፩፡- የትዳር ጓደኛን ማን ይምረጥልን?
የትዳር ጓደኛ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ባለጸጋ ፥ወይም ባለሥልጣን፥ ወይም ቆንጆ፥ ወይም ጤነኛ፥ ስለሆኑ ብቻ የሚሹት አይደለም። ደሀ፥ ወይም ተርታ ሰው፥ ወይም መልከ
ጥፉ፥ ወይም በሽተኛ ፥ቢሆኑም የሚፈለግ የሚናፈቅ ነው። ሳያገቡ ለመኖር የወሰኑትም ቢሆኑ ፥ፍላጎቱ ያለው በአፍአ ሳይሆን
በውስጥ ስለሆነ፥ ከኅሊና ውጣ ውረድ ሊድኑ አይችሉም። ስለሆነም ከኅሊናቸውና ከፍላጎታቸው ጋር እየታገሉ በገድል ይኖራሉ። በዚህ
ትግል ማሸነፍም መሸነፍም ሊኖር ይችላል። የትዳር ጓደኛ ከውጭ ወደ ውስጥ የምናስገባው ሳይሆን፥ ከውስጣችን ፈልገን የምናገኘው
ነው። ይህም ማለት፡- በአዳምና ሔዋን ሕይወት እንዳየነው፡- እግዚአብሔር የትዳር ጓደኞቻችንን አስቀድሞ በእያንዳንዳችን ሕይወት
ውስጥ አስቀምጧቸዋል። በመሆኑም አንድ ሰው ሥዕል (ፎቶ ግራፍ) ይዞ የሥዕሉን ባለቤት እንደሚፈልግ በውስጣችን የተቀመጠውን፥
የተሣለውን ይዘን መፈለግ ይገባል።
የሰው ልጅ በእምነቱም ሆነ በሌላው ነገር ሁሉ ፍጹምነት ስለሌለው በፍለጋው
(በመንገዱ) አጋዥ ያስፈልገዋል። ያንንም የሚሰጠን ያለ ጥርጥር እግዚአብሔር ነው። ለዚሀም የጾምና የጸሎት ሰው መሆን
ያስፈልጋል። የነቢያት አለቃ ሙሴ ጽላቱን ከእግዚአብሰሔር እጅ የተቀበለው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ነው፥ እንጀራ
አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ዘጸ ፴፩፥፲፰። እኛም እንደ ጽላት እንደ ታቦት ተከብረው የሚያስከብሩ የትዳር ጓደኞቻችንን በጾምና
በጸሎት ልናገኛቸው እንችላለን ብለን ልናምን ይገባል። በአገራችን፡-«አቶ እገሌ እኮ ታቦት ማለት ናቸው፥ ወ/ሮ እገሊት እኮ ታቦት ማለት ናቸው፤» የሚባሉ
ነበሩ። ታቦት የሚያሰኛቸው የጸና ሃይማኖታቸው፥ የቀና ምግባራቸው ነበረ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ኢተአምሩኑ ከመ ታቦቱ
ለእግዚአብሔር አንትሙ፥ ወመንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌክሙ። እናንተስ የእግዚአብሔር ታቦት (ማደሪያ) እንደሆናችሁ፥ መንፈስ
ቅዱስም አድሮባችሁ እንዳለ፥ እንደሚኖርም አታውቁምን? (አታስተውሉምን፥ ልብ አትሉምን)?» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛቆሮ ፫፥፲፮።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ጽላቱን ለመቀበል እስከ ደብረ ሲና ተጉዟል፥ አቀበቱን (ተራራውን) ወጥቷል። እግዚአብሔር የሚያሳየውን ሁሉ
በትእግሥት ተመልክቷል፥ የሚነግረውንም ሁሉ በትእግሥት አድምጧል፥ የሰጠውንም በጸጋ ተቀብሏል። እኛም የምንሻውን ለማግኘት እስከ
ቤተክርስቲያን በእግረ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በእግረ ልቡና ጭምር መጓዝ አለብን። (ንስሐ መግባት፥ ሥጋ ወደሙ መቀበል፥ ዘወትር ማስቀደስ፥
ቃለ እግዚአብሔርን ማድመጥ ይጠበቅብናል)። ይኸንን ሁሉ ለማድረግ አቀበት ቢሆንብንም ከራሳችን ጋር ታግለን ማሸነፍ፥ ለነገሮች
ሁሉ ትእግሥተኛ መሆን ይኖርብናል።
፩፥፩፡- የትዳር ጓደኛችንን ራሳችን
መምረጥ አለብን፤
ልካችንን የምናውቀው ከማንም በላይ ራሳችን ነን። ራሳችንን ካልዋሸነው በስተቀር
ለዓይናችን የሚሞላውን፥ የልባችንን ሚዛን የሚደፋውን፥ በልካችን የተሰፋውን ልብስ እናውቀዋለን። በመሆኑም ጊዜው ሲደርስ በጣም
ሳንቸኩል፥ እጅግም ሳንዘገይ፥ እግዚአብሔር እንዳመለከተን ልንመርጥ ይገባል። ምክንያቱም መቸኰልም፥ መዘግየትም በየራሳቸው ችግር
አለባቸውና ነው። ቸኩለውም ዘግይተወም የሚቸገሩና የሚጨነቁ፥ የሚበሳጩና የሚያማርሩ፥ ተስፋ ቆርጠውም እግዚአብሔር ትቶኛል፥
ረስቶኛል፥ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። በአገራችን፡- «የቸኰለ አፍሶ ለቀመ፥ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል፥ የነቶሎ ቶሎ ቤት
ዳርዳሩ ሰንበሌጥ፤» የሚሉ ሥነ ቃላት አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፡- እንኳን ለግብር ለነቢብ (ለመናገር) እንኳ መቸኰል እንደማይገባ
ይመሰክራል። «ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ (ረጋ-ያለ)፥ ለቁጣም
የዘገየ ይሁን፤»ብሏል። ያዕ ፩፥፲፱። ይኸንን በተመለከተ፡- «የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል፤» የሚል ሥነ ቃል አለ። እንዲህም
ሲባል በጣም መዘግየት ይገባል ማለት አይደለም። ምክንያቱም፦
ለበጎ ነገር ሲሆን ሰይጣን ሰውን ሆን ብሎ የሚያዘገይበት ጊዜ አለና። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ፡- የኤማሁስን መንገደኞች፡- «እናንት የማታስተውሉ፥ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤» በማለት
ወቅሷቸዋል። መውቀስ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ የተጻፈውን፡- ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት ትንቢት እየጠቀሰ ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ
፳፬፥፳፭። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ሰይጣን አዘገየኝ፤» ያለበት ጊዜ አለ።
እንግዲህ በጣም ሳንቸኵል፥ በጣምም ሳንዘገይ፡- የትዳር
ጓደኛችንን እንምረጥ ስንል፡- «ስለ እኔ ማንም አያገባውም፤» በሚል መንፈስ፥ በራችንን ጥርቅም አድርገን ዘግተን አይደለም።
የተዘጋ ቤት ንጹሕ አየር እንደልብ ስለማይገባው ይታፈናል። በዚህን ጊዜ ለመተንፈስ ያስቸግራል፥ ለአስምና ለተመሳሳይ በሽታዎችም
ስለሚያጋልጥ ጤና ይታወካል። ለብቻው አእምሮውን ዘግቶ የሚያስብም ሰው እንዲሁ ነው። ስለዚህ አሳባችንን የምናጋራው፥
ጭንቀታችንን የምናካፍለው ሰው ያስፈልገናል። ቅዱስ ዳዊት፡- «ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር፥ ምክር ሠናይት ለኵሉ
ዘይገብራ። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት።» ያለው ለዚህ ነውና። መዝ
፻፲፥፲።