Monday, January 19, 2015

እኛ የምንጠመቀው ጥምቀት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

እኛ የምንጠመቀው ጥምቀት በኹለት ታላላቅ ክፍል ይከፈላል፦

፩ኛ፦ ጥምቀተ ኦሪት (ጥምቀተ ንስሐ)
፪ኛ፦ ጥምቀተ ወንጌል (ጥምቀተ ክርስቶስ)

፩ኛ፥ ጥምቀተ ንስሐ

የኦሪት ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር፤ አንድ ሠው የኦሪትን ሕግ ተላልፎ ኃጢአት የሰራ  እንደኾነ ሲመለስ በውኃ ይጠመቅ ነበር። (ዘሌ ፲፭፥፰)። አንድ አሕዛብ በኦሪት ወደ አይሁዳዊነት ሲገባ ይህን የንስሐ ጥምቀት ይጠመቅ ነበር፤ (ማቴ ፫፥፲፩)። እሥራኤል ባሕረ ኤርትራን መሻገራቸው ጥምቀታቸው ነበር። (፩ኛ ቆሮ ፲፥፪)።

መጥምቁ ዮሐንስ ሲያጠምቀው የነበረው ጥምቀት የኦሪቱ የንስሐ ጥምቀት ነበር (ማቴ ፫፥፲፩)። የጌታም ደቀ መዝሙርት ይህን የንስሐ ጥምቀት አልፈው አልፈው አጥምቀዋል፤ በዚህ ጥምቀተ ንስሐ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ቄደር ገብቷል። አሁንም ይሠራበታል በማለት ይቻላል፤ አላማው ያው ጥምቀተ ንስሐ ነው። አዲሶች አማንያን ለዐቅመ አዳምና ሔዋን ከደረሱ በኋላ ንስሐ ገብተው፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ለመጠመቅ ሲፈልጉ፣  በመጀመርያ  የሚጠመቁት ይህን ጥምቀተ ቄደር (የንስሐ ጥምቀት) ነው። ያለፈው ኃጢአታቸው በዚህ ጥምቀተ ቄደር እንዲነፃ ነው። ሕፃናት ግን ኃጢአት ስለሌለባቸው የንስሐ ጥምቀት ሳይጠመቁ፣ የልጅነት ጥምቀት ብቻ ይጠመቃሉ። ከአመኑ፥ ከተጠመቁ በኋላ ብዙ ኃጢአት ሲሠሩ የኖሩ፣ ክርስቶስን ክደው በአረማዊነት፣ በእሥልምና፣ በአምልኮ ጣዖት የቆዩ  ሠዎች እንደገና አምነው በንስሐ ሲመለሱ ጥምቀተ ቄደር ይጠመቃሉ፤ ይህም ጥምቀተ ቄደር ይደገማል።

ኃጢአተኞች ይህን ጥምቀት የሚጠመቁት ፣ ለቀሳውስት ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ነው። ይህም ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ሲያጠምቅ ሕዝቡ ከእሱ የሚጠመቁት፥ በመጀመርያ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙለትና እየተናገሩት ስለነበር ነው። (ማቴ ፫፥፩-፯፣ ፫፥፲፩) ሐዋርያትም ሲያጠምቁ፥ የሚያጠምቋቸውን ሠዎች እንዲያምኑ፣ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ንስሐ እንዲገቡ ይጠይቋቸው ነበር። (ዮሐ ፩፥፳፰፤ ሐዋ ፳፮፥፳)።

፪ኛ፥ ጥምቀተ ክርስቶስ

ጥምቀተ ክርስቶስ ወይም የልጅነት ጥምቀት የሚባለው፦ ክርስቶስ ለሊቆዲሞስ ያስተማረው፣ ሐዋርያት እንዲጠመቁ ያዘዛቸው፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። (ማቴ ፫፥፲፩፤ ዮሐ ፫፥፩-፲፪)።

ይህ የክርስቶስ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን ያሰጣል (ያስገኛል)፣ መንግሥተ ሠማያትን ያስገባል፣ ኃጢአት ያስተሰርያል፤ (ሐዋ ፪፥፴፰)። ይህ የልጅነት ኹለተኛ ልደት ተብሎ  ተተርጉሟል፤ (ዮሐ ፫፥፭-፯፤ ቲቶ ፫፥፭)። ይህ የክርስቶስ ጥምቀት እንደ ጥምቀተ ቄደር አይደለም፤ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚፈጸመው። ምክንያቱም፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <<ጥምቀት አንዲት ናት>> ስለ አለና መቅዶንዮስን በቁስጥንጥንያ ጉባኤ ያወገዙት ፩፻፶ ሊቃውንትም <<ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት /በአንዲት ጥምቀት እናምናለን>> ብለው ስለወሰኑ ነው። (ኤፌ ፬፥፭-፮) ዮሐንስ አፍወርቅም በ፲፫ኛው ተግሣጹ ጥምቀት አንዲት ናት እንጂ ኹለተኛ ጥምቀት የለም ብሎ የጻፈው ስለ ልጅነት ጥምቀት አለመደገም ሲያስረዳ ነው።
 ----------------------------------------------------------------------
 ምንጭ፦ በየጥቂቱ (ጥቂት በጥቂ) አደገ በ፴ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ገፅ ፴፩-፴፪፤ አዲስ አበባ ጥር ፲ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ከታተመ መጽሐፍ
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ፦ "በዓለ ጥምቀት፤ ምሳሌውና ምስጢሩ" በሚል (ሰባኪ ወንጌል ዘ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው የተሰጠ መንፈሳዊ ትምህርተ ወንጌል ሰምተውና አዳምጠው ስጋዎትንና ነፍሶትን ይመግቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዘዋል።




 

Tuesday, January 6, 2015

ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ (በምሥጢረ ሥጋዌ አስተምህሮ)


                 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

      ተሠገወ፡- ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህሥጋዌሰው መሆንን፣ መገለጽን (በተአቅቦ) መግዘፍን፣ መወሰንን፣ መዳሰስን ያመለክታል። ቀድሞ ምን ነበር? ወይም ማን? ለሚለው ጥያቄ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልበመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ.11) ሰው የሆነም አካላዊ ቃል እንደሆነቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ።በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐ.114) ሰው የሆነውም በተዋሕዶ ነው። ይኸውምአንድ ጊዜ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነውበማለት ነው። ምሥጢረ ሥጋዌ የአብ አካላዊ ቃል ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል ሰው የሆነበት፤ ሰውንም ያዳነበት መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ማለት ነው።
 
      ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) የለም። ሞትን በቀመሰ ጊዜም መለኮት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም። በዚህም ምክንያት ሞቱ እንደሌሎች ፍጡራን ወይም እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የማይታይ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስእርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፤ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።ሲል ገልጦልናል። (ዕብ. 214) በመሆኑም ሲራብም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲተኛም፣ ሲነሳም፣ ተዓምራት ሲያደርግም፤ በአንድ ባሕርይ ጸንቶ እንጂ እንደ ማየ ግብጽ በሚጠት አንድ ጊዜ አምላክ አንድ ጊዜ ሰው እየሆነ አይደለም።

        ሰው የሆነውም እንደ ወይነ ቃና እና እንደ ብእሲተ ሎጥ (የሎጥ ሚስት) በውላጤ (በመለወጥ) እንደ መስኖ ውኃ በኅድረት፤ ሳይሆን ተአቅቦ ባልተለየው ተዋሕዶ ነው።የሰውን ሥጋ ነሥቶ ቢዋሐድ እንጂ ሥጋንማ ባይነሳ እንደምን ሰው በሆነ ነበር፤ ነፍስን ሥጋን መዋሐዱም መለወጥ፤ መቀላቀል ፤መለየት በሌለበት የሁለቱን ባሕርያት አንድነት እነደፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ አንድ አደረገ። ሥጋ ሥጋ ነውና፤ መለኮት አይደለም። እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ቢሆንም ቃልስ አሁን አምላክ ነው። ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም። ሥጋን ለራሱ ገንዘብ ቢያደርግም፤ በዚህም ደግሞ ከተዋሕዶ በምንም በምን አይናወጥም። ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም። መከፈል የሌለበትን አንዱን ሁለት እናደርገው ዘንድ አንከፍለውም። አንድ ወልድ አንድ ባሕርይ ነው ብለው እንደተናገሩት። ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር በልቡናችን እንደምናውቅ በነፍሳችን ዓይንም እንደምናይ መጠን ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋልና አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ገዢ፣ አንድ ወልድ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ እግዚአብሔር ቃል ነው እንላለን። 

"በዓለ ልደት" ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ

                                                                              (ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም) ያስተማሩት።

 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

                         የተወደዳችሁ ምእመናን! እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ።

ጋድ (ገሃድ) እና ገና፥ ልደቱ ለእግዚእነ። (ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ/ም)

            «ጾመ ገሃድ (ጋድ)፦ የቃሉ ትርጕም «ገሃድ» ሲል መገለጥ፥ «ጋድ» ሲል ለውጥ ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት፦ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ በዓል በሳምንት ሁለት ቀን በምንጾምባቸው ጾም በተሠራባቸው በረቡዕና በዓርብ የዋለ እንደ ሆነ የጾሙ ሥርዓት ሳይጠበቅ፤ ፩ኛ፤ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ለ፳፱ አጥቢያ፤ ፪ኛ፤ ጥር ፲ ቀን ለ፲፩ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ቅዳሴ እንዲፈጸምና ምእመናን በትንሣኤው የአከባበር ሥርዐት ዐይነት በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ አዝዘዋል። ስለዚህ ሁለቱም ማለት የልደት፥ የጥምቀት ዋዜማ በጾም እንዲታሰብ ሆኗል።

           በአንድ በኩል የጌታን መገለጥ የምናስብበት ነው። መገለጥ ሲባልም እንደ በዓላቱ ጠባይ ሁለት ነው። በልደት መገለጥ ሲባል ሰው ሆኖ የማያውቅ አምላክ በሥጋ ሰው ሆኖ በአጭር ቁመት፥ በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለ ተገለጠና ሰዎች ሊያዩት ሊዳስሱት ስለ ቻሉበት ነው።

        በጥምቀት መገለጥ መባሉ፤ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ ፴ ዓመት ዕድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲሕ፥ ሰው የሆነው አምላክ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኋላ በ፴ ዓመት ዕድሜው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፤ አብ፤ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት፤» ብሎ በሰጠው ምስክርነት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት የተነበዩለት የሰው ልጆች መድኃኒት ሥግው አምላክ ማለት ሰው የሆነ አምላክ እሱ መሆኑ ስለ ተገለጠበት ነው። ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ ቅዳሜ፥ እሑድ ቢሆን በሰንበት ጾም ስለ ሌለ ሥርዓተ ጾሙ ከጥሉላት ምግብ በመከልከል ብቻ ይፈጸማል።» [የጽድቅ በር፤ ፲፱፻፸፱ ዓ ም፤ ገጽ ፳፯ - ፳፱።]

        «ልደቱ ለእግዚእነ። ይህ በዓል ሰውን በመልካችን በምሳሌአችን እንፍጠር ብሎ በጥንተ ፍጥረት የተናገረ እግዚአብሔር ቃል የሰውን ልጆች ለማዳን፤ «አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ።» «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ እመጣለሁ፤» ሲል በሰጠው ተስፋ፤ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ያለ አባት የተወለደበት ነው። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ግዚአብሔር ቃል ወልደ አብ ድኅረ ዓለም ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም መወለዱና ወልደ ማርያም መባሉ ለሰው ልጆች ክብርና ሕይወት ስለ ሆነ፤ ሥጋ ቃልን ተዋሕዶ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ከሰማያውያን መላእክት፥ ከምድራውያን ኖሎት (እረኞች) ምስጋናን በግልጥ የተቀበለበትን፥ ለሰው ልጆች ዕርቅ የተመሠረተበትን ይህንን ታላቅ በዓል ኢትዮጵያ ከዓለም ክርስቲያኖች ጋራ በመተባበር ታከብረዋለች። (ዘፍ፤ ፲፰፥ ፲። ሉቃ፤ ፪፥ ፲፫ - ፲፱።)

       መሠረቱም፤ «እነሆ በኤፍራታ በጎል ተጥሎ፥ በጨርቅ ተጠቅልሎ አገኘነው፤ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው፤ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተን የጌታችን እግር ከቆመበት እንሰግዳለን፤» የሚለው ትንቢታዊ ቃል ነው። (መዝ ፻፴፪፥ ቍ ፮ እና ፰።) [የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤ ገጽ ፪፻፴፭]

(ክቡር አባታችን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ በዓለ ልደትን በማስመልከት ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ያስተላለፉንት መንፈሳዊ ትምህርት ነው። በተጨማሪም፦ በስማቸው የተሰየመውን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩን መንፈሳዊ መጦመርያ ይጎብኙ (ለአባታችን፥ ለሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ፦ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፤ ጸጋ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!!!)