ፈላስፋው ህርቃን፦ ያዘዘው ትዕዛዝ የመከረው
ምክር ይህ ነው።
ልጄ ሆይ፦
የምነግርህን ቃሌን ስማ ልዑል ክቡር የሚሆን እግዚአብሔርን እንድታስታውሰው ምክሬን ተቀበል።
ልጄ ሆይ፦
ነገርን (ምስጢርን) የሰማህ እንደሆነ በልብህ ውስጥ ሰውረው ለሌላ አትግለጠው። ተመልሶ የእሳት ፍም ሆኖ አንደበትህንና
ኣካላትህን ሁሉ እንዳያቃጥልህ። በዚያው ላይ እገሌ ምስጢር አይቋጥርም አሰኝቶ ስድብንና ውርደትን ያስከትልብሃል።
ልጄ ሆይ፦
ዓይንህ ያየውን ሁሉ አትሳብ (አታንሣ)፣ ታስሮ ያገኘኸውን አትፍታ፣ ተፈትቶ ያገኘኸውን አትሰር፣ ተከድኖ ያገኘኸውን አትክፈት፤
ተከፍቶ የቆየህን አትክደን።
ልጄ ሆይ፦ በሰው
ዘንድ የተመስገንህ፥ በእግዚአበሔር ዘንድ የተወደድህ ትሆን ዘንድ ለሁሉ ጠባይህን አሳምር፥ አነጋገርህን አርም። ውሻ ጅራቱን
መቁላቱን እንጀራን ያሰጠዋል፥ አፉን ማላቀቁ ግን በዱላ መመታትንና በድንጊያ መደብደብን ያመጣበታል።
ልጄ ሆይ፦
ለመስማት ፍጠን ለመናገር ለመናገር ግን አትቸኩል።
“ፈጥነህ ስማ
ቃልን ለመመለስ ግን የታገሥህ ሁን።” ሲራክ 5፥ 11
“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን።” ያዕ 1፥19
ልጄ ሆይ፦ የሰው
ዓይኑ ባለማቋረጥ እንደሚመነጭ እንደ ውኃ ምንጭ ገንዘብን ቢያይ ቢያይ አይጠግብም፥ ወደ መሬትም ካልገባ በስተቀር ገንዘብን
ለማግኘትና ለመሰብሰብ ሲል እረፍት የለውም።
ልጄ ሆይ፦ መልከ
መልካምና ቆንጆ ሴት ጥሩ ጥሩ ልብስን ተሸላልማና መልካሙን ጌጣጌጥ አድርጋ ብታያት ልብህ ወደ እርሷ አያዘንብል። ከህፃንነትህ
ጀምረህ ያከማቸኸውን ገንዘብ ሁሉ ብትሰጣት እንኳ ኃጢአትን መፈጸምና እግዚአብሔርን ማሳዘን ነው እንጂ (ኃጢአትን ከመፈጸም፥
እግዚአብሔርን ከማሳዘን በቀር) ከሚስትህ ጋር ካለው የበለጠ አታገኝባትም።
(አንዲት ሴት
ባሏ ከሌሎች ሴቶች እያመነዘረ ቢያስቸግራት ከዕለታት አንድ ቀን ምሳውን በሚበላበት ሰዓት እንዱን ወጭት የዶሮ ወጥ አልባሌ
ግምጃ አልብሳ አንዱን ወጭት የተልባ ወጥ አስይዛ ጥሩ ወስከምብያ ከድና ሁለቱን አቀረበችለትና የቱን ላውጣልዎ ብትለው ባለ
ግምጃውን መረጠ። ብትከፍተው ተልባ ሆነና ኸረግ! ቢከፍቱት ተልባ! አለ። እንደገና ሁለተኛውን ወጭት ክፈችው አላትና ብትከፍተው
መልካም የዶሮ ወጥ ሆኖ አገኘው። ምክንያቱን ቢጠይቃት፥ አንዲት ሴት ተርታውን ልብስ ብትለብስ፥ ሌላይቱ ሴት ጥሩውን ልብስ ብትለብስ፥
ልብሱ ተለያየ እንጂ ሴትነታቸው አልተለያይም ብላ ስላስረዳችው ከዚያ በኋላ ሚስቱን ትቶ ወደ ሌላ መሄዱን አቋረጠ ይባላል) ።
ልጄ ሆይ፦ አነጋገርህን
ጠብቅ፣ ራስህን ዝቅ ዝቅ አድርግ፣ አረማመድህ በዝግታ ይሁን። ማየትህ ወደ ታች ይሁን እንጂ ወደ ላይ አይሁን ማለት ካንተ
በታች ያለውን እይ እንጂ ካንተ በላይ ያለውን አትይ።
ልጄ ሆይ፦
ጭቅጭቅ ካለበት ቦታ አትቀመጥ። ጭቅጭቅ፥ ጸብንና ክርክርን ያወርሳልና። ጸብና ክርክርም ቂም በቀልን አውርሶ ከመገዳደል
ያደርሳልና።
“የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት፥ የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።” ምሳ 15፥ 17
ልጄ ሆይ፦
ድምፅን ከፍ አድርጎ በመጮኸ ቤት የሚሰራ ቢሆን አህያ በቀን በቀኑ ሁለት ሁለት ቤት በሠራ ነበር።
ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። 1ኛ ዮሐ 3፥ 18 (የአፍ ዘመድ ከገበያም አይገድ)
እንዲሉ።
ልጄ ሆይ፦ በጽኑ
ኃይል ካልሆነ ጠላቶችን መያዝ (ማሸነፍ) የሚቻል ቢሆን ኖሮ ትንሽ ሕፃን ልጅ ግመሎችን መምራት በቻለ ነበር።
ልጄ ሆይ፦
ከሰነፍ ባለጌ ሰው ጋር ጠጅ ከመጠጣት፥ ከአዋቂ ሰው ጋር ደንጊያ መሸከም ይሻላል። ልጄ ሆይ ጫማ በእግርህ ሳለ በእሾህ ላይ
ተራመድ ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ መንገድ ጥረግላቸው። (ጊዜ ሳለህ ጊዜን አትጠብቅ)።
(እኛ
የምንሠራውን የሚከተሉን ትውልድ እንዲቀጥሉት ነውና፥ እኛ ካለፍን በኋላ እንዳይቸገሩ መንገድ ልንጠርግላቸው ይገባናል።)
ብ/ጀ/ዓ/አበበ
.............................................................
ይቀጥላል
..................................................................
ዋቢ መፅሐፍ:- አንገረ ፈላስፋ (የፈላስፋዎች አነጋገር) በሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ
No comments:
Post a Comment