(ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም) ያስተማሩት።
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የተወደዳችሁ ምእመናን! እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ።
ጋድ (ገሃድ) እና ገና፥ ልደቱ ለእግዚእነ። (ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ/ም)
«ጾመ ገሃድ (ጋድ)፦ የቃሉ ትርጕም «ገሃድ» ሲል መገለጥ፥ «ጋድ» ሲል ለውጥ ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት፦
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ በዓል በሳምንት ሁለት ቀን በምንጾምባቸው ጾም በተሠራባቸው በረቡዕና
በዓርብ የዋለ እንደ ሆነ የጾሙ ሥርዓት ሳይጠበቅ፤ ፩ኛ፤ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ለ፳፱ አጥቢያ፤ ፪ኛ፤ ጥር ፲ ቀን
ለ፲፩ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ቅዳሴ እንዲፈጸምና ምእመናን በትንሣኤው የአከባበር ሥርዐት ዐይነት በዓሉን በደስታ
እንዲያከብሩ አዝዘዋል። ስለዚህ ሁለቱም ማለት የልደት፥ የጥምቀት ዋዜማ በጾም እንዲታሰብ ሆኗል።
በአንድ
በኩል የጌታን መገለጥ የምናስብበት ነው። መገለጥ ሲባልም እንደ በዓላቱ ጠባይ ሁለት ነው። በልደት መገለጥ ሲባል
ሰው ሆኖ የማያውቅ አምላክ በሥጋ ሰው ሆኖ በአጭር ቁመት፥ በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለ ተገለጠና ሰዎች ሊያዩት
ሊዳስሱት ስለ ቻሉበት ነው።
በጥምቀት መገለጥ መባሉ፤ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ ፴ ዓመት
ዕድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲሕ፥ ሰው የሆነው አምላክ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ
ከኖሩ በኋላ በ፴ ዓመት ዕድሜው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፤ አብ፤ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን
ስሙት፤» ብሎ በሰጠው ምስክርነት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት
የተነበዩለት የሰው ልጆች መድኃኒት ሥግው አምላክ ማለት ሰው የሆነ አምላክ እሱ መሆኑ ስለ ተገለጠበት ነው። ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ ቅዳሜ፥ እሑድ ቢሆን በሰንበት ጾም ስለ ሌለ ሥርዓተ ጾሙ ከጥሉላት ምግብ በመከልከል ብቻ ይፈጸማል።» [የጽድቅ በር፤ ፲፱፻፸፱ ዓ ም፤ ገጽ ፳፯ - ፳፱።]
«ልደቱ ለእግዚእነ። ይህ በዓል ሰውን በመልካችን በምሳሌአችን እንፍጠር ብሎ በጥንተ ፍጥረት የተናገረ እግዚአብሔር
ቃል የሰውን ልጆች ለማዳን፤ «አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ።» «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ እመጣለሁ፤»
ሲል በሰጠው ተስፋ፤ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ያለ አባት የተወለደበት ነው። ቅድመ
ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው እግዚአብሔር ቃል ወልደ አብ ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
መወለዱና ወልደ ማርያም መባሉ ለሰው ልጆች ክብርና ሕይወት ስለ ሆነ፤ ሥጋ ቃልን ተዋሕዶ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ
ከሰማያውያን መላእክት፥ ከምድራውያን ኖሎት (እረኞች) ምስጋናን በግልጥ የተቀበለበትን፥ ለሰው ልጆች ዕርቅ
የተመሠረተበትን ይህንን ታላቅ በዓል ኢትዮጵያ ከዓለም ክርስቲያኖች ጋራ በመተባበር ታከብረዋለች። (ዘፍ፤ ፲፰፥ ፲።
ሉቃ፤ ፪፥ ፲፫ - ፲፱።)
መሠረቱም፤ «እነሆ በኤፍራታ በጎል ተጥሎ፥ በጨርቅ ተጠቅልሎ አገኘነው፤
በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው፤ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተን የጌታችን እግር ከቆመበት
እንሰግዳለን፤» የሚለው ትንቢታዊ ቃል ነው። (መዝ ፻፴፪፥ ቍ ፮ እና ፰።) [የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤
ገጽ ፪፻፴፭]
(ክቡር አባታችን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ በዓለ ልደትን በማስመልከት ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ያስተላለፉንት መንፈሳዊ ትምህርት ነው። በተጨማሪም፦ በስማቸው የተሰየመውን የሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩን መንፈሳዊ መጦመርያ ይጎብኙ (ለአባታችን፥ ለሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ፦ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፤ ጸጋ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!!!)
No comments:
Post a Comment