እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ አድሮ መንፈሳዊውን ቃል የሚያናግረን፣ መልካም የሆኑትን
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ሐሳብና እንድንማማር የሚያደርገን እርሱ ባለቤቱ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘመነ ልቦና እስከ ኦሪት ድረስ ስለ ድንግልና በሰፊው ከሚያትቱልን
ዓበይት ክፍል አንዱ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ ነው። ስለ ርብቃ፥ ድንግልዋን ጠብቃ ስለመኖሮ፦ "ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች" ይላል። /ዘፍ ፳፮፥፲፬/
እንዲሁም፥ ስለ ዮፍታሄ ልጅ ስለ ድንግሊቱ፤ /መሣ ፲፩፥፴-፵/ በአጠቃላይ ስለ ድንግልና ጠበቆ መገኘትና ድንግልና ጠበቆ
አለመገኘት፤ በእግዚአብሔር ዘንድና በእስራኤላውያን እምነትና ሃይማኖት አንፃር ምን ያህል ትልቅ ሥፍራ እንዳለው ሊቀ ነቢያት
ሙሴ በዘ ዳግም ምዕራፍ ፳፪ ከቁጥር ፲፫-፳፰ መመልከት፤ ማንበብና ማገናዘብ ብልህነት ነው እግዚአብሔር በነቢያት አንደበት
አድሮ ትንቢቱንና የእግዚአብሔር ልጆች በሕይወታቸው ምን መምሰል እንዳለባቸው በተለያየ ጊዜያት ተናግሯል። በሐዲስ ኪዳንም፥ ስለ
ድንግል ማርያምም በነቢየ ኢሳያስ ቀን አስቆጥሮ፣ ትንቢት ተናግር፦ "ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።" /ኢሳ ፯፥፲፬/ ተብሎ የተተነበየው ትንቢት ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ "እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር
ከእኛ ጋር የሚል ነው።" /ማቴ ፩፥፳፫፤ ሉቃ ፩፥፳፯/
ለማጠየቅም፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፤ ወደ ገላትያ በላከላቸው ክታቡ ላይ፦ "ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ" በማለት፤ "ሴት" ብሎ ስለ እናቱ ድንግሊቷ ድንግል ማርያም፣ "የተወለደውን ልጁን" ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገልፃቸዋል።
ሌላውና ዋናው ርዕሰ-ጉዳዬ
"የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ
ድረስ አላወቃትም" /ማቴ ፩፥፳፭/ የሚለው ሐረፍተ ነገር (ቃል) ነው። እራሳቸው ስተው ሌላውን ለማሳት ደፋ ቀና የሚሉ ሠዎች፦ ይህንንም አሳባቸውን እንዲያጠናክርላቸው "አዳምም
ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች።" እና "ቃየንም ሚስቱን አወቀ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም
ወለደች።" /ዘፍ ፬፥፩ እና ፲፯/ በማለት ታላቅ የሆነ የስህተተ ስህተት፤ የጥፋት ጥፋት እየሠሩ ይገኛሉ። በመቀጠልም
የልባቸውን ምኞት ለማሳካት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በማለት፦ "እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" ካለ ከወለደች በኋላ አወቃት ማለት ነው፤ በማለት የተዛባ ትርጓሜ ያክሉበታል፤
እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን!።