በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ በጥሬ-ቃል “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ወይንም ሐረግ 7361 (ሰባት ሺ ሦስት መቶ ስልሳ አንድ) ጊዜያት ተጠቅሶና ተጽፎ እናገኛለን። እንደዚህ ቢሆን መፅሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥም በአንድም በሌላም መንገድ እናገኘዋለን፤ ለምሳሌ እኔ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆ አምላክ እንዲል።
"እግዚአብሔር
ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው!" በሚለው በዚህ ጥቅስ
ውስጥ ሁለት ዓበይት ነገሮችን እናገኛለን። ይኸውም፦
1ኛ . "እግዚአብሔር"
2ኛ . "ተዋጊ" የሚሉትን ቃል ወይንም ሐረግ ናቸው።
"እግዚአብሔር"
ማለት «ያለና የሚኖር፣ መጀመርያውና መጨረሻው፣ አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፤» ማለት ነው፥ ይህም የዘላለሙ ስሙ ነው። /ዘጸ 3፥14፤ ራእ 1፥17፣ 2፥8፣ 21፥6፣ 22፥13፤/
"ተዋጊ" ማለት ደግሞ በአንድም በሌላ መንገድ እግዚአብሔር
ስለ እኛ መጠጊያ፣ ስለ እኛ ጋሻ፣ ስለ እኛ መከታ፣ ስለ እኛ ተዋጊ
(ይዋጋል)፥ እኛም ዝም እንላለን! እርሱም፥ ማዳኑን፣ ፍቅሩን፣ ቸርነቱንና ምህረቱን በእነዚህ መንገዶች ይገልጥልናል ማለት ነው። /ዘጸ 14፥14፤ ዘዳ
1፥30፣ 3፥22፤ ነህ 4፣20፤ 2ኛ ሳሙ 22፥31፤ መዝ 5፥12፣ 28፥7፣ 90፥1፣ 91፥1-10፤ ምሳ 30፥5፤ ኢሳ 38፥14፤ ዘካ 14፥3፤ ሮሜ 13፣12፤ ኤፌ 6፥16፤ ዮሐ 19፥11፤/
እግዚአብሔር ማለት «ያለና የሚኖር፣ መጀመርያውና መጨረሻው፣ አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፤» ነው ካልን፤ ታዲያ ተዋጊ ደግሞ፥ መጠጊያ፣ ጋሻ፣ መከታና ተዋጊ እንደሆነ ተመልክተናል። ስለዚህ ሁለቱን ስናቀናጀው፥ እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፣ እግዚአብሔር ጋሻ ነው፣ እግዚአብሔር መከታ ነው፣ እግዚአብሔር መጠጊያ ነው፤ የሚሉ ሐይለ ቃል ወይንም ሐረግ እናገኛለን።እንግዲህ የእነዚህን የሁለቱን ትርጉሞችን ከተረዳን እንደ እግዚአብሔር
ፈቃድ "እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው!"
የሚለው ጥቅስ እንዴት እንየው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ?
* የእግዚአብሔር፥ ጋሻ፣ መከታና ውጊያ፤ ወደ ፈርዖን
ቤት፦
እስራኤል ዘ ሥጋ በጽኑ ሐዘን፣ በከባድ የጉልበት ሥራ፣ በመረረ ለቅሶና
በታላቅ በሆነ ጩኽት በግብፅ ምድር ሳሉ ነበር እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ለሙሴ ተገልጦለት ወደ ፈርዖን
ቤት ሄዶ ህዝቤን እንዲያገለግለኝ ልቀቅ በል ብሎት በሰደደው ጊዜ ነበር ሊቀ ነቢያት ሙሴ አንድ
ጥያቄ ጠየቀ።
የሊቀ ነቢያት ሙሴ ጥያቄም፦ "ሙሴም፥ እግዚአብሔርን ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? ብሎ በጠየቀው ጊዜ፤ እርሱም
(እግዚአብሔር)፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር
ትገዛላችሁ አለ። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፣ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ?
ሲል፤ እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ ብሎታል። እንዲህ ለእስራኤል ልጆች «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ። እግዚአብሔርም
ደግሞ ሙሴን አለው፥ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ፤ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።" ትላለህ ብሎታል። /ዘጸ 3፥11-15/
እዚህ ጋር ታዲያ በእግዚአብሔር ፍቃድ አዛዥነት፣ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ታዛዢነት፤ እስራኤል ዘ ሥጋ በብዙ መከራና ችግር፣ ከውጣ-ውረድና እንግልት፤ ከባርነት ወደ ነፃነት ከመውጣታቸው በፊት እግዚአብሔር ትእዛዝ አዟቸው ነበር። ትእዛዙም፦ የበጉ የደም ምልክት በቤቶቻቸው እንዲሆንላቸው
ነው። ከወጡ በኋላ
ደግሞ ትእዛዙን እንዲጠብቁት እርሱ የበጉ
የደሙ ምልክት የእግዚአብሔር ፋሲካ
ነውና በዓል አድርጉ ብሎ ትእዛዝ አዟቸዋል።
“የበጉ የደሙ ምልክት የእግዚአብሔር ፋሲካ ነውና በዓል
አድርጉ” የበጉ የደም ምልክትና ፋሲካ የሚለውን! ልብ ይበሉ!
* እስራኤል ዘ ሥጋ፦
እስራኤል ዘ ሥጋ በወጡበት ወቅት፥ ሠላም፣ ሐሴት፣ ፍስሐ፤ በሆነበት፥ በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው
ተናገሩ።
በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤
ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤
ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁም፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለ።
እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤
የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤
የተመረጡት ሦተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ።
ቀላያትም ከደኑአቸው፤
ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ።
አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤
አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ።
በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤
ቁጣህን ሰደድህ፥ እንደ ገለባም በላቸው።
በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥
ፈሳሾችም እንደ ክምር ቆሙ፤
ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ።
ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥
ምርኮንም እካፈላለሁ፥
ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤
ሰይፌንም እመዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች
አለ።
ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤
በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ።
አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
በምስጋናህ የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥
በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው።
በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን
ሕዝብህን መራህ፤
በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው።
አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤
በፍልስጥኤም የሚኖሩት ምጥ ያዛቻው። /ዘጸ 15፥ 1-14/
የሊቀ ነቢያት ሙሴ ኅህት ማርያም፣ ዘማርያንና ዘማሪያት ተሰብስበው በሆሆታና በእልልታ የእግዚአብሔርን፥ ተዋጊነት፣ ኃያልነት፣ መድኃኒትነት፣ መጠጊያነት፣ ጋሻነት፤ ከመዝሙሩ መንፈሳዊ ሥነ ግጥም መረዳት እንችላለን።