 

      ሀገር፣ መንደር፣ ቤት ንብረቱን ትቶ ወደ ሩቅ የሄደ ሰው ባይተዋር ይባላል። ይህ ስያሜ በኑሮ አድራሻ መለወጥ ብቻ ምክንያቱን የሚያገኝ አይደለም።   የመንፈስ ባይተዋርነትም አለ። ሰው ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ ሳይዘዋወርም ለአዲስ አስተሳሰብ፣ ፈሊጥና የኑሮ መልክ ሊጋለጥ ይችላል። አንደኛው እስኪያይል ወይም ሁለቱም እስኪዋሐዱ ድረስ የወትሮው እና የአሁኑ በሕሊና ውስጥ የባላንጣዎች ተቃርኖ ይፈትራሉ።

       እንዲህ ያለ ሰውነት ሲታገል ይቆይና ሲሰለቸው፦ የቸልተኘነት፣ የግዴለሽነት ኢንዲፈረንቲዝም መንፈስ ይሰፍንበታል። ይህ በተለይ የሚገለጸው በሥነ ምግባር መስክ ነው። ሥለታም የነበረው ሥነ ምግባራዊ በሕሊናው ይሰንፋል። የሚመቹ፣ የማይቆረቁሩ፣ የማይጋጩ እንደ ዘዴኝነት፣ ጮሌነት፣ ብልሃተኝነት፤ ያሉ የማይጨበጡ የቀልጣፋ ሰውነት ጠባዮች ያይላል።አስመሳይ፣ አድር ባይ፣ እንደ እምነቱ የማያምን፣ እንደ ኑሮው የማይኖር፣ የሕሊናውን ብኵርና ለምስር ንፍሮ የለወጠሌላም ሌላም። እንደ አለንጋ የሚጋረፉ ተግሣጾች ወቅታዊነታቸውን የሚያገኙት በዚህ ሳቢያ ይመስለናል።የሞራል ድቀትየሚባለው ይህ ሳይሆን ይቀራል? የመነሳቱ፣ የመቆሙ፣ ከራሱ ጋር ተስማምቶ ሚዛን ጠበቆ የመራከመዱ፤ ነገርስ እንዴት ይሆን? ቅን ሕሊና የማያልፈው ጥያቄ ነው።
                           +++++++++++++++++              +++++++++++++++++

Tuesday, April 30, 2013

"ሰሙነ ሕማማት" በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ


         ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የምትጓዝ አካል አድርገው ሊገልጧት ይሞክራሉ፡፡ ይህ እጅግ አላዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኘና በሥጋዊና በደማዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት የላትም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ‹‹ከሕማማቱ በኋላ›› በማለት ስለ ሰሙነ ሕማማት የሚያወሳ ቃል ተጠቅሟል፡፡ (የሐዋ1.3)

            ሰሙነ ሕማማት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ ‹‹ሰሙን›› የሚለው ቃል ‹‹ሰመነ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስምንት ቀኖች ወይም ሳምንት ማለት ው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የሚለው ቃልም እንደዚሁ ‹‹ሐመመ›› ወይም ‹‹ሐመ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መከራዎች ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የምንለው ለብዙ ሲሆን ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ደግሞ ‹‹ሕማም›› እንላለን፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ቃላት በማናበብ ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ስንል ‹‹የመከራዎች ሳምንት›› ማለታችን ነው፡፡

Thursday, April 25, 2013

“ምስጢራዊው ቡድን”

 በመምህር ምሕረትተአብ አሰፋ (የደብረ መዊዕ ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ስብከተ ወንጌል ሐላፊ)

“በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” 1ኛ ጴጥ 3፥15
 

     በዚህ “ምስጢራዊው ቡድን” በተሰኘው ቪሲዲ ትምህርታችን የምንመለከተው በተዋህዶ ጓዳ በክርስትና ዓለም ምሽጋቸውን መሽገው በዲቁናና በቅስና እንዲሁም በምንኩስና ከተቻላቸውም በጵጵስና መሐረግ በየአብያተ ክርስቲያናቱና በየገዳማቱ ተደብቅው ከቆዩ በኃላ ውስጣችን አጥንተው ምስጢራችንን አየተው የስለላ ስራቸውን በማጠናከር ቀን ጠብቅው ጊዜ አመቻችተው እኛ ኮብልለናል እናንተም ኮብልሉ በማለት እንጀራችንን በልተው ተረከዛቸውን በኛ ላይ ስለሚያነሱብን ወገኖች ነው።

        ሃያ ሰባት ዓመት በክርስትናው ዓለም ቆይቻለሁ፥ ክርስትናንም ከእግር እስከ ራሱ መርምርያለሁ ነገር ግን የሚያሳምነኝ ነገር ለህሊናዬ አላገኘሁም በማለት፦ “ጉዞ ወደ ኢስላም” በሚል የኮበለለውን በእንጦንስና በመቃርስ ቆብ የቆመረውን የትላንቱን አባ ወ/ሥላሴ የዛሬው ኻሊድ ካሳሁንን ምስጢራዊ ተልዕኮ መርምረን ላነሳቸው ጥቄዎች መልስ የምንሰጥ ሲሆን በቀጣይነት ልክ እንደ ኻሊድ ካሳሁን “ብርሀናዊው ጎዳና” በማለት የክርስትናውን ዓለምና ክርስትናን በማጠልሸት ለኮበለለው ዳኢ ኻሊድ ክብሮም መልስ የምንሰጥ ይሆናል።

               ከሁሉ አስቀድመን ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ሠው የፈለገውንና የመረጠውን እንዲሁም ያመነበትን ማምለክ እንደሚችል ሕገ እግዚአብሔርም ሆነ ሕገ መንግስት በሚገባ ደንግገውታል። ነገር ግን ሠው ከራሱ አልፎ ሌላው ያዋጣኛል ብሎ ያመነበትን ማንቋሸሽና ማጠልሸት ተገቢ ነው ብለን አናምንም።

Friday, March 8, 2013

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል አንድ)

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 
የእቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር፦

1. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን አያከብሯትም፣ ምልጃም አይጠይቋትም፣ በዓላቶቿንም አያከብሩም፤ አንዳንድ ቡድኖች ጭራሽ ጫጩት ከተፈለፈለ ወዲያ ዋጋ በሌለው እንቁላል ቅርፊት ሊመስሏት ይወዳሉ። ፕሮቴስታንቶች እመቤታችንን ላለማክበር የሚያደርጉት ይህ ሁሉ ተቃውሞ ምናልባት ካቶሊኮች ለእርሷ ከሚሰጧት የተጋነነና ቅጥ ያጣ ክብር የመጣ ይመስለኛል።

2. አንዳንድ ፕሮቴስታንት አንጃዎች ጭራሹን ደፋር ከመሆናቸው የተነሳ እመቤታችንን “እህታችን ማርያም” ብለው ይጠሯታል።

3. በተጨማሪም ፕሮቴስታንቶች ጌታችንን ከወለደች በኋላ የዮሴፍ ሚስት ሆና ኖራለች፣ ለዮሴፍ “የኢየሱስ ወንድሞች” ወይም “የጌታ ወንድሞች” በመባል የሚታወቁ ልጆችን ወልዳለታለች ይላሉ።

4. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን እንዳያከብሩ ደረጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው “ጸጋን የተሞላሽ” የሚለውን የመላኩን ቃል “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” በሚለው ሐረግ በመለወጣቸው ነው ።

5. ፕሮቴስታንቶች እመቤታችን በ1980 ዓ/ም አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው “አንቺ ጸጋን የተሞላብሽ ሰላም ላንቺ ይሁን እግዚአበሔር ከአንቺ ጋር ነው” ካለ በኋላ በቅንፍ ውስጥ “(አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ)” ብለው ፅፈዋል።

Wednesday, February 6, 2013

ክርስቶስ ለእኛ ኦርቶዶክሳዊያን ማን ነው?



እርሱ የእግዚአብሔር በግ ነው፤ እርሱም መሥዋዕት ነው።

እርሱ ስለብዙዎች ኃጢአት የተሠዋው ፍሪዳ ነው፤ እርሱ መሥዋዕቱን የሚያቀርብ ሊቀ ካህናት ነው፤መሥዋት ተቀባዩም እርሱ ነው።

ስለእኛ መከራን የተቀበለው እርሱ ነው፤ ስለእኛም የራራልን እርሱ ነው።

እርሱ ሙሽራ ነው፤ እርሱ ራሱ ሙሽሪትም ነው። (ከእናታችን የነሣው ሥጋ ለጌታችን እንደሙሽሪት ነው። ይህ ሥጋ ግን አምላክ በመሆኑ ሙሽራ ሆነ፤ በሐዋርያትም እኛ ለእርሱ ታጨን። ስለዚህም እርሱ ሙሽራ ነው፤ እርሱ ራሱ ሙሽሪት ነው አልን)

እርሱ  የሰርጉ ቤት ነው፤ እርሱ ራሱ  የሰርግ ቤቱ አሳላፊ ነው።

Sunday, January 27, 2013

“ቁጣንና ሌሎችንም አስመልክቶ የቅዱስ ኤፍሬም ተግሣጽ”


      "አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ" አለህ። ነፍስህም የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት። እናም ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር በመኖር የእግዚአብሔር አርዓያ የሆነችውን ነፍስህን አክብራት። በምትኖርባቸው ዘመኖችህ ሁሉ በተቻለህ መጠን ሰውነትህን ከቁጣ ጠብቅ። ያለበለዚያ አንተን ወደ ሲኦል ታወርድሃለች፤ ጎዳናዎቿም ወደ ገሃነም የሚያመሩ ናቸው። እናም ቁጣን በልብህ አታኑራት መራርነትንም በነፍስህ አታሳድር በነፍሰህ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህምና ነፍስህን መልካም በማድረግ ጠብቃት

 

አንተ በእግዚአብሔር ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል በክርስቶስ ሕማምም ድነኀል፤ አንተ በፈንታህ ለኃጢአት ሥራዎች የሞትክ ትሆን ዘንድ ስለአንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፋበት መታገሡ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሣቸው አርአያ ሊሆንህ ነው መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው በጅራፍ ተገርፎ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለጽድቅ ስትል መከራን እንዳትሰቀቅ ነው

   ስለእውነት አንተ የእርሱ አገልጋይ ባሪያው ከሆንክ ቅዱስ የሆነውን ጌታህን ፍራው ስለእውነት አንተ የእርሱ እውነተኛ ደቀመዝሙር ከሆንክ የመምህርን ፈለግ ተከተል የክርስቶስ ወዳጅ ትባል ዘንድ ባልንጀራህ በአንተ ላይ ቢሳለቅ ታገሠው ከመድኃኒዓለም የተለየህ እንዳትሆን በሰው ላይ ቁጣህን አትግለጥ

Sunday, January 20, 2013

ስለ ቅዱሳን አበው አጥንት /አፅም/ ስናወራ ይህን እናስብ!

ስለ ቅዱሳን አበው አጥንት /አፅም/ ስናወራ በሁለት መንገድ እንመልከት፦ ይኸውም አንደኛው የግያዝ ዓይኖች (በዚህ ዓይን መንፈሳዊውን ነገር ለመረዳት ስለሚከብድ ባናይበትና ባንመለከትበት እመርጣለሁ) ይህ የግያዝ ዓይን ስጋዊ ደማዊ ብቻ ነው የሚመለከተውና።

ሁለተኛው ደግሞ የኤልሳዕ ዓይኖች፥ ክርስቲያን እንደ መሆናችን መጠን በኤልሳዕ ዓይኖች ስናይ የራቀው ቀርቦ የተሰወረው ተገልጦ በእዝነ ህሊና በዓይናችን ስናይ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድና አሳብ የተጋደሉ የቅዱ አበው አጥንት /አጽም/ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለንን ዘጠኝ የሚያህሉ እውነታዎችን በደንብ እንረዳበታለን! ይኽውም፦