Saturday, April 30, 2016

የመስቀሉ ምስጢር፦

(እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!)

ድንቅ ሥነ ስዕል
ክርስቶስ ክርስትና ፋና ፈንጣቂ፤
ሃይማኖቴ ተዋሕዶ ነሽ እጅግ ድመቂ።

የሠማዕታት ተጋድሎ የጻድቃን ክብር፤
አንድም በምሳሌ አንድም በምስጢር፤
በፍቅር ሁነን በአንድነት እንድንመሰክር፤
ይሄ ነው ታላቁ የመስቀሉ ምስጢር።

ኃያሉ አምላክ ድንቅ መካር አማኑኤል የእኛ ጌታ፤
ድንግል ተወልዶ ዓለሙን ሁሉ በፍቅሩ የረታ።

ክርስቶስን የምንወድ ትዕዛዙን እንጠብቅ፤
ስለ ጻድቃን ስለ ሠማዕታት እንድንጠነቀቅ፤
ይልቅ ተጋድሏቸውን በአርምሞ እንድናደንቅ፤
ተናግሯል የእኛ ጌታ መስክረን እንድንመረቅ።

የዓለሙ በግ የመስቀሉ ምስጢር፤
ተቤዥቶ ወደደን ሰጠን ፍፁም ፍቅር፤

ድንግል ያን ጊዜ ያን ጊዜ ከአጠገቡ፤
ዐይኖቿ አረፈ ወደ ልጇ ጣምራ እያነቡ፤
ልቧ ተከፈለ በአምስቱ ኅዘናት ተመታ፤
ልጇ ወልደ አምላክ በስቃይ ሲንገላታ።

እንዴት ቻለቺው ያን የአንጀት መንሰፍሰፍ፤
የተንቢቱን ፍፃሜ የኅዘኗ ታላቅ ሠይፍ።

ጻድቅ ዮሴፍ ዕንባውን ረጨ ወደ አዶናይ፤
እጅግ ተደነቀ መልአከ ዑራኤል ከሠማይ፤
ወልድ ዋሕድ የፍቅሩ ጥጉ እንዲታይ፤
አፉን አልከፈተም በሸላቾቹ ስቃይ።

የመስቀሉ ምስጢር እንደተጻፈ ተፈፀመ፤
ተፈጥሮ ተናገረ ዓለም በፍቅሩ ተደመመ።

ስለ ሠውነቱ የሦስት ቀን ቀጠሮ፤
በአዲስ መቃብር አካሉ ተቀብሮ፤
ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን መዝብሮ፤
ሠላምን አውጀ ሰይጣንን አስሮ፤

በእባብ ገላ የገባው ዲያብሎስ ተሽሮ፤
ትንሣኤን አሳየን የሞት ሞትን ሽሮ፤
ለአዳም ልጆች ሠላምን ተናግሮ፤
እውነት ትመስክር ትናገር ተፈጥሮ።



(ማስታወሻነቱ፦ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያገለገሉና ለቤተክርስቲያን ብዙ መምህራንን ያፈሩ፣ በጣሊያን ሀገር በፊሬንዜ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ፅዋ ማሕበርን በማጠናከር ብዙ ለደከሙ ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዲያቆን አምሳሉ ተፈራ  ይሁንልኝ። /ኃይለ ኢየሱስ፤ ፳፪/፰/፳፻፰ ዓ/ም)

Wednesday, January 27, 2016

ይድረስ ለመንፈሳዊ መምህራኖቻችን (ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ)፦

       ውድ ወንድሞቻችንንና መምህራኖቻችን፥ ሠላምና ፍቅር በድንግል ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከመላው ቤተሰባችሁ ጋር ይብዛላችሁ።

አንድ ነገር ለማለት ፈልጌ ነበር፥ እርሱም፦ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ስለ መጠቀም> ጠቀሜታው ምንድን ነው? ጉዳቱስ እስከምን ያህል ነው? በሚል የግንዛቤ መስጫ ትምህርት እንዲሰጡን ከማሰብ የመነጨ ነው።

ምክንያቱም፦ እነ "ቀሲስ" ትዝታውና  እነ "ቀሲስ" መላኩ ሠሞኑን በፒያኖ (በኦርጋን) ስለመዘመር የሚያጣቅሱስ የዶክተር ኢሳያስና አለሜ ሥራዎችና አንዳንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር በፒያኖ (በኦርጋን) የዘመሩትን እንደነ ዘማሪ ኪነጥበብ፣ እንደነ ዘማሪ ይልማ ኃይሉ፣ እንደዘመሩ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህ እውነት በዚያን ጊዜ በፒያኖ (በኦርጋን) የተዘመሩ ዝማሬዎች በነባራዊው ኹናቴ ነው ወይንስ ለቤተክርስቲያን የመዝሙር ማሳሪያ ተደርጎ ለመንፈሳዊ ልዕልና፣ ለመንፈሳዊ አርምሞ የሚሰጠው ጠቀሜታ ታምኖበት ነው ወይ?

ይህንን አርዕስት በዋቢነት የሚጠቀሙት እነ "ቀሲስ" መላኩ ቢኾኑም ከዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ በመነሳት ነው፤ ይህም ሃሳብቸው እንዲህ ይላል፦ <ይኽውም የተደከመበት አጭር መዝሙረ ጸሎት የዜማው ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ ተስማሚ መሆኑን ለመዝሙር አፍቃሪዎቼ አስገነዝባለሁ> (መዝሙረ ጸሎት ገፅ /9 ዶክተር ኢሳያስ አለሜ የፃፉት) ይላል እንጂ በንጉሡም ይሁን በጊዜው የነበረ ቅዱስ ሲኖዶስ፦ በፒያኖ (በኦርጋን) ስለ መዘመር ስለ ጥቅሙና ስለ ጎጂንቱን አይገልፅም፣ አያብራራም!

የኾነው ኾኖ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ  <የዜማው ስልት ለመሰንቆ፣ ለአርጋኖንና (ለኦርጋን) ለፒያኖ እንዲሁም ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ምን ያህል በጥልቀት ተገንዝበውት ይሆን ወይ?

በእርግጥ በእነ ዶክተር ኢሳያስ አለሜ ሃሳብ ተንተርሰው እየተከራከሩ ያሉት እነ "ቀሲስ" መላኩ በዚሁ በፒያኖ (በኦርጋን) የሚያቆሙ አይመስሉም፣ ምክንያቱ፦ <ኖት ላላቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ሁሉ> ያሉትን የዶክተር ኢሳያስን ጽንሰ ሃሳብ> በመያዝ ዛሬ በፒያኖ (በኦርጋን)  የተጀመረ ነገ ይቀጥልና ድረም፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ትራምሬት፣ ጊታር፣ ቫዮሊን ወዘተ . . .  እያሉ ይቀጥላሉ።

ስለዚህ <ለመንፈሳዊ ዝማሬ ዘመናዊ መሳሪያ> ስለ መጠቀም ስንነጋገር በሕዝብ ብዛትና በፐርሰንት ሳይኾን ለመንፈሳዊ አምልኮና ለመንፈሳዊ ዝማሬ አርምሞ (ተመስጦ) የቱ ነው ወደ መንፈሳዊ ልዕልና የሚመራን? መሠረታዊና ቀና መንፈሳዊ መንገድ የሚመራን የቱ ነው? በኦርጋን ወይንስ በክራር፣ በሳክስፎን ወይንስ በዋሽንት፣ ጃዝ ወይንስ ከበሮ፣ ቫዮሊን ወይስ ማሲንቆ፣ በኦርኬስትራ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚይዙት ዘንግ ወይንስ መንፈሳዊ አባቶቻችን ለምስጋና የሚይዙት መቋሚያ፤ የቱ ነው ለመንፈሳዊ ዝማሬና ለአርምሞ (ለተመስጦ) የሚኾነው?

Saturday, January 16, 2016

ማሕበረ ቅዱሳን፥ ስምና ምግባሩ፦

ማ፦ ማገር ነው ለቤተክርስቲያናችን፤
ሕ፦ ሕይወተ ክርስቶስ መሰበኪያችን፤
በ፦ በረቱ ጥልቅ ነው መኖሪያችን፤
ረ፦ ረስተው አይሄዱም ታሪካችንን።

ቅ፦ ቅዱስ እግዚአብሔር አለ' በአንድነታቸው፤
ዱ፦ ዱካ ቅዱሳንን ተከትለው በሃይማታቸው፤
ሳ፦ ሳንቃውን ለሚያነቃንቁ እረፍት ይነሳሉ፤
ን፦ ንስጥሮሳዊያንን ተግተው ይዋጋሉ!።

(ስለ ማሕበረ ቅዱሳን ይህን እላለሁ፤ ስሙም ይኹን ምግባሩ በእኔ ገለፃ፦ ለቤተክርስቲያናችን ማሕበረ ቅዱሳን ማገር ነው!።)

Sunday, October 18, 2015

ነገረ ተሐድሶ፦ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ



እነዚህ ራሳቸውንተሐድሶብለው የሚጠሩ አካላት ለራሳቸው ከማመን አልፈው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ያልሆነ መልክ በመስጠት ፕሮቴስታንታዊ የሆነውን የራሳቸውን አዲስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በግድ ለመጫን እየተንቀሳቀሱ ነው። የእነዚህ አካላት ዋና ዋና ስልታቸው ሦስት ናቸው። እነሱም፦

1 አንደኛው ስልት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና አስተምሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከቀደምት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተለየ እና የራቀ አስመስሎ ለማሳየት መሞከር ነው። ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንናችንን አስተምህሮዋንና እምነቷን፣ ምስጢራቷንና ሥርዓቷን፣ ይትበሃሏንና ትውፊቷን፤ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሕወቷን በሙሉ ከጥንቱ ከጌታችንና ከሐዋርያት እንዲሁም ከሊቃውንት ትምህርት የራቀና የሚቃረን አስመስሎ ማሳየት ነው። ይህም ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልኳ ያልሆነውን ሌላ መልክ በመስጠት ሰዎች ከልቦናቸው ውስጥ እንዲያወጧትና እንዲጠሏት ለማድረግ የረዳናል በሚል ነው። ለዚህ ዓላማቸውም ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታምነውን እንደማታምን፣ የማታምነው ደግሞ እንደምታምን፣ የምትለውን ደግሞ እንደማትል፣ የማትለውን ደግሞ እንደምትል እያስመሰሉ ያለ ይሉኝታና ያለ ኃፍረት ደጋግመው ጽፈዋል።

ተሐድሶዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐዋርያዊ እና ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ጥላሸት ለመቀባት ይረዳናል ያሉትን ነገር ሁሉ አንዳችም ሳያስቀሩ አሟጠው ለመጠቀም ሞክረዋል። ጽሑፋቸው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን በመንቀፍና በማጥላላት ላይ ያተኮረና ያመዘነ ነው። ለዚህም እነርሱ ሌሎችም የሚነቅፉበትን ነገር ሳይቀር ለራሳቸው ሲሆን ደግሞ በአዎንታ ተቀብለው ተጠቅመውበታል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ብዙ ምንጮችንና ነገሮችን ከመጠቀማቸውም ባሻገር ባለቤትነታቸው ከሚታወቁት ሆነ ከማይታወቁ ተረቶችና ወጎችን እንኳ ሳይቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመንቀፍ የሚጠቅም መስሎ እስከታያቸው ድረስ ለመጠቀም ሞክረዋል። አንድን ነገር ደግመው ደጋግመው በመመላለስና ስድቡና ነቀፋውም ቢሆን መልኩን ከመለወጥ በስተቀር ያለቀባቸው መሆኑን አፍ አውጥቶ እስኪናገር ድረስ ያንኑ ነገር በየመጣጥፎቻቸውና በየገጹ ያቀርባሉ።

ተቀባይነታቸውን ለማስፋት ሲሉምኦርቶዶክስየሚለውን ከሁለት በመክፈል ራሳቸውንየጥንቱ ኦርቶዶክስብለው ሲመድቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምታምነውና የምታደርገውን ደግሞ ከጥንቱ የተለየ ነው ለማለትየአሁኑ ኦርቶዶክስየሚል ታርጋ ሊለጥፉላት የሞከሩም አሉ። ይህም ራሳቸውን ፕሮቴስታንት አይደለንም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነን ለማለት ነው። ይህን መጠቀም የሚፈልጉትም ቤተ ክርስቲያኒቷን ከውስጥ ሆነው ሙሉ በሙሉ ቀስ በቀስ በሂደት በመሸርሽር ኦርቶዶክሳዊ ማንነቷን በማሳጣት ፕሮቴስታንት የማድረግ ስውር ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስ እንዲረዳቸው ነው።

ሁሉተኛ፦ ተሐድሶዎች ራሳቸውን በየመጣጥፎቻቸውና በየገጹ፣ በንግግራቸው ሁሉየጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንእንደሆኑ ለማሳየት እንዴት እንደሚዳክሩመድሎተ ጽድቅ” (የእውነት ሚዛን ቅጽ ) በሠፊው ያትታል። ወዘተ. . .

ሦስተኛ፦ ስልታቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አስተምህሮ ላይ ያቀረቡት ነቀፋና ማሳጣት እውነት ለማስመሰል ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ትምህርቶች መካከል ለሃሳባቸው ድጋፍ ይሆናል ያሏቸውን የተወሰኑ ነገሮች ለመጠቃቀስ መሞከር ነው። ወዘተ. . .

-----------------------------------------------
ምንጭ፦መድሎተ ጽድቅ” (የእውነት ሚዛን ቅጽ ) ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፤ መጋቢት ፳፻፯ /
-----------------------------------------------

((የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ስውር ደባቸውንና ማንነታቸውን [በዩቱብ ክፍል 1 እና ክፍል 2 እዚህ ተጭነው ይመልከቱ] እንዲሁም ደግሞ "የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ሀራ ጥቃ" ስውር ደባቸውንና  አጠቃላይ ስራቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያስቃኝና ሊነበብ የሚገባ እጹብ ድንቅ ምላሽእጅግ ምጡቅ፣ በጥልቀትና በምርመራ፣ በመረጃና በማስረጃ የተደገፈና የተጻፈ ልዩ መጽሐፍመድሎተ ጽድቅየእውነት ሚዛን! አንብቡ፣ ለሌሎችም ያስነብቡ!)