Tuesday, January 6, 2015

ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ (በምሥጢረ ሥጋዌ አስተምህሮ)


                 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

      ተሠገወ፡- ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህሥጋዌሰው መሆንን፣ መገለጽን (በተአቅቦ) መግዘፍን፣ መወሰንን፣ መዳሰስን ያመለክታል። ቀድሞ ምን ነበር? ወይም ማን? ለሚለው ጥያቄ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልበመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ.11) ሰው የሆነም አካላዊ ቃል እንደሆነቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ።በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐ.114) ሰው የሆነውም በተዋሕዶ ነው። ይኸውምአንድ ጊዜ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነውበማለት ነው። ምሥጢረ ሥጋዌ የአብ አካላዊ ቃል ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል ሰው የሆነበት፤ ሰውንም ያዳነበት መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ማለት ነው።
 
      ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) የለም። ሞትን በቀመሰ ጊዜም መለኮት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም። በዚህም ምክንያት ሞቱ እንደሌሎች ፍጡራን ወይም እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የማይታይ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስእርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፤ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።ሲል ገልጦልናል። (ዕብ. 214) በመሆኑም ሲራብም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲተኛም፣ ሲነሳም፣ ተዓምራት ሲያደርግም፤ በአንድ ባሕርይ ጸንቶ እንጂ እንደ ማየ ግብጽ በሚጠት አንድ ጊዜ አምላክ አንድ ጊዜ ሰው እየሆነ አይደለም።

        ሰው የሆነውም እንደ ወይነ ቃና እና እንደ ብእሲተ ሎጥ (የሎጥ ሚስት) በውላጤ (በመለወጥ) እንደ መስኖ ውኃ በኅድረት፤ ሳይሆን ተአቅቦ ባልተለየው ተዋሕዶ ነው።የሰውን ሥጋ ነሥቶ ቢዋሐድ እንጂ ሥጋንማ ባይነሳ እንደምን ሰው በሆነ ነበር፤ ነፍስን ሥጋን መዋሐዱም መለወጥ፤ መቀላቀል ፤መለየት በሌለበት የሁለቱን ባሕርያት አንድነት እነደፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ አንድ አደረገ። ሥጋ ሥጋ ነውና፤ መለኮት አይደለም። እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ቢሆንም ቃልስ አሁን አምላክ ነው። ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም። ሥጋን ለራሱ ገንዘብ ቢያደርግም፤ በዚህም ደግሞ ከተዋሕዶ በምንም በምን አይናወጥም። ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም። መከፈል የሌለበትን አንዱን ሁለት እናደርገው ዘንድ አንከፍለውም። አንድ ወልድ አንድ ባሕርይ ነው ብለው እንደተናገሩት። ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር በልቡናችን እንደምናውቅ በነፍሳችን ዓይንም እንደምናይ መጠን ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋልና አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ገዢ፣ አንድ ወልድ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ እግዚአብሔር ቃል ነው እንላለን። 

      “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ሲያስብ፤ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው እንዲህም አለ፡- የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ እነሆ ድንግል ተፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል። የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይሁ ሁሉ ሆኗል። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ። እጮኛውን ማርያምን ወሰደ። የበኵር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም። ስሙንም ኢየሱስ አለው።” (ማቴ 118-25) ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችንን ልደት ለመናገር አስቀድሞ የተናገረው ጽንሰቱን ነው። ፅንሰት ልደትን ይቀድማልና። ስለፅንሱ ሲናገር ደግሞ እመቤታችን ጌታችንን የፀነሰችበትን ጊዜ በቤተ ዮሴፍ ሳለች መሆኑን ጨምሮ በመግለጽ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ ስለፅንሰቱ ሁለት ነገሮችን ብቻ መግለጽ እንደተቻለው ለመረዳት ይቻላል።

       አንደኛው፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ (እንዲጠብቃት፤ እንዲላካት፤ እንዲያገለግላት) የነበረች መሆኑን። ይህም ጥበብ የእግዚአብሔር ነውለ ፅንሱ ከመጀመሪያው በድንግልና መሆኑ ታውቆ ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ጌታን ያገኘ መስሎት ብዙ ፅንስ ሊያስወርድ ይችል ነበር። ምክንያቱም በኋላ ሰብአሰገል ሁለት ዓመት እንደተጓዙ ሲነግሩት፤ ከሁለት ዓመት በታች ያሉትን ሕፃናት በሄሮድስ አድሮ አስጨፍጭፏልና።

       ሁለተኛ፡- ቅዱስ ማቴዎስ ስለጌታችን ፅንስ የተናገረው ሌላው ዐቢይ ነገር ከዮሴፍ ጋር አለመገናኘቷን ብቻ ሳይሆን በግብረ መንፈስቅዱስ ፀንሳ መገኘቷን ብቻ ነው። እንዴት ሆና? ለሚለው ግን መልስ ሊሰጥ አልሞከረም፤ አይቻልምና። እንኳን እርሱ ቅዱስ ገብርኤልምመንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይል ይጸልልሻል። ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።አላት እንጂ እንዴት እንደሚከናወን መረዳት አልተቻለውም። (ሉቃ 135) ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ውጤቱን ወይም ክንውኑን እንጂ አሠራሩን የምንረዳበት ዐቅም የለንምና ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅየማይወሰነው (የሚወስነው ዓለም የሌለው) እርሱ በማሕፀንሽ እንዴት ተወሰነ? ዓለሙንም የያዘ እርሱ እንዴት በማሕፀንሽ ተሸከምሽው? በድንግልና ተፀንሶ ድንግልናዋ አለመለወጡስ እንደምን ያለ ነው? በማሕፀን ሲዋሐድስ ሥጋዋን ሁሉ እንደምን አልነሳም? እንዴትስ እርሱን አሳደገ? እርሱንስ እንዴት ተዋሐደ? እርሱ ከድንግል በፊት ነበርና።እያለ ሊመረምርና ሊነገር በማይቻል ባሕርዩን በመደነቅ ይገልጻል።

       ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችንን የተቀበለው ሊጠብቃት፣ ሊንከባከባት እንጂ ሚስት ትሆነው ዘንድ አይደለም። ይኸንም ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ገልጾታል። የዮሴፍም ጽድቅ የተገለጠው በዚሁ ምክንያት ነው። ምክንያቱም ለሚስትነት ወስዷት ቢሆን ኖሮ ከእርሱ እንዳልፀነሰች እያወቀ እርግዝናዋን ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም ነበር። እንኳን በግብር ሳያውቃት ቀርቶ በግብር ቢያውቃትም ፅንሱ ከእርሱ እንዳልሆነ ከጠረጠረ (በባልና በሚስት መካከል መቀናናት በተከሰተ ጊዜ፥ "የቅንዓት ሕግ" በተባለው መሠረት) በኦሪቱ ሥርዓት መሠረት ወደ ሊቃነ ካህናቱ ይወስዳታል፤ ጥርጣሪውንም ይናገራል። ካህኑም ወንዱ ይዞት የመጣውን የገብስ ዱቄትና ውኃ በቤተ መቅደሱ ካለ የዕጣኑ ዕራፊ ጋር ቀላቅሎ የሚጸልየውን ጸልዮባልሽ የጠረጠረሽን አድርገሽው ከሆነ፤ ሥጋሽ ይበጥ፣ ቁርበትሽ (ቆዳሽ) ይላጥ፤ አላደረግሽው እንደሆነ በወንድ ልጅ ተበከሪብሎ ይሰጣታል። እርሷም መርገሙ ይደረግብኝ በረከቱ ይሁንልኝ ብላ ትጠጣዋለች። (ዘኍ 511-31) ዮሴፍ ግን ይኸን በሕግ የተፈቀደውን ያላደረገው መጀመሪያውኑ ሊጠብቃት፤ ሊያገለግላት የተቀበላት በመሆኑ ነው።

       ይሁን እንጂ ዮሴፍ ጭንቀት አልቀረለትም። ከመጨነቁም የተነሳ ከሁለት ነገሮች በአንዱ ላይ መወሰን ተስኖት በአሳብ ይዋዥቅ ነበር። ወደቆጠራው ይዟት እንዳይወጣልትጠብቃት ሰጥተንህ ለምን እንዲህ አደረግህ?” ተብሎ ቢጠየቅና የእርሱ አለመሆኑን ቢናገር እርሷን እንደ ሕጋቸው በድንጋይ ወግረው፣ በእሳት አቃጥለው ይገድሉብኛል ብሎ ተጨነቀ። ትቷት ቢሄድም ያደረገውን ዐውቆ ወደ ቆጠራ ሳይዛት መጣ የሚሉ ከሳሾችን ፈራ። በእነዚህ በሁለቱ ሲጨነቅ፣ ሲያወጣ ሲያወርድ፣ ሲፈራ ሲቸር መልአኩ በሕልም አነጋገረው። ወንጌላዊውእጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።ያለው ይኸንኑ ለመግለጥ ነው።

       የዮሴፍም ጽድቅ የወንጌል እንጂ የኦሪት አይደለም። ዮሱፍ ግን በግብር ፈጽሞ ስለማያውቃት ሆኖ ሳለ እንኳ ሊተዋት ነገሩን ላገልጥባት አስቧልና። ይኸም በወንጌል ያለ፤ ከባቴ አበሳነት ነው። ስለዚህ ዮሴፍ ጻድቀ ወንጌል እንጂ ጻድቀ ኦሪት አይባልም። ዮሴፍ በዚህ ግብሩ ጻድቅ ቢሆንም ለቆጠራው የሚያደርገው አስጨንቆት ነበር። መልአኩ በሕልም ተገልጦየዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።ያለውም ለዚህ ነው።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከመናገሩ በፊት በሥጋ ብእሲ መገለጡን ለማስረዳት ከአብርሃም በመነሳት የሌሎቹን ልደት እየተናገረ መጥቷል። ስለልደታቸው ሲገርም ፍፁም ዕሩቅ ብእሲ መሆናቸውን በመግለጥ ነው። ይኸውምአብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤…” በሚለው አገላለጽ ነበር። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ እናታቸውንም ይገልጻል።ንጉሥ ዳዊት ከኦርዮን ሚስት ሰሎሞንን ወለደእንዳለ። ልደተ.እግዚእን ሲገልጽ፦ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናል እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።” (ማቴ. 21) አለ። ቅዱስ ማቴዎስ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሲገልጽ በቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን መወለዱን አውስቷል። የቤተልሔምንና የሄሮድስን ስም ለምን ማንሳት አስፈለገው? ቢሉ፦

       1 የተናገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ ለመከተል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ስለ ጌታ መወለድ የጻፈው በነቢያት ስለቤተልሔም የተነገረውን ትንቢትና በኦሪት የተመሰለውን ምሳሌ በማስታወስ ነው። ትንቢቱምወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉሥ ዘይርእዮም ለሕዝብየ እስራኤል፤ አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና።የሚል ነው። ምሳሌው ደግሞ ካሌብ ምድረ ርስትን ሰልሎ ሲመለስ ኬብሮንን አይቶ መጥቶ ኢያሱን ኬብሮንን ስጠኝ ቀድሞ ሙሴ ሰጥቶኝ ነበር። (ሚክ 52) ምንም እንኳን 80 ዓመት ሽማግሌ ብሆንም ከአንተ ጋር መውጣት መውረድ የሚያስችለኝ ጉልበት አለኝ። ብሎ ከኢያሱ ኬብሮንን ወሰደ። እርሷን እጅ አድርጎ አዙባ የምትባል ሴት አገባ። ከጠላቶቹ ወገን ነበረችና በእርሷ ስም አልጠራትም። ቀጥሎ ከብታ የምትባል አገባ፤ በከብታ ከብታ ተባለች። እንደገናም ኤፍራታ የምትባልም ሲያገባ ኤፍራታ ተባለች። ካሌብ ወንድ ልጅ ከሷ በወለደ ጊዜ እንጀራ እገባ እገባ ብሎት ስለነበር (ሀብት ስላገኘ) የልጁን ስም ልሔም (ኅብስት) አለው። በልሔም ቤተ-ልሔም ተብላለች።

                                  ይህም ምሳሌ ሲብራራ-

      * ከብታ ማለት ቤተ-ስብሐት ማለት ነው። ቤት የእመቤታችን ስብሐት የጌታችን። ኤፍራታ ማለት ጸዋሪተ ፍሬ (ፍሬ የምትሸከም፤ የሚዘይዝ) ማለት ነው። ጸዋሪት የእመቤታችን፤ ፍሬ የጌታችን ምሳሌ ነው።

        * ቤተ-ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ሲሆን ቤት የእመቤታችን ኅብስት (ልሔም) የጌታችን ምሳሌ ነው። ከቤተልሔም ኅብስት እንዲገኝ ከእመቤታችንም ለሰው ልጅ እውነተኛ ደሙንና ክቡር ሥጋውን የሰጠው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል።

       2አንቺ ቤተልሔምብሎ ስለቤተልሔም መገለጹ ስለማይቀር ቤተልሔምን አነሣ። ሌላኛው ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያው ምዕራፍ ትኩረት የተሰጠው ከጌታ መወለድ ጋር የሄሮድስ ስም አብሮ መነሳት ነው። ይኸውም፦

      * በጌታ መወለድ ምክንያት የተደናገጠው ሄሮድስ በቤተልሔም የሚገኙ ሕፃናትን መግደሉን ስለሚገልጽ ማቴዎስ ሄሮድስን አስቀድሞ ማስታወሱ ነው።

        * በእስራኤል ልምድ ትውልድ እና ዘመን የሚቆጠር በንጉሥ ነውና የሄሮድስን ስም አነሣ።

       * በንጉሥ ሄሮድስ ላይ ሰማያዎ ንጉሥ ተወለደ፤ እግዚአብሔር ክርስቶስ ተወለደ ለማለት ሄሮድስን አነሳው። በዚህም ከቤተ ይሁዳ ንግሥና አይጠፋም ተብሎ የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን ለማጠየቅ ነው። ከዚያው ከቤተልሔም ሳሉ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። የእንግዳ ማረፊያ ቢያጡ ከከብቶች በረት ዮሴፍ ዳስ ጥሎላት በሴቶች የሚደርሰው ሳይደርስባት ሕማመ ምጽ (የምጥ ሕማም) ሳይሰማት ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወልዳዋለች።እምሀበ አብ ወጽዓ ቃል ዘንበለ ድካም ወእም ድንግል ተወልደ ዘንበለ ሕማም፤ ከአብ ዘንድ ያለድካም ወጣ ከድንግልም ያለሕማም ተወለደእንዲል (ቅዱስ ኤፍሬም)

       ልደቱን ያለዘርዓ ብእሲ ያደረገው ለምንድን ነው? ቢሉ ቀዳማዊ ልደቱን ለመግለጽ ነው። ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለአባት መወለዱን ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያጠይቀናልና።ልደተ ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደት፤ የቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀእንዲል። አንድም የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድም ነው፡ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ፤ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለችተብሎ ተነግሯልና። (ኢሳ 714) ይህም አዳም ከኅቱም ምድር ተገኝቷል፤ ሔዋንም ከኅቱም ገቦ ተገኝታለች። ይህም ጌታ በኅቱም ማኅፀን ለመወለዱ ምሳሌ ነው።በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀእንዲል (ኢሳ 13) እንስሳት ጌታቸውን አውቀው እስትንፋሳቸውን ገብረውለታል። ቁረ ሌሊቱን ለመግለጽ ነው። በሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞች ነበሩ። መልአኩ መጥቶ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።አላቸው። (ሉቃ 210-12) ከሡም ጋራ ሠራዊተ መላእክት መጥተውስብሐት ለእግዚአብሔር በሠማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለእመሕያው፡ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ፤ የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር።” (ሉቃ 213-19)

         መላእክትም ሠማይ መንበሩ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆኑለት አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በጎል ተኝቶ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተውት ደስ ብሏቸው ወደሠማይ ቢያርጉ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በዕሪና ከመንበሩ አይተውትስብሐት ለእግዚአብሔር በሠማያትብለው አመስግነውት በጣዕም ላይ ጣዕም፤ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋል። ልደቱን ይሹታልና፤ መላእክትም ብቻ አይደሉም እንስሳትም አራዊትም ደስ ብሏቸዋል። ይህም ሊታወቅ አንድ ባሕታዊ ቋርፍ ሲምስ ምዳቋ ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም ዮም ተወልደ ከሣቴ ብርሃን እያለች ስትዘል አይቷል። በልደቱም የባሕር ውኃ ወተትና ማር ተራሮች እንጀራ እንጨቶችም የበረከት ፍሬ ሆነዋል።በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ.ሕይወት ወዕፀ.ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት ማየ.ባህርኒ ሞነት ሐሊበ ወመዓረእንዲል ቅዱስ ያሬድ።

        ልደቱንም በኮከብ ተረድተው ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ስማቸውም ማንቱሲማር፣ ሜልኩ በዲዳስፋ የተባሉ የፋርስ ነገሥታት ከገነት የተገኘ ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ገብረውለታል። ከምን አገኙት? ቢሉ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ሰጡት። እርሱ ለሔዋን ሰጣት። ሔዋን ለሴት ሰጠችው። ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደረሰ። ኖኅ ከመርከብ ከወጣ በኋላ ለሴም ሰጠው። ሴም መልከጼዴቅን አስጠበቀው፤ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ሰጠው። ከአብርሃም ሲወርድ ሲዋረድ በዳዊት በሰሎሞን አድርጎ ከአካዝ ደረሰ። በሱ ዘመን ቴልጌልፌልሶር ማርኮ ወስዶ ከቤተ.መዛግብቱ አኑሮታል። አባታቸው ዥረደሽት ይባላል፤ ፈላስፋ ነበር። አንድ ቀን በቀትር ከውኃ ዳር ሆኖ ሲላሰፍ በሰሌዳ ኮከብ ድንግል ሕፃን ታቅፋ አየ። ያየውን በሰሌዳ ቀርጾ አስቀመጠው። ሲሞት ልጆቼ እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ይህን ወስዳችሁ እጅ ንሱ ብሎ ሰጥቷቸዋል። አንድም በለዓምከያዕቆብ ቤት ኮከብ ይወጣልያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። (ዘኅ 2017) አንድም ትሩፋን በባቢሎን ሳሉ ነገሥተ ተርሴስ ወደ ስያት ስጦታ (ገጸ በረከት) አመጡ፤ ንግሥተ ሳባ ወዓረብ እጅ መንሻ ያመጣሉ እያሉ ሲጸልዩ ይሰሙ ነበረና ይኸን ይዘው መጥተዋል። አንድም ባሮክ አቴና ወርዶ ነበር። ያን ጊዜ ዛሬ የሀገራችሁን ንጉሥ የሚገብረውን ወርቅ ኋላ ከእኛ ወገን ንጉሥ ሲወለድ ይገብረዋል ብሎ የነገራቸውን ይዘው ነው።

        የተወለደ ዕለት ኮከቡን አይተው አባታችን የነገረን ደረሰ ብለው 12 ሆነው ሠራዊቶቻቸውን አስከትለው ተነሱ። ብዙም ሳይርቁ ጠላት ተነስቶባቸው ዘጠኙ ተመለሱ። እኒህ ሦስቱ ግን ኮከቡ እየመራቸው ኢየሩሳሌም ደርሰው በሄሮድስ በኩል አድርገው ቤተልሔም ወርደው አግኝተው ገብረውለታል። ምሥጢሩም፡-

       ፩፦ ወርቅ መገበራቸው፡ ይኸን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ነህ፤ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ እንዲሁም በአንተ ያመኑ ምዕመናንም ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው። የሃይማኖት ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና።

፪፦ ዕጣን መገበራቸው፡ ይኸንን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። አንድም ዕጣን ምዑዝ ነው፤ አንተም በባሕርይ ምዑዝ ነህ ሲሉ እንዲሁ ደግሞ በአንተም የሚያምኑ ምእመናንን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ዕጣን የተስፋ ምሳሌ ነው። ዕጣን ከሩቅእንዲሸት ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና።

       ፫፦ ከርቤ መገበራቸው ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ በኋላም የማታልፍ ብትሆንም በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ አንድም ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ። አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት። ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው። በፍቅር አንድ ይሆናሉና። ከርቤ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ አንድ እንዲያደርግ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና። በአጠቃላይ ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ እጣን ከርቤ የገበሩለት ሃይማኖት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ነው። በሌላ መልኩ ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለመለኮቱ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ ናቸው።

       እጅ ነስተው ከወጡ በኋላ አንዱ እንዴት ያለ ሽማግሌ ነው ብሎ አደነቀ። ሁለተኛው የምን ሽማግሌ ጎልማሳ ነው እንጅ አለ። ሦስተኛው ደግሞ ሕፃን ነው እንጂ አለ። ገብተን እንይ ተባብለው ቢገቡ ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ፤ ጎልማሳ መለስሎ ለታየው ሕፃን፤ ሕፃነ መስሎ ለታየው ሽማግሌ መስሎ ታያቸው። ወጥተው እንዳንተ ነው እንዳንተ ነው ይባባሉ ጀመር። መልአኩ መጥቶ እንደሁላችሁም ነው አላቸው። በጆሮ የሰሙትን በዓይን ቢያዩት ይረዳል ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ገቡ። ሽማግሌ ጎልማሳ መስሎ ለታየው ሕፃን፤ ጎልማሳ ሕፃን መስሎ ለታየው ሽማግሌ፤ ሕፃን ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ መስሎ ታያቸው። እጹብ እጹብ ብለው አመስግነው፤ አምላክነቱን ተረድተዋል። በሚሄዱበትም ጊዜ እመቤታችን የገብስ እንጀራ ጋግራ ሰጠቻቸው። ሀገራቸው እስኪገቡ ድረስ ከሠራዊቶታቸው ጋር (እያንዳንዳቸው አስር ሺህ፤ አስር ሺህ ሠራዊት) ሲመገቡ ቆይተው ከከተማቸው ሲደርሱ ይህን ቅዱስ ምግብ ከከተማችን አናስገባም ብለው ከከተማው በር ቀብረውት ገቡ። ደርሳችሁ መጣችሁን? አሏቸው። አዎን በአርባ ቀን መጣነው፤ እናቱም የሰጠችንን የገብስ እንጀራ እኛ እና ሠራዊቶቻችን ስንመገበው መጥተን ከከተማችን አናገባም ብለን ከከተማው በር ቀብረነዋል አሏቸው። አሳዩን አሉ። ተያይዘው ቢሄዱ ሲጨስ አግኝተውታል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወድንግል ማርያም!

መልካም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ይሁንልን!!!
---------------------------- // -----------------------------
ምንጭ፦ [የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ሰ/ት/ቤትመንፈሳዊ ድረ ገጽ]







No comments:

Post a Comment