፩፦
መጠናናት፤
ምንም እንኳን የሰው ልጅ ተጠንቶ የማያልቅ ሳይንስ ቢሆንም ፦ ወደ ትዳር ዓለም ከመግባት በፊት
፦እንደ ሰው፥ በሰው አቅም መጠናናት እንደሚያስፈልግ ለማንም ግልጥ ነው። ይኸውም በሰከነ ልቡና ፥ በተረጋጋ መንፈስ ሊሆን
ይገባል። በትውውቅ ሰሞን የተሸፈነ ብዙ ነገር ፥ በሂደት ቀስ እያለ ብቅ ማለቱ ስለማይቀር ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። ሰውን
የምናጠናው ድካም የሌለበት ፍጹም የሆነ ሰው ለማግኘት አይደለም። ምክንያቱም እኛም ፍጹም አይደለንምና ነው ፥ አንድም በዓለመ
ሥጋ ፍጹም ሰው አይገኝምና ነው። በመሆኑም፦ በእኛ ዘንድ ድካም እንዳለ ሁሉ ፦ በሌላም በኲል ድካም ሊኖር እንደሚችል አምነን
ኅሊናችንን ልናዘጋጀው ይገባል። ከዚ ህ በኋላ ድካሙን ፦ በአራት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን። ፩ኛ፦ በቶሎ የሚወገድ
ድካም ፤ ፪ኛ ፦ በሂደት የሚወገድ ድካም፤ ፫ኛ፦ ልንሸከመው የሚገባን ድካም፤ ፬ኛ ፦ የማይወገድ ድካም፤
፩፥፩፦
በቶሎ የሚወገድ ድካም፤
የሰው ልጅ በትምህርት ፥ በምክርና በተግሣጽ ፦ ከጥፋቱ ሊመለስ ፥ ከድካሙም ሊበረታ ይችላል።
ስለሆነም ያሉትን ደካማ ጐኖች ዘርዝሮ በማውጣት ፦ እርስ በርስ መነጋገር ፥ መማማር ያስፈልጋል። ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ
ወደ ካህኑ በማምጣት ማስ መከር ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ድካም ፦ ከእውቀት ማነስ፥ ከመካሪ ማጣት ፥ አርአያ የሚሆን ሰው
ካለማግኘት በመሆኑ በቶሎ ይወ ገዳል። ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ምክር በሰው ልቡና እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን
ይቀዳዋል።» እንዳለ፦ አእምሮ ያላቸው የሚያስተውሉ ሰዎች ይስተካከሉበታል። ምሳ ፳፥፭። «ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን
ይወድዳል፤» እንዲል፦ በሁሉ ይገሠጻሉ። ምሳ ፲፪፥፩። «የተማረ ልጅ ብልህ ይሆናል፤» እንዲል፦ ልባሞች ፥ አስተዋዮች እየሆኑ
ይሄዳሉ። ምሳ ፲፥፭። ይህም ከምድራዊ ሀብት የሚበልጥ ሀብት ነው። ምክንያቱም « ከብር ይልቅ ትምህርትን ፥ ከተፈተነ ወርቅም
ይልቅ ዕውቀትን ተቀበሉ ፤ » ይላልና። ምሳ ፰፥፲። «ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፤» የሚልም አለ። ምሳ
፮፥፳፫።
፩፥፪፦
በሂደት የሚወገድ ድካም፤
በሰው ልጅ ሕይወት ፦ በአንድ ጀንበር ወይም በአጭር ጊዜ የማይወገድ የሥጋ ድካም አለ። አብሮ
የኖረ ጠባይ እጅግ አስ ቸጋሪ ስለሆነ፦ በሂደት የሚወገድበትን መንገድ በመፈለግ በትዕግስት መጓዝን ይጠይቃል። የየዕለቱን
ለውጥም መከታተል ያስፈልጋል። ዋናው ነገር ችግሩን አምኖ መቀበል ነው። እኛም በምክርና በትምህርት ድካማችንን ለማስወገድ ፥
ሕይወታችንን ለመለወጥ የሚታ ገሉትን ልናግዛቸው ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ ጾምና ጸሎትንም ይጠይቃል። መካሪው ክፍል «ፈጣሪ ሆይ
ይህን ሰው እርዳው፤ » እያለ ፥ ድካም ያለበትም ሰው፦ « ፈጣሪዬ ሆይ፥ እርዳኝ፤ » እያለ ፦ ሊጾሙ ሊጸልዩ ይገባል። ጌታ
በወንጌል፦ እንደተናገረ፦ ካልጾሙና ካልጸ ለዩ በስተቀር የማይለቅ ክፉ መንፈስ ፥ ክፉ ጠባይ አለና። ማቴ ፲፯፥፳፩።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ወደ ቤተ ሳይዳ በደረሰ ጊዜ፦ አንድ ማየት
የተሳነው ሰው ወደ እርሱ አመጡ ፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። ጌታም ያን ሰው እጁን ይዞ ከመንደር ካወጣው በኋላ፦ በዓይኑ ላይ
እንትፍ ብሎ ዳሰሰውና፦ «ምን ታያለህ?» አለው። ያም ሰው በአንድ ጊዜ መዳሰስ አጥርቶ ማየት ባለመቻሉ፦ «ሰዎችን እንደ ዛፎች
ወዲያና ወዲህ ሲመላለሱ አያለሁ፤» አለ። ጌታም ዳግመኛ ዳሰሰውና አጥርቶ እንዲያይ ፥ ፈጽሞም እንዲድን አደረገው። ዓይኖቹ
ብሩህ ሆነውለት ሁሉንም ለመመልከት ችሏል። ልክ እንደዚህ በዕደ ምክር ደግሞ ደጋግሞ መዳሰስ የሚገባው ሕይወት አለ። በሂደትም
እየጠራ ፥ እየተስተካከለ ይሄዳል።
፩፥፫፦
ልንሸከመው የሚገባን ድካም፤
ከትዳር ዓላማዎች አንዱ መረዳዳት ስለሆነ፦ በማናቸውም ሰዎች ዘንድ የማይጠፉ ድካሞች ይኖራሉ።
መልካቸውና ባህር ያቸው ይለያይ እንጂ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ የሚንጸባረቁ ናቸው። ከታገሧቸውም ለክፋት የማይሰጡ ናቸው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳው ሎስ፦ «እኛም ኃይለኞች (ብርቱዎች) የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ
ይገባናል። እያንዳንዳችን እንድናጸናው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና።» እንዳለው፦ ሆነን ልንገኝ ይገባል። ሮሜ ፲፭፥፩። በተሰሎንቄ መልእክቱም፦
«ለደካሞች ትጉላቸው፤» ብሏል። ፩ኛ ተሰ ፭፥፲፬። ክርስትና፦ ማለት ክርስቶስን መምሰል ነውና። እርሱ ደዌያችንን እንደተቀበለ
፥ ሕመማችንንም እንደተሸከመ መርሳት አይገባንም። ኢሳ ፶፫፥፬። ምንም ነገር ቢደርስብን እርሱ ከተገረፋቸው ስድስት
ሺህ ስድስት መቶ ስልሣ ስድስት ግርፋቶች መካከል ከአንዲቷም ስለማይመጣጠን። ያን ማሰብ ነው።
አቅልለው ካዩት ሁሉ ነገር ቀላል ነው ፥ ካከበዱትም ሁሉ ነገር ከባድ ነው። የአብዛኞቻችን ችግር
ቁንጫ የምታክለውን ችግር ዝኆን አሳክሎ የማየት ችግር ነው። ብዙ ሰው ከተለያየ በኋላ ጸጸት ውስጥ የሚገባው ለዚህ ነው። ለያዥ
፥ ለገራዥ እንዳላስቸገረ ሁሉ ምን ሆኜ ነው ማለት ይጀምራል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የራስ ምታቱንና የጐን ውጋቱን ተሸክሞ ሲኖር የእግዚአብሔር ጸጋ በዛለት
እንጂ አልጐደለበትም። ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፯። ጢሞቴዎስም፦ የሆድ ሕመሙን ተሸክሞ ኖሯል። ፩ኛ ጢሞ ፭፥፳፫። ስለዚህ የምንሸከመው
ድካም ሕመም ሊኖረው ይችላል። ቢሆንም ዋጋ አለው ፥ ጸጋን ያበዛል። በሌላ በኲል ደግሞ ፦ እኛ የሌላውን ድካም ስንሸከም ፥
ሌላውም የእኛን ድካም እንደ ተሸከመልን ልንረሳ አይገባም።
፩፥፬
፦ የማይወገድ ድካም ፤
ብዙ ሰዎች ምንም ቢያደርጉን ልናስወግደው የማንችለው ድካም አለ።
እንዳንሸከመው ፥ እንዳይሸከሙልን ከአቅም በላይ ይሆናል። ለክፉም
አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ከሁሉ በላይ የሚያስቸግረው፦ ምን ቢመክሩን ፥ ቢያስተምሩንና ቢገሥጹን ፦ ድካማችንን አምነን ስለማንቀበል
በሕይወታችን አለመለወጣችን ነው። ድካማችን ችግር ውስጥ ከቶን ብናይም ዓይናችንን ጨፍነን ፥ ጆርአችንን ደፍነን ፥ ልባችንን
ዘግተን ፥ «የእኔ ድካም ያመጣው አይደለም፤» እንላለን። በቃል ምክርም ፥ በመከራም አንማርም። ይህም ታላቅ ስንፍና ነው።
ጠቢቡ ሰሎሞን ፦ «ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም፤» ብሏል። ምሳ
፳፯፥፳፪።
እንዲህ ዓይነቱን ድካም መሸከም ሰማዕትነትን ይጠይቃል። ስለሆነም፦ በጊዜያዊ ፍቅር ታውረን ችግር
ውስጥ ከመግባታችን በፊት አቅማችንን ማመዛዘን ይኖርብናል። «ሁልጊዜ የሚፈራ ሰው ምስጉን ነው፤ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ
ይወድቃል።» የተባለውን የሕይወት መመሪያ ማድረግ ይገባል። ምሳ ፳፰፥፲፬። ብቃቱ ስለሌለን መፍራታችን ተገቢ ነው። በግብዝነት
ገብተንበት ኋላ ከመማረር፦ «አልችለውም ፥አልወጣውም፤» ማለት
ልባምነት ነው። « የሚችለኝ ፥ የምትችለኝ አገኝ ይሆን? » ማለትም አሰተዋይነት ነው። እንዲህም ማለታችን፦ «ላይችል አይሰጥም
፥ሳይደግስ አይጣለም፤» ዓይነት ሰዎች ፈጽሞ የሉም ማለታችን አይደለም። እነዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ኃይልን በሚሰጠኝ
በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፤» እንዳለው ዓይነት ሰዎች ናቸው። ፊል ፬፥፲፫።
በመጠናናት ጊዜ ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥም የሚመለከት ዓይን ያስፈልጋል። ይኽንን ሊወገድ
የሚገባውን ነገር ግን ሊወገድ የማይችለውን ድካም ልሸከመው እችላለሁ? ማለት ብቻ ሳይሆን፥ እርሷስ የእኔን ድካም ልትሸከመው
ትችላለች ወይ? ማለት ይኖርብናል። በአፍላ ፍቅር ዘው ከማለታችን በፊት፦ እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ አርቀን ማሰብ አለብን።
ምክንያቱም ፦ በእፍ እፍ ሰሞን በጣም ከፍ ያለው የፍቅር ሙቀት ወደ ቦታው ሲመለስ ዓይን መገለጥ ፥ አእምሮ መከፈት ይጀምራል።
መጨረሻውም በጸጸት እሳት መቃጠል ፥ በጸጸት አለንጋ መገረፍ ይሆናል። ከችግሩም ይልቅ ጸጸቱ ይጐዳል።
አብዛኛውን ጊዜ ፦ ደጋው በረሃ ፥ በረሃውም ደጋ ላይሆን ፦ ልባችን እያወቀ ፦«ሊለወጥ ይችላል
፥ ልትለወጥ ትችላለች ፤» በሚል ተስፋ በግብዝነት እንገባበታለን። በኋላም በጭንጫ መሬት ላይ እንደወደቀ ዘር እንሆናለን።
«ሌላውም ብዙ መሬት (አፈር) በሌለበት በጭንጫ (በድንጋያማ) መሬት ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ ፥
ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ፤» ይላል። ማቴ ፲፫ ፥፭። ጭንጫ የተባለው የእኛ ሕይወት ነው።
ሕይወታችን ለጊዜው የትዳርን ዘር ያበቅል ይሆናል ፥ ነገር ግን ፈጥኖ መጠውለጉ አይቀርም።
እንግዲህ ወደ ትዳር ዓለም ከመግባታችን በፊት ልንሠራው የሚገባንን የክፍልም ሆነ የቤት ሥራ
በትክክል መሥራት አለብን። እንዲህም ስል መቶ በመቶ እናገኛለን ማለቴ አይደለም። ብዙ ስሕተት ፥ብዙ አረም እንዳይኖረው
አድርገን እንሥራ ማለቴ ነው። የደጋውን አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜም ሆነ ፥ እንደ ቅቤ የሚያቀልጠውን የበረሃ ሙቀት ለመከላከልም
፥ ለመታገሥም ወስነን መግባት አለብን። እዚህ እኛ የምንኖርበት አገር ክረምቱም በጋውም ከባድ ነው። በክረምት፦ ምድሩ ሁሉ
በበረዶ ስለሚከደን መኖሪያውም መጓጓዣውም ሰው ሰራሽ ማሞቂያ አለው ፥ ልብሱም ወፈርፈር ያለና ሙቀት የሚሰጥ ነው። በጋውም
ጨርቅ አስጥል ነው። በመሆኑም፦ ቤቱም መጓጓዣውም ማቀዝቀዣ አየር አለው። ይሁን እንጂ እንደተፈጥሮው አይሆንም። ሙቀቱም አየሩም
ጤና የማይሰጠውም ሰው አለ። ስለዚህ የመረጥነው ሰው ጠባይ በጣም ሲቀዘቅዝ የምናሞቅበት ፥ በጣም ሲግልም የምናበርድበት ልቡና
ስጠኝ ማለት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ፦ ችግሩን የምንታገስበት ልቡና ፥ ድካሙን የምንሸከምበት ትከሻ ማግኘቱ በራሱ ፦ ችግሩ
የተወገደ ፥ ድካሙም የቀለለ ያህል ነው። ብቻ ጥናታችን ራሳችንን በፍጹማን ወንበር ላይ አስቀምጠን እንዳይሆን አደራ።
በመጨረሻም ለማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ቢኖር፦ «የማይወገድ ድካም ፤» ማለቴ እንደ ሰው
የማይወገደውን እንጂ እንደ እግዚአብሔሩ አይደለም። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ። ሉቃ ፩፥፴፯። ከዚህም
በመቀጠል የምናየው በመጠናናት ጊዜ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነው ግልፅነት ነው።
፪፦
ግልጽነት፤
በመጠናናት ጊዜ ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገው ግልፅነት ነው። ስለሆነም፦ ነገ ትዳርን ከሚያስፈርስ
ችግር ውስጥ ከመውደቅ ዛሬ በግልፅነት መቀራረቡ ይበጃል። የአብዛኛው ሰው መቀራረብ ግን የድብብቆሽ ነው። ሁሉም ማንነቱን
ይደብቃል። ይህም፦ «ልትተወኝ ትችላለች ፥ ሊተወኝ ይችላል፤» ከሚል ስጋት ነው። ወይም ይህን ነገር ባንገፋበትና ብናቋርጠው ስሜን ታጠፋዋለች ፥ ስሜን
ያጠፋዋል ከሚል ፍራቻ ነው። ወይም ግብዝነት ሊሆን ይችላል። ይህም በሰው ሁሉ ፊት እንደ ጻድቃን ለመታየት የሚደረግ ጥረት
ነው። ጌታ በወንጌል፦ «በውጪያቸው አምረው የሚታዩ ፥ በውስጣቸው
ግን የሙታን አጥንትንና ርኲሰትን ሁሉ የተመሉ ፥ የተለሰኑ መቃብሮችን የምትመስሉ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ!
እንዲሁም እናንተም በውጭ ለሰው ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ዐመጽንና ግብዝነትን ፥ ቅሚያንም የተሞላችሁ ናችሁ። »
በማለት ፈሪሳውያንን የወቀሳቸው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፫፥፳፯።
ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊነት ካባ ስለምንሸፈን ብዙ ሰዎች ይታለላሉ። በስብከተ ወንጌል ጉባኤ ፥ በሰንበት
ት/ቤት ፥ በገዳማት ጉዞ ፥ በማኅበራት አገልግሎት ሲያዩን ፍጹማን እንመስላቸዋልን።የሚያዩን፦ ስንጾም ፥ስንጸልይ ፥ ስናስቀድስ
፥ ሱባዔ ስንገባ ነው። የተገባበዝነውን ሻይ ቡና የምንቀምሰው ፦ አቡነ ዘበሰማያት ደግመን ሳይሆን ፥ የዕለት ውዳሴ ማርያም
ወይም የዕለት ዳዊት ደግመን ነው። ነጠላ ከትከሻችን አይወርድም ፥ የሚለበሰው ቀሚስ የእግርን ጥፍር እንኳ የሚሸፍን ነው።
በነገር ሁሉ ዋሻ የዘጋ ፍጹም ባሕታዊ እንመስላለን። ከሠርግ በኋላ ግን ውስጣዊ ማንነታችን አግጥጦ ይወጣል። እንኳን በየዕለቱ
ኪዳን ልናደረስ ፦ በሰንበት እንኳ ማስቀደስ ያቅተናል።
የተገዛውም መዝገበ ጸሎት እንዳያቃዠን ለትራስ ብቻ ይሆናል። በመንፈስ ተጀምሮ በሥጋ ይደመደማል። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት
እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ . . . እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ?
በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁ?» ብሏል። ገላ ፫፥፩።
ስለዚህ ከመንፈሳዊ ሕይወታችንም አንፃር ያለብንን ድካም ለመሸፋፈን ከመታገል በግልፅ ተነጋግሮ
ድካሙን ለማስወገድ መታገል ይሻላል። ማንም ሰው ቢሆን ለትዳር ጓደኝነት ስለመረጠው ሰው የማያውቀው ነገር መኖር የለበትም።
ምክንያቱም ሰው መኖር ያለበት ከማያውቀው ሰው ጋር ሳይሆን ከሚያውቀው ጋር ነውና። ምናልባት የታሰበው ሳይሳካ ቀርቶ መለያየት
ቢመጣ ፦ አንዱ የአንዱን ስም ለማጥፋት ከመጣደፍ ፥ በመካከላቸው ያለውን ምሥጢር መጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታ መሆኑን ለአፍታም
መዘንጋት አያስፈልግም። አለበለዚያ በዚህ ጉዳይ አንዴ የቆሰለ ሰው እድሜ ልኩን ድብቅ ይሆናል። ድብቅነቱም ራሱንም ሌላውንም
ይጐዳል።
ግልጽነት የሚጐዳበት ጊዜም አለ። ምክንያቱም አንዳንድ ሰው ቀረብ ብሎ ሰውን ካጠና በኋላ ሥራውን
እንደጨረሰ ሰላይ እልም ድርግም ይላል። የሚጐዳው እልም ድርግም ማለቱ አይደለም። ነገር ግን የሰማውን አንዱን አሥር ፥ አሥሩን
መቶ አድርጎ ስለሚያወራ አእምሮን ይጐዳል። የእኛም ሰው በዓይኑ ከሚያየው እውነት ይልቅ በጆሮ የሰማውን ውሸት ስለሚያምን የሰው
ስም ይጠፋል። ስለዚህ ግልጽነት ትርጉም በማይሰጠው ዓለም በተወሰነ ደረጃም ቁጥብ መሆን ያስፈልጋል። ይህም እስከመጨረሻው
አይደለም። ወደ እርግጠኝነቱ ስናዘነብል ከቁጥብነቱ ወደ ግልፅነቱ
መሄድ ያስፈልጋል።
፫፦
መተጫጨት ፤
መተጫጨት የመጠናናት መጨረሻ ነው። አንድ ሰው አጨ ማለት ፦ ለማግባት ወሰነ ፥ መረጠ ፥ማለት
ነው። ማጨት ፦ ሴትን ልጅ መመኘት ፥ መፈለግ ፥መሻት ፥ ለሚስትነት ስጡኝ ማለት ነው። «ልጃገረድ ፦ አሥር ያጭሽ ፥አንድ
ያገባሽ ፤» እንዲል ፦ እሺ ካሰኙ በኋላ የጋብቻውን ውል ፦ ማሰር ፥ ማቆም ፥ ቃል ኪዳን መገባባት ፥ መፈጣጠም ማለት ነው።
የእጮኝነት ዘመን የዝግጅት ጊዜ ነው። ጎጆ ለመውጣት ፥ ራስን ለመቻል ፥አዲስ ሕይወት ለመጀመር
የሽግግር ወቅት ነው። በመጠናናት ጊዜ የሰው ልቡ መንታ ፥ አሳቡም ሁለት ነው፤ «ሊሳካም ፥ላይሳካም ይችላል፤» በሚል መናዋወጡ
፥ መጠራጠሩ አለ። ከታጨ በኋላ ግን፦ በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ ፦ ስለ ትዳር ብቻ ማሰብ ይጀመራል። አቅም በፈቀደ
የሚገቡበትን ጎጆ ፥ የሚገለገሉበትን ቊሳቊስ ያሰናዳሉ። በኅሊናም ይዘጋጃሉ።
መጠናናት
ለመተጫጨት ፥ መተጫጨት ደግሞ ለመጋባት ነው። በመሆኑም ከጋብቻ በፊት መታቀብ ያስፈልጋል። ብዙ ሰዎች ከተዋወቁበት ዕለት
አንሥቶ እንደ ባልና ሚስት መኖር ይጀምራሉ፡። በአገር ቤት ተቀጣጥሮ በመገናኘት ፥ በውጭው ዓለም ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥ
አብሮ በመኖር ፦ ሁሉ ነገር ከጋብቻ በፊት ተጀምሮ ከጋብቻ በፊት ያልቃል። ግልጽ በሆነ አነጋገር ሳይጋቡ ተጋብተዋል። ይሁን
እንጂ እነርሱም ፥ቤተሰብም ፥ሽማግሌም ፥ማዘጋጃቤትም ፥ቤተ ክርስቲያንም አላጸደቁትም። ሲጠየቁ ፦ አሥር ዓመት ሙሉ እየተጠናኑ
ነው። «እጮኛ አለኝ ፥ አለችኝ፤» የሚለውም በሕጋዊ መንገድ የጸደቀ አይደለም።
በዚህ መንገድ ያላለፉ ሰዎችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። አሁን አሁንማ ሰለጠንኩ ባዩን
ከተሜውን ጨርሶት ገጠሬውንም እየተቆጣጠረው ነው። በዚህ መካከል አንዱ ሌለኛውን እንደ ሸንኰራ መጥጦ ፥ ጣእም አሳጥቶ የመትፋት
(የመጣል ፥የመክዳት) አደጋ ይከሠታል። ይህም የወንዱንም ሆነ የሴቱን ቅስም የሚሰብር ነው። በዚህ የተነሣ፦ ተስፋ ቆርጠው
መማር አቅቷቸው ፥ መሥራትም ተስኗቸው ሕይወታቸው የተመሰቃቀለባቸው ሰዎች ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። ራሳቸውን ለማጥፋት የተመኙ
፥የሞከሩ ፥የደፈሩም የሉም ማለት አይቻልም።
በመተጫጨት ዘመን ሁሉን ነገር ጨርሰው ከተጋቡ በኋላ የጋብቻ ትርጉሙ የሚጠፋባቸው ብዙዎች ናቸው።
ይኸውም፦ ከጋብቻ በፊት የነበራቸው ሕይወትና ከጋብቻ በኋላ የሚኖሩት ሕይወት ተመሳሳይ ስለሚሆንባቸው ነው። የቤት ለውጥ ካልሆነ
በስተቀር አዲስ ነገር ያጡበታል። ከጋብቻ በፊት ተሰለቻችተው ይሰነብቱና በተሰላቸ መንፈስ ጋብቻን ይጀምራሉ። በዚህም ምክንያት
የጋብቻ ኑሮ እጅ እጅ ይላቸዋል። እንግዲህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፦ እስከ ጋብቻ ድረስ በተአቅቦ መኖር የሚያስፈልገው።
በክርስትና ከጋብቻ በፊት እንደ ባልና ሚስት መኖር ዝሙት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል
መጋባት ይሻላልና ፥ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ። » ያለው፦ ከጋብቻ በፊት ራስን ካለመግዛት የተነሣ በዝሙት እንዳይወድቁ
ነው። ፩ኛ ቆሮ ፯፥፱። ከዚህም አስቀድሞ « ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም ፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ . . .
ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን?
አይገባም። . . . ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ
ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት
በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ
በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።» የሚል ተጽፏል። ፩ኛ ቆሮ ፮፥፲፫-፳። ስለዚህ ጸንተን ያለን በጽናታችን መቀጠል ፥ ያልጸናን
ደግሞ በንስሐ መስተካከል ይጠበቅብናል። በንስሐ የማይሰረይ ኃጢአት ፥ የማይደመሰስ በደል የለም። የሐዋ ፪፥፴፰። እግዚአብሔር
በነቢዩ በሕዝቅኤል አንደበት ፦ «ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፥ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፥ ነፍሱን (ሰውነቱን)
ይጠብቃል። አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሷልና ፈጽሞ በሕይወት
ይኖራል እንጂ አይሞትም።» በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ሕዝ ፲፰፥፳፯። በመሆኑም ሰው አንዴ ንስሐ ከገባ በኋላ ፦ «
ትናንተ እንዲህ ነበርና ይሙት በቃ ይፈረድበት፤» ማለት አይገባም። ይህም በዕውቀትም ይሁን ያለዕውቀት በራስም ላይ ጭምር
መፍረድ ነው። ምክንያቱም ሁሉም የየራሱ ትናንት አለውና።ስለዚህ ዛሬ ምን እየሠራ ነው? ለነገስ ምን አቅዷል ማለት ይገባል።
እግዚአብሔር ያነጻውን ማቆሸሽ ፥ የቀደሰውንም ማርከስ አይቻልምና።
ብዙ ሰው የሚያጨቃጭቀው የሚያነዛንዘው የዛሬው ማንነት ሳይሆን የትናንቱ ነው። ይህም፦ በእንባ
ታጥቦ ጽርሐ አርያም የደረሰውን ቅዱስ ጴጥሮስን ከሃዲ እንደ ማለት ነው። ወይም እስከ ሦስተኛ ሰማይ የተነጠቀውን ፥ የሕይወት
አክሊል የተዘጋጀለትን ቅዱስ ጳውሎስን አሳዳጅ ብሎ እንደ መርገም ነው። ወይም በእንባዋ ታጥባ ትንሣኤ ክርስቶስ የተገለጠላትን
፥ ቅዱሳን መላእክት ያነጋገሯትን ፥ ለቅድስና በቅታ ጽላት የተቀረጸላትን መግደላዊት ማርያምን አመንዝራ ብሎ እንደመሳደብ ነው።
ስለዚህ በንስሐ የተደመደመውን ነገር ሁሉ ትተን ፥ በዛሬ ላይ ተማምነን ወደ ነገ መጓዝ ነው።
በትዳር ውስጥ የምናያቸው አለመግባባቶች በአብዛኛው የእጮኝነት የዞሩ ድምሮች ናቸው። እንደ ዋዛ
ያየናቸው ወይም ምንም አያመጡም በሚል፦ ቸል ያልናቸው ሁሉ የምር ሆነው ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ። የእጮኝነት ጊዜ የብቃት
ዘመን በመሆኑ ሁሉን በትእግሥት እናሳልፍና ወደ ጋብቻው ስንገባ፦ በአንድ ጊዜ ከፍጹምነት ማዕረግ ወደ ታች ወርደን ወጣኒ
(ጀማሪ ፥አዲስ) እንሆናለን። ትናንት የተፈታው ችግር ዛሬ እንዳይፈታ ሆኖ ይቋጠራል ፥ ትናንት የታገሥነው ዛሬ ደማችንን
ያፈላዋል። ትናንት ስንነጋገርበት የተወገደ የመሰለን ችግር ልክ እንደ ቫይረስ ራሱን ደብቆ ፥ ስንዳከም ጠብቆ ፥ ኃይሉን
አጠንክሮ ይመለሳል። ስለዚህ ፦ «አለባብሰው ቢያርሱ ፥ በአረም ይመለሱ፤» ነውና በደንብ ማረስ ፥ በደንብ መጐልጐል
ያስፈልጋል። የእጮኝነት ዘመን « ችግር የለውም ፤» እያልን አለባብሰን የምናልፍበት ሳይሆን፦ «ችግር ሊያመጣ ይችላል፤» ብለን
የምንጠነቀቅበት ነው።
ብርቱ ገበሬ፦ ምን በርትቶ ቢያርስና ቢጐለጉል ፥ ከዚህም ጋር የአረም መድኃኒትም ቢረጭ ፥ዘሩንም
አበጥሮ አንጠርጥሮ ቢዘራ፥ አረምን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይችልም። ያለው እድል ፦ ቀስ ብሎ አረሙን ለይቶ ለመንቀል መድከም
ብቻ ነው። እኛም ምን ብንጠነቀቅ የማናስቀራቸው ችግሮች አሉ። በመሆኑም የገበሬ ትእግስት ስጠኝ ብሎ መድከም ነው። አንዳንድ
ሰው፦ ዘጠና በመቶው ጥሩ ሆኖለት እንኳ፦ በጐደለችው በአሥሯ
ምክንያት ሲበጠበጥ ሲበጠብጥ ይኖራል። ይህም ከቁጥር በላይ የሆኑ የገነት ዕፅዋት ተሰጥተውት ሳለ በአንድ በለስ ምክንያት ችግር
ውስጥ እንደገባው አዳም መሆን ነው። ስለዚህ በሰው ድካም ላይ ሳይሆን በብርታቱ ላይ ማተኰር ነው። ያንጊዜ ደካማ ጐኑን
እንረሳለታለን ፥ እርሱም ይረሳልናል። አለበለዚያ አዳም የዕፀ በለስ ፍሬ በልቶ አምላክ ላይሆን፦ ገነትንም እግዚአብሔርንም
አጥቶ እንደተቀመጠ ፥ እኛም ለትንሽ ነገር ስንኘካኘክ ብዙ ጥሩ ነገር ልናጣ እንችላለን።
No comments:
Post a Comment