አንድ ወዳጄ በየገጸ ድሩና በየውይይት መድረኩ የሚሰማውን ‹መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፣ መጀመሪያ ትግሬ ነኝ፣ መጀመሪያ አማራ ነኝ› የሚል ክርክር አየና ‹አንተ መጀመሪያ ምድንነህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
እኔ መጀመሪያ ሰው ነኝ፡፡ የተፈጠርኩትም ሰው ሆኜ ነው፡፡ አምላክም የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ቡድን፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ነገድ የሚባሉ ነገሮችን ፈጠረ የሚል መጽሐፍም ትምህርትም አላገኘሁም፡፡ ክብርም፣ ሥልጣንም፣ ጥበብም፣ ፈጣሪውን መምሰልም የተሰጠው ለሰው ነው፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ በማኅበር ነው የተፈጠሩት፡፡ አንድ ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሰው ግን ሲፈጠር በየተራ ነው፡፡ መጀመሪያ አዳም፣ ከዚያ ሔዋን፣ ከዚያ ቃየል፣ ከዚያ አቤል እያለ ተራ በተራ፡፡ ቡድኖቹን ሰው በኋላ ራሱ ፈጠራቸው እንጂ አብረውት አልተፈጠሩም፡፡
መጀመሪያ ሰውነቴ ነበረ፤ በኋላ ቡድኔ መጣ፡፡ በኋላ የመጣው ቡድኔ በፊት የነበረውን ሰውነቴን ከዚህ አትለፍ ከዚህ አትውጣ፣ ከዚህ አትዝለል ከዚህ አትሻገር አለው፡፡ ቡድኔ በእኔ መጠራት ሲገባው እኔ በቡድኔ ተጠራሁ፡፡ ለእርሱ ህልውና ሲል እኔን ሰዋኝ፡፡ እርሱ ሳይመጣ በፊት ግን እኔ ሰውዬው ነበርኩ፡፡
መጀመሪያ ሰው ስለነበርኩ መጀመሪያ ሰው ነው መከበር ያለበት፣ መጀመሪያ ሰውነቴ ነው መብት የሚያስፈልገው፣ ሰውነቴን አሥረህ፣ ገርፈህ፣ ገድለህ፣ ነጥቀህ፣ ቀምተህ ቡድኔን ከየት ታገኘዋለህ? እኔን ትተህ እንዴት እኔ ለፈጠርኩት ቅድሚያ ትሰጣለህ? እኔን ንቀህ እንዴት እኔነት ተሰባስቦ ላቋቋመው ቡድን ክብር ትሰጣለህ? ይኼማ ሐሰት ነው፡፡ ሴሎቹን ገድለህ ሰውየውን ማኖር ትችላለህ? ገጾቹን ገንጥለህስ መጽሐፉን ታኖራለህን? ከብቶቹን አርደህ ስለ መንጋው መጨነቅስ ምን ማለት ነው?