"አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ" አለህ። ነፍስህም የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት። እናም ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር በመኖር የእግዚአብሔር አርዓያ የሆነችውን ነፍስህን አክብራት። በምትኖርባቸው ዘመኖችህ ሁሉ በተቻለህ መጠን ሰውነትህን ከቁጣ ጠብቅ። ያለበለዚያ አንተን ወደ ሲኦል ታወርድሃለች፤ ጎዳናዎቿም ወደ ገሃነም የሚያመሩ ናቸው። እናም ቁጣን በልብህ አታኑራት። መራርነትንም በነፍስህ አታሳድር። በነፍሰህ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህምና ነፍስህን መልካም በማድረግ ጠብቃት።
አንተ በእግዚአብሔር ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል። በክርስቶስ ሕማምም ድነኀል፤ አንተ በፈንታህ ለኃጢአት ሥራዎች የሞትክ ትሆን ዘንድ ስለአንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል። አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፋበት መታገሡ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሣቸው አርአያ ሊሆንህ ነው። መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው። በጅራፍ ተገርፎ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለጽድቅ ስትል መከራን እንዳትሰቀቅ ነው።
ስለእውነት አንተ የእርሱ አገልጋይ ባሪያው ከሆንክ ቅዱስ የሆነውን ጌታህን ፍራው። ስለእውነት አንተ የእርሱ እውነተኛ ደቀመዝሙር ከሆንክ የመምህርን ፈለግ ተከተል። የክርስቶስ ወዳጅ ትባል ዘንድ ባልንጀራህ በአንተ ላይ ቢሳለቅ ታገሠው። ከመድኃኒዓለም የተለየህ እንዳትሆን በሰው ላይ ቁጣህን አትግለጥ።