አንድ ወዳጄ በየገጸ ድሩና በየውይይት መድረኩ የሚሰማውን ‹መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፣ መጀመሪያ ትግሬ ነኝ፣ መጀመሪያ አማራ ነኝ› የሚል ክርክር አየና ‹አንተ መጀመሪያ ምድንነህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
እኔ መጀመሪያ ሰው ነኝ፡፡ የተፈጠርኩትም ሰው ሆኜ ነው፡፡ አምላክም የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ቡድን፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ነገድ የሚባሉ ነገሮችን ፈጠረ የሚል መጽሐፍም ትምህርትም አላገኘሁም፡፡ ክብርም፣ ሥልጣንም፣ ጥበብም፣ ፈጣሪውን መምሰልም የተሰጠው ለሰው ነው፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ በማኅበር ነው የተፈጠሩት፡፡ አንድ ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሰው ግን ሲፈጠር በየተራ ነው፡፡ መጀመሪያ አዳም፣ ከዚያ ሔዋን፣ ከዚያ ቃየል፣ ከዚያ አቤል እያለ ተራ በተራ፡፡ ቡድኖቹን ሰው በኋላ ራሱ ፈጠራቸው እንጂ አብረውት አልተፈጠሩም፡፡
መጀመሪያ ሰውነቴ ነበረ፤ በኋላ ቡድኔ መጣ፡፡ በኋላ የመጣው ቡድኔ በፊት የነበረውን ሰውነቴን ከዚህ አትለፍ ከዚህ አትውጣ፣ ከዚህ አትዝለል ከዚህ አትሻገር አለው፡፡ ቡድኔ በእኔ መጠራት ሲገባው እኔ በቡድኔ ተጠራሁ፡፡ ለእርሱ ህልውና ሲል እኔን ሰዋኝ፡፡ እርሱ ሳይመጣ በፊት ግን እኔ ሰውዬው ነበርኩ፡፡
መጀመሪያ ሰው ስለነበርኩ መጀመሪያ ሰው ነው መከበር ያለበት፣ መጀመሪያ ሰውነቴ ነው መብት የሚያስፈልገው፣ ሰውነቴን አሥረህ፣ ገርፈህ፣ ገድለህ፣ ነጥቀህ፣ ቀምተህ ቡድኔን ከየት ታገኘዋለህ? እኔን ትተህ እንዴት እኔ ለፈጠርኩት ቅድሚያ ትሰጣለህ? እኔን ንቀህ እንዴት እኔነት ተሰባስቦ ላቋቋመው ቡድን ክብር ትሰጣለህ? ይኼማ ሐሰት ነው፡፡ ሴሎቹን ገድለህ ሰውየውን ማኖር ትችላለህ? ገጾቹን ገንጥለህስ መጽሐፉን ታኖራለህን? ከብቶቹን አርደህ ስለ መንጋው መጨነቅስ ምን ማለት ነው?
ሀገር ይቀየራል፣ ቋንቋ ይቀየራል፣ ባሕል ይለወጣል፣ እምነት ይለወጣል፣ ጎሳ ይለወጣል፤ ሰውነት ግን እኔ ነኝ፡፡ እነዚህን ሁሉ መቀየር የቻልኩት ሰው ስለሆንኩ ነው፡፡ ሰው ሆኜ ስለተፈጠርኩ ከሰዎች ጋር እኖራለሁ፡፡ ለብቻዬ የማልችላቸውን ነገሮች በጋራ ለመከወን፡፡ ያን ጊዜ የጋራ መግባቢያ ያስፈልገኛል፡፡ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ልማድ፣ ወግ፣ ሥርዓት ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰዎችን በጋራ ለማኖር፣ ሲኖሩም ተግባብተውና የጋራ የሆነ እሴት ኖሯቸው እንዲኖሩ ለማድረግ በእኔ በሰውየው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሊተውኝ አይችሉም፤ ልተዋቸው ግን እችላለሁ፡፡ ያለ እነርሱ መኖር እችላለሁ፤ ያለ እኔ መኖር ግን አይችሉም፡፡ እኔ ነኛ ዋናው፡፡
ስለዚህ ነው መጀመሪያ ሰው ነኝ ያልኩት፡፡ ሰው ስለሆንኩ የሰው ሁሉ ነገር ይመለከተኛል፡፡ የሰውም ሁሉ ነገር ያሳስበኛል፡፡ ያ ሰው ማንም ይሁን፣ ምንም ዓይነት ቋንቋ ይኑረው፤ የትኛውንም ዓይነት ባሕል ይከተል፡፡ እርሱ እኔና እርሱን አያገናኘንም፡፡ መገናኛችን ሰውነት ነው፡፡ የእሥረኛው ነገር ይመለከተኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለታሠረ፤ የሟቹ ነገር ይቆረቁረኛል፤ ምንያቱም ሰው ስለሞተ፤ የተገፋው ልቅሶ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለተገፋ፤ የተቀማው ዕንባ ያርሰኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለተቀማ፡፡
እንደሰው በፈጠረው ነገር መልሶ የሚጠፋ፣ በሠራው ነገር መከራ የሚያይ፣ ባመጣው ነገር የሚሄድ፣ ባስገኘው ነገር የሚታሠር ፍጡር የለም፡፡ ራሱ ያመጣቸው ጎሳዎች፣ ነገዶች፣ ቡድኖች ራሱን እንዳያይና የተፈጠረበትን እንዲረሳ አድርገውታል፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ሰውነትን እንዲረሳ፡፡ ‹እገሌ እንዲህ ሆነ› ሲሉት ‹ሀገሩ የት ነው፣ የማን ወገን ነው፣ የኛ ሰው ነው፣› ጎሳ ነገዱ፣ ወንዙ ጎጡ እያለ እያጠበበ ይጠይቃል፡፡ የሰውየው ማንነት ከእርሱ ቡድን እየራቀ በሄደ ቁጥር ጭንቀቱ ይቀንሳል፡፡ አንዳንዴም እንደ ድል ይቆጥረዋል፡፡ ‹የራሱ ወገን› የተጠቃ ሲመስለው ግን አራስ ነበር ሆኖ ይነሣል፡፡ ራሱ በፈጠረው አጥር ራሱን አጥሮ፤ መገናኛውን ሰውነትን ሰብሮታል፡፡ ያም ሰውኮ ሰው ነው፡፤ መጀመሪያ ሰው ነው፡፡ ሰው ስለሆነ ነው እንደዚያም የሆነው፡፡ ሃይማኖት የኖረው ሰው ስለሆነ ነው፣ ባሕልም የኖረው ሰው ስለሆነ ነው፣ በቋንቋም ያወራው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ የተለየ አመለካከትም የያዘው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ የሚቃወምህም ሰው ስለሆነ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰው ነው፡፡
ያኛው ባሕል፣ ያኛው እምነት፣ ያኛው ቋንቋ፣ ያኛው አስተሳሰብ፣ ያኛው ልማድ፣ እንዲከበር፣ መብቱም እንይደፈር፣ ዋጋም እንዳያጣ የምፈልገው - የሰው ስለሆነ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ሰው ስላለበት ነው፡፡ የዚያኛው ፓርቲ፣ የዚያኛው ማኅበር፣ የዚያኛው ቡድን መብትና ክብር እንዲጠበቅ የምሟገተው ስለማምንበት፣ ስለምቀበለውና ስለሚስማማኝ አይደለም - ሰው ስላለበት ነው፡፡ የሰው ስለሆነ ነው፡፡ በተለየ መንገድ የተደራጀው፣ በተለየ መንገድ ያሰበው፣ በተለየ መንገድ የሄደው፣ በተለየ መንገድ ያመነው፣ በተለየ መንገድ የተፈላሰፈው ሰው ስለሆነ ነው፡፡
ልዩነቱን እንኳን መፍጠር የቻለ-ሰውኮ ነው፡፡ ሌሎቹ ፍጡራን ልዩነታቸው ተፈጠረላቸው እንጂ ልዩነትን አልፈጠሩትም፡፡ ሰው ግን ባሕል፣ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ሥርዓት፣ ሀገር፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብ የሚባሉ ነገሮችን አምጥቶ የገዛ ልዩነቱን ራሱ የፈጠረ ነው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰው ስለሆነ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚከብሩት ሰው ሲከብር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ህልው የሚሆኑት ሰው ህልው ሲሆን ነው፡፡
አማራ ሆኖ፣ ኦሮሞ ሆኖ፣ ሶማሌ ሆኖ፣ ሕንድና ቻይና ሆኖ፣ እንግሊዝና ጣልያን ሆኖ የተወለደ የለም፡፡ ሁሉም ሰው ሆኖ ነው የተወለደው፡፡ ባሕሉን ለመደው፣ ቋንቋውን ለመደው፣ አለባበሱን ለመደው፣ ሀገሩን ለመደው እንጂ ራቁቱን፣ ቋንቋ ሳያውቅ፣ ወገን ሳይኖረው ነው የተወለደው፡፡
አሁን አሉኝ የምላቸው ልዩነቶች በሙሉ ቢነሡ፣ ከልዩነቶቹ ሥር እኔ ሰውዬው ብቻዬን ቆሜ እገኛለሁ፡፡ ሰው ነኛ፡፡ መጀመሪያም ሰው ነኝ፤ መጨረሻ ሰው ነኝ፡፡
ምንጭ፦( ከዳንኤል ክብረት ዕይታዎች )
No comments:
Post a Comment