Friday, October 2, 2015

በመልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙ ላይ ማጉረምረም ለምን? ክፍል ፫



በክፍል ሁለት ላይ ያቆምነው፦ «ስለ ከንቱ ውዳሴ እና ከከንቱ ውዳሴ ስለ ለማምለጥ» ነው፤ ካቆምንበት ስንቀጥል፦ እርግጥ ነው ማንኛውም ምዕመን ውዳሴ ከንቱ ከመስጡት መቆጠብ አለበት፣ እንዲሁም ደግሞ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልጋይ ስለ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሲል ከውዳሴ ከንቱነት እራሱን መጠብቅ ግድ ይላል!፤ ይህ ታዲያ የሚሆነው በምዕመናን ዘንድ ይሁን በአገልጋዮች ዘንድ የመንፈሳዊነት ልዕልና ሲኖር ነው። በዚሁ «ስለ ከንቱ ውዳሴ እና ከከንቱ ውዳሴ ስለ ለማምለጥ» ስንነጋገር መምህር ግርማ፦ «እኔ አዳኝ አይደለሁም፥ ነኝ ብዬ ተናግሬ፣ ተመፃድቄም አላውቅም፤ አገልግሎት እየሰጠሁ እንጂ! የሚፈስና የሚያድው እግዚአብሔር አምልክ ነው!።» ያሉትን እናስታውስ።

ደግሞም ሁሉም መምህራን፥ ስለ መተተኞች፣ ስለ ጠንቋዮች፣ ስለ ድግምታሞች፣ ስለ ዛር መንፈሶች፣ አጠቃላይ ስለ አጋንት ሥራዎች መኖር ያውቃሉ፤ ስለነዚህ የአጋንት ሥራዎች እንዴት ማስቀረትና ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደሚመልስ በትምህርታቸው ውስጥ ይሰጣል፤ ቢሆንም ግን አሁን ስለምንነጋገርበት ወደ ጠንቋይና ወደ ቃልቻ ቤት የሚሄደንው፣ ሥራውን በመተትና በጥንቆላ የሚተዳደረውን ወደ እግዚአብሔር ቤት ፊቱን እንዲመልስ እያደረጉ ያሉትን አባት መምህር ግርማን መቃወም ምን የሚሉት ነገር ነው? ደግሞስ እኚሁ አባት፥ ካህናት መብላት ያለባችሁ ቅልጥም ጠንቋዩ እንዳይበላው፣ ካህናት መጠጣት የነበረባችው ጠጅ ጠንቋዩ  እንዳይጠጣው፣ ሕዝቡን እየሰኩ እያስቀሩ፣ ሕዝቡን ፍትፍቱን ወደ ጠንቋይ ቤት መውሰዱን እንዲያቆም እና ወደ ካህኑ እንዲያመጣው እያደረጉ ያሉ አባት ናቸው። ቤተ ክርስቲያንንም በማሳነጽ ረገድም የበኩላቸውን ድርሻ እያደረጉ ነው። እንደውም ስለ ቤተ ክርስቲያንን ማሳነጽ መጋቢ አእላፍ መክብብ አጥናው ያሉትን እናጢነው።

Wednesday, September 30, 2015

በመልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙ ላይ ማጉረምረም ለምን? ክፍል ፪



እኔ ታናሽ ብላቴና ይህንን ጹሑፍ እንዳዘጋጅ ያነሳሳኝ ነገር ስለ  ሦስት ዓበይት ነገር ነው።

አንደኛ፦ ከአንድ ዓመት አምስት ወር በፊት የምንወድው ውዱ ወንድማችንና መምህራችን ቀሲስ ሕብረት የሺጥላ «አጋንንትን ከሰዎች የማስወጣት ሥርዓት» በሚል ባስተማረው ትምህርት በዚህ ትምህርትህ ላይ መምህራችን ስም ሳይጠቅስ (ስለ መልአከ መንክራት ግርማ ወንዱ ያስተማረው ትምህርት እንደሆነ ነው በቀጥታ የተመለከትኩት።)

ኹለተኛ፦ በፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ የሚመራው መለከት የተባለ ሬድዮ ያሰራጨው የሐሰት ዶሴና ክስ፤ ጲላጦስና ሄሮድስ የማይስማሙ ኾነው ሳለ ክርስቶስን አሳልፈው ለመሰጣጠት ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ሲሉ አንድነታቸውን አበረቱ፤ እንዲሁም ደግሞ መልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙ ለማሳደድ አንዳንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጉያ ከተሰገሰጉ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጋር በማበር ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ሲሉ አንድነታቸውን አበረቱ፤ ሲያብሩ አየን፤ ሰማን።

እነዚህ አንዳንድ ዘለባብዳን /ዘለባጆች "መለከት ሬድዮ" በተባለ በድምፅ ማሠራጫ ባስተላለፉት የድምፅ ማዕደር የወንጌል ሥራ ከእኛ ጋር የሚሰሩ የተባሉ፤ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጉያ ከተሰገሰጉ ፕሮቴስታንት ተሐድሶ ከኾኑት ከእነ አቶ ጽጌ ስጦታው፣ ከእነ አቶ ሙሴ መንበሩ ጋር (እነዚህ በይፋ የተወገዙና የተለዩ ቢኾኑም ሌሎች ያልተወገዙና ያልተለዩ አሉ) መረቡን የዘረጋው ፕሮቴስታንታዊው ተሀድሶ ቡድን ነው፤ ይሄ ቡድን የተለመደውን መዘለባበጃቸውን ለይስሙላ በመልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙን በማነጣጠር፣ የመምህር ግርማ ወንዱሙን መንፈሳዊ አገልግሎታቸውንም እንነቅፋለን ቢሉም ቅሉ ግን አጠቃላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ዶግማንና ቀኖናን ያነጣጠረ ነበር። ይሄም፥ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አባቶችን፣ ቅዱሳት መላእክትን፣ ጻድቃንን፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን በማንቋሸሽና በማጥልሸት፤ የተለመደው የኑፋቄ መርዛቸውን ሲረጩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ጠቢቡ ሠለሞን በምሳሌው፦ "በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።" /ምሳ 1019/ ብሎ እንዳዘዘን፤ እኛም ከንፈራችን የተባለው፥ አንደበታችን ሰብስበን፤ ይሄንን የድምፅ ማዕደርን በመስማት እውነቱን እንወቅ!።

Monday, June 29, 2015

ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና፣ ድንግልና፣ ቃል ኪዳንና አማላጅነት በሰፊው የታወቀ ነው።

ቅድስናዋ

አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፤ /ኢሳ.19/ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ጸጋን ሁሉ የተሞላች ብፅዕት ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡ /መኃ 47 ሉቃ 126-44/ ጸጋን ሁሉ የተመላች፣ ብፅዕት፣ ከተለዩ የተለየች፣ ቡርክት፣ ንጽሕት፣ ቅዱስተ ቅዱሳን ስለሆነችምምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽተብላ በቅዱሳን መላእክት አንደበት በቅድስናዋ ተመስግናለች፤ ትመሰገናለችም። /ሉቃ 128-30/

እመቤታችን፥ በውስጥ በአፍኣ፣ በነፍስ በሥጋ፤ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል። ማኅደረ መለኮት እንድትሆን አድርጓታል። አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ፣ ንጽሕናዋ ነው። /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፤ መዝ 13213/ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።

----------------------------------------------------------------------------

Friday, June 5, 2015

ሠዓቱ ስንት ነው? ቀሲስ ደረጀ ሥዩም



                      (ከሰባኪው ማስታወሻ በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በኅትመት ላይ ካለ መጽሐፍ የተወሰደ።)

*********ዮሐ. 316 “እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፡፡ እኛም ስለወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል፡፡ብዙ ጊዜ የሚጎዳን ሰው ያደረገብን አይደለም፡፡ ሰዎች ላደረጉብን ነገር የምንሰጠው ምላሽና የበቀል ስሜት የበለጠ ይጎዳናል፡፡ ከምንወዳቸው ስዎች ጋር ከኖርንበት ዘመን ይልቅ ከምንጠላቸው ሰዎች ጋር የምንኖርበት ዘመን ይበዛል፤ ምክንያቱም የምንወዳቸውን ሰዎች ለማግኘት ቀጠሮ ያስፈልጋል። ይቅርታ ያላደረግንላቸው ጠበኞቻችንን ግን ሁል ጊዜ ለበቀል ስልምንፈልጋቸው ስንበላ በምግቡ ውስጥ አሉ፣ ስንተኛ ምኝታችን ላይ ይመጣሉ፣ ስንጸልይ እንኳን በጸሎት ውስጥ ብቅ ይላሉ። የእግዚአብሔር ቃል ግንክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፋ አትሸነፍ፡፡ይላል። (ሮሜ 1221)**********

“ ….ግጭት ሁሉ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም፤ እንዲሁም አብረን እየኖርን ግጭትን ማስቀረት አይቻልም። ቤተክርስቲያን ነን ካልን ግጭትና ፈተና ይጠፋል ብሎ መገመት የዋህነት ነው። ችግሩ የግጭቱ መኖር ሳይሆን የግጭት አፈታት ብስለት ማጣታችንና ለታላቁ ተልዕኮ ስንል በቁጥጥር ሥር ማዋል አለመቻላችን፣ ወይንም አለማወቃችን ነው። ይህ ማለት ችግሩን ማስቀረት ባይቻልም ችግሩ ሲከሰት ግን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ችግሩን የምንፈታበት ጥበብ ሊኖረን ይገባል።*******
ቀሲስ ደረጀ ሥዩም

“…እኛም የምንቀርብበት ሌላ ችሎት የለንም። ቃሉ የመዳኘት ሥልጣን ያለው ነው። የሥነ-ምግባር የአስተምህሮና የሰይጣን ፈተና የተመለሰው በቃሉ ሥልጣን ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ከዓለምና ከዓለማውያን ጋር ማድረግ የሚገባት ትብብርና ስምምነት ሊኖር አይገባም። ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች ዛሬ እንደጊዜው ይኖራሉ። ለመንፈሳውያኑምየጊዜውን መንፈስ ውሰዱና እንደጊዜው ኑሩይላሉ። ቤተክርስቲያን በሊቢራሊዝም በሌጋሊዝም በኢሞራሊቲ፣ በማቲሪያሊዝምና በድምፅ አልባ ዶክትሪኖች ተከባ በመንገዳገድ ላይ ትገኛለች። ከራሷ ውስጥ በተነሱ መንፈስ ቅዱስ ያልነካቸው አገልጋዮች፥ የሥልጣን ጥመኞችና ፍቅረ ነዋይ ባሰከራቸው ትታመሳለች፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሥራችን የዘመኑን መንፈስ መዝለፍና የጊዜውን መሳዮች ሳንታክት መገሰጽ ይገባል።************

******የኖኅ መርከብ ፍጥረትን ለማትርፍ አንዲትና ብቸኛ እንደነበረች ሁሉ ዛሬም በእግዚአብሔር አምኖ ለመዳን ብዙ ቤተክርስቲያን የለም:: ቤተክርስቲያን አንዲት ናት።

*******ስለ ቅዱስ መቃርዮስ ሰይጣን ሲመሰክር፦መቃርዮስ ሆይ፥ አንተ ትጾማለህ እኔ ጭርሱኑ እህል አልበላም፤ አንተ በትግሃ ሌሊት ታድራለህ እኔ ግን ጭርሱኑ አልተኛም፤ በአንተ ክፉ ላደርግብህ ያልቻልኹት በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ አንተ እኔን ያሸነፍኸኝ በትሕትናህ ነውአለው ይባላል፡፡ ቅዱስ እንጦንስም የሰይጣን ወጥመድ እስከ ሰማይ ድረስ ተዘርግቶ የሰውን ልጆች እንወጣለን ሲሉ ጠልፎ ሲጥላቸው በማየቱ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበ፤አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የሰይጣን ወጥመዱ እንዲህ ብርቱ ከሆነ ታዲያ ሰው እንዴት ሰይጣንን ማምለጥ ይችላል?” ብሎ ቢጠይቀው "በትሕትና" ብሎ መልሶለታል።********

********እግዚአብሔር በመካከላችን ለመኖሩና ሲጎበኝን ለማየት እንዳንችል ልባችን በብዙ መንፈሳዊ ውድቀቶቻችን ምክንያት በሐዘን ስለተሰበረ ሥራውን ማስተዋልና መገንዘብ የምንችልበት ጊዜ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ኋላ ተመልሰን ከአባቶቻችን የተረከብናትን ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ውበትና መልክ፣ ቅድስናና ግርማ ምን ትመስል እንደነበር ማስብ ብንችልና ብናስተውል ቤተክርስቲያን ውብና የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች፤ ባለቤትዋ እግዚአብሒር እንደማይተዋት፣ እንደማይለያት፣ ሊገባንና ሊታየን ይችላል ብዬ ደግሞ አምናለሁ፡፡************

******….ድኅነትን የሚሻ ያለ ክርስቶስ ጸጋ ሕግን ብቻ በመፈጸም የሚድን የለም፡፡ ስለዚህ ጸጋና ሕግ በክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ውስጥ ሚዛን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ….በጸጋ መዳን ማለት ኃጢአት ለመሥራት ፈቃድ ማግኘት ማለት አይደለም፡፡ በጸጋው ጉልበት ሕግን ለመፈጸም እንጂ።፤*******