Wednesday, December 10, 2014

«ወዮልኝ» መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው



        በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
                              «ወዮልኝ»

እግዚአብሔር ሰዎች «ወዮልኝ፤» እያሉ ራሳቸውን ገሥጸው ይኖራሉ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ፊት ለፊት ስላየው ፥ ቃል በቃል ስላነጋገረው፡- «አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፡- «ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥ አትሞትም፤» ብሎታል። (መሳ ፮፥፳፪)። ነቢዩ ኤርምያስም፡- «በሆድ ሳልሠራ አውቄሃለሁ፥ ከማኀፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሐዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» በተባለ ጊዜ፡- «ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤» ብሏል። (ኤር ፩፥፬)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤ » ብሏል። (፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮)።

          እነዚህ «ወዮልኝ፤» ማለታቸው ለእኛ አብነት ነው። ታላላቆቹ እንዲህ ካሉ ከእኛ ከታናናሾቹ የብዙ ብዙ ይጠበቃል። ዕለት ዕለት «ወዮልኝ፤» እያልን ደረታችንን ልንደቃ፥ እንባችንን ልናፈስስ ይገባል። ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በስተቀር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን አናውቅምና። ሰውን ደስ ለማሰኘት በሰውም ዘንድ ለመወደድ (ለውዳሴ ከንቱ) እግዚአብሔርን እናሳዝናለንና። እንኳን መንፈሳዊ መሆን መምሰሉ እንኳ አቅቶናልና። ሃያ፥ ሠላሳ ዓመት ቃለ እግዚአብሔር ዘር ተዘርቶብን፡- ሠላሳ ስድሳ መቶ ማፍራት የተሳነን ዘረ ቆርጥሞች ነንና። መቁረባችን ማቁረባችን መቀደሳችን ማስቀደሳችን ማሳለማችንመሳለማችን መናዘዛችን ማናዘዛችን መዘመራችን ማዘመራችን መስበካችን መሰበካችን ሁሉ ከንቱ ሆኖብናልና። ስለሆነም «እገሌ ሳይገባው ነው፤» የሚለውን ትተን፡- «እኔ ሳይገባኝ ነውና ወዮልኝ፤» እንበል። የእግዚአብሔር ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ አይጠብቁምና።

                                                           «ወዮላችሁ»

          የዓለም ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ ይጠብቃሉ፤ ተብለውም አይመለሱም፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቃሉን ትምህርት ሰምተው፥ የእጁን ተአምራት አይተው ያልተመለሱትን ጸሐፍት ፈሪሳውያንን በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስምንት ጊዜ «ወዮላችሁ፤» ብሏቸዋል።

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።»

* «ማንም በቤተመቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተመቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሓላው ይያዛል  የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ ከአዘሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ሰለምታወጡ፥ ፍርድንና  ምሕረትን፥ ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውስጡ ቅሚያና ስስት፦ ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭስለምታጠሩ ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ  የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።»

* «እናንተ ግብዞች ጻፍችና ፈሪሳውያን፦ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ ፥ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም በአልተባበረናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።»

         አይሁድ «ወዮላችሁ፤» ተብለውም አልተመለሱም፥ ጌታም እንደማይመለሱ ያውቃል። ስለሚያውቅም «እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?» ብሏቸዋል (ማቴ ፳፫፥፲፫-፴፪)። ከእነርሱም በፊት የኮራዚንና የቤተ ሳይዳ ሰዎች «ወዮላችሁ»፤ ብሏቸው ነበር (ማቴ ፲፩፥፳፩)። ይኸውም ንስሐ ባለመግባታቸው ነው።

የሰዶምና የጐመራ ሰዎች እነርሱ ያገኙትን ዕድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ፦ ማቅ ለብሰው፥ ዓመድ ላይ ተኝተው ንስሐ ይገቡ እንደነበር ነግሯቸዋል። እኛም ያገኘነውን ዕድል ያላገኙ ብዙ ሕዝቦች እንዳሉ ማስተዋል አለብን። ጌታችን፦ «ወዮ ለዓለም ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።» ያለበትም ጊዜ አለ (ማቴ፲፰፥፯)። ያ ሰው የተባለ ለጊዜው ይሁዳ ሲሆን ለፍፃሜው የሁላችንንም ሕይወት ይመለከታል። በአንድም ይሁን በሌላ የእኛም ሕይወት ለሌላው መሰናክል እንቅፋት እየሆነ ነውና።

ንጹሐ ባርይ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ወዮላችሁ፤» ቢል የባህርይ አምላክ በመሆኑ ነው። ቅዱሳንም፦ «ወዮላችሁ» ቢሉ ከኃጢአት ርቀው ከበደል ተለይተው ሃይማኖት ይዘው ምግባር ሠርተው ነው። እኛ ግን እምነታችን ደካማ ጸሎታችን የማይሰማ ምግባራችን ጐዶሎ መሆኑን እያወቅን ሌሎችን «ወዮላቸው» እንላለን። ከምዕመናን ከዲያቆናት ከቀሳውስት ከመዘምራን ከሰባክያን ከጳጳሳት የማንፈርድበት የለም። አንድም ቀን በራሳችን ፈርደን፥ «ወዮልን፤» ብለን አናውቅም። ስለዚህ ኃጢአታችን እንዲሠረይልን በደላችንም እንዲወገድልን የዘወትር ጸሎታችን «ወዮልኝ፤» የሚል ይሁን። በሌላ በል ግን ሃይማኖት ሥርዓት ትውፊት ሲጠፋ ተመክረው ተገሥፀው የማይመለሱትን «ወዮላችሁ፤» ብሎ ማስጠንቀቅ መፍረድም ይገባል። እንግዲህ እንደ ፈሪሳዊያን ከመሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፥ ድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቀን አሜን!።
                             ------------------------- / / --------------------


ምንጭ፦ (የቀድሞ ቤተ ደጀኔ መንፈሳዊ ድረ ገፅ) www.betedejene.org




No comments:

Post a Comment