Wednesday, June 19, 2013

ሾፌሮችንና ተሳፋሪዎችን በመንገዳቸው ላይ የሚያጠቁ ክፉ መንፈሶች!

                        “በማለዳ መያ’ዝ” በመልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙ

ሰዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች የትራንስፖርት ዘዴዎች ማለትም በአውሮፕላን፣ በመርከብ፣ በባቡር፣ በመኪና በመጠቀም፤ ከቦታ ወደ ቦታ ይዘዋወራሉ። ጉዞ ጀምረው በሚገጥማቸው አደጋ፣ ያሰቡበት ሥፍራ ሳይደርሱ ወጥተው የቀሩ፤ ወደ ቤታቸውና ወደ ቤተሰባቸው ያልተመለሱ ብዙዎች ናቸው።

በመጓጓዣ ዘዴዎች ላይ የሚደርሱ የመጋጨት፣ የመከስከስ፣ የመገልበጥ፣ የመቃጠል፣ የመስመጥ ወዘተ .... አደጋዎች፤ ከግማሽ በላይ መንስኤያቸው ከክፉ መናፍስት ምሪት ጋር የተያያዙ ናቸው።

አውሮፕላን አብራሪዎች፣ የመርከብ ካፒቴኖች፣  የባቡርና የመኪና ሹፌሮች፤ ኃላፊነታቸው የመክበዱን ያህል፤ የማይጸልዩና መንፈሱን በጸሎት አስረው የማይነቀሳቀሱ ከሆነ፤ የመናፍስቱ ጥያቄዎች የማያቋርጥ የመንገድ ላይ ጦርነት ይሆንባቸዋል።

ብዙ ጊዜ በዲያቢሎስ አማካኝነት በሁሉም የመጓጓዣ ዘዴዎች ላይ የሚደርሰው አደጋ ተመሳሳይነት ያለው ነው። ለዚህ ገለፃችን፣ አንዱ የሆነውን በመኪና ላይ የሚያደርሰውን አደጋ፤ በምሳሌነት እንመልከት፦



የመኪና አደጋ በክፉ መንፈስ አማካኝነት የሚደርሰው፦

·        ክፉው መንፈስ አሽከርካሪውን ማለትም ሹፌሩን ማዕከል አድርጎ ሲይዝ፤

·        የመንፈሱ የጥፋት ልጆች መኪናውን ሲሳፈሩ፤

·        ደም የለመዱ የሰይጣን መንፈሶች በመኪናው መንገዶች ላይ ሰፍነው ሲገኙ፤

ሹፌሩ የቤተሰብ የዛር መንፈስ ሲኖርበትና በራሱ ገንዘብ ዶሮ፣ እጣን፣ ሰንደል፣ ሽቶ፤ ወዘተ ... እየገዛ በመስጠት መንፈሱን የሚገብርና የሚያስገብር ሆኖ ይቆይና ከጊዜ በኋላ፤ በተለያየ ምክንያት ግብሩን ሲቀንስ ሲዘነጋና ሲያቋርጥ፤ መንፈሱ ተቆጥቶ የመኪና አደጋ በማድረስ፣ ግለሰቡን ይቀጣዋል።

በዚህም የአሽከርካሪው ጦስ የአዙሪት መንፈስ ሆኖ፣ መዘዙ ለተሳፋሪዎቸዎች በሙሉ ይተርፋል፤ ማለት ነው። የአደጋው ከባድነትና ቀላልነት የሚወሰነው፥ ሾፌሩ መንፈሱን ባስቆጣበት የጥፋት መጠን ልክ ይሆናል።

ከዚህ በተቃራኒው፥ ሾፌሩ የዘር መንፈስ እንዳለበት ሳያውቅ ይቀርና በሥራውና በኑሮው ላይ ብቻ ሲያተኩር፣ ግብሩን ያላገኘውና ወስጡ የተደበቀው ክፉ መንፈስ በመቆጣት፤ በማሽከርከር ላይ እንዳለ ልቡን ሰውሮ አደጋ ያደርስበታል።

በዚህ መሠረት የተቆጡት ክፉ መንፈሶች በሾፌሮችና በተሳፋሪዎች ላይ ከሚያደርሱት አደጋዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት፦

·        ከፍ ብሎ እንደተጥጠቀሰው፥ ደም የለመዱ መናፍስቶች በመንገድ ላይ በመስፈን፤ በቋሚነት መኪና በመገልበጥ፣ ትራፊክ መስለው በመቆም ቀጥታና ጠመዝማዛ (ኩርቫ) መንገዶችን አስቶ ገደል ውስጥ በመክተት፣ ከግንብ፣ ከድልድይ፣ ከግንድ፣ ከቆመ መኪና ወይም ከሌላ ግዑዝ አካል ጋር ወዘተ .... በማጋጨት፤ ሕይወት እንዲጠፋና ደም እንዲፈስ ያደርጋሉ።

·        የሾፌሩ፥ የጫት፣ የሺሻ፣ የሐሺሽና የመጠጥ ሱስ መንፈሶች ግብራቸውን በበቂ ሁኔታ ካላገኙ፤ እንደተናቁና እንደተጠሉ በመቁጠር፤ አደጋ ያደርሳሉ፤ ከዚህ በተቃራኒ በሾፌሩ ሕይወት የሚቀና የምቀኛ የመተት መንፈስ በሰውዬውና በመኪናው ላይ የተላከ ከሆነ ደግሞ፤ ግለሰቡ ከላይ በተጠቀሱት የሱስ ዓይነቶች ሕሊናው ናውዞና ተሸብቦ፣ ልቦናውና ዓይኑ ተጋርዶ፤ ለአደጋ ይጋብዘዋል።

·        ለምሳሌ፦ በመንፈሱ ተጽዕኖ አሽከርካሪው መሪንና ፍሬንን መቆጣጠር ተስኖት፤ መኪናው እንዲጋጭ፣ እንዲገለበጥ፣ ገደል እንዲገባ፣ ሌላ አደጋ እንዲደርስ ወዘተ ... በማድረግ፤ ጥቃቱን በክፉ ሁኔታ ይገልጣል።

·        አንዳንድ ሾፌሮች፥ በሥራ ምክንያት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲጓዙ፤ ከብዙ ሴቶች ጋር በሚፈፅሙት ዝሙት የተነሳ፤ በቀላሉ በቡዳ መንፈስ ተይዘው፤ መንፈሱ ልቦናቸውንና ዓይናቸውን በመሰወር፤ አደጋ ሊያደርስባቸው ይችላል።

·        በመጀመርያ ደረጃ፥ ባለቤቱ መኪናውን በሟርትና በስልብና ገንዘብ ከገዛው፤ እንዲሁም፥ የግዢው ግንኙነት ከጠንቋይና ከመተት ጋር የተነካካ ከሆነ፤ ያ መኪና ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል።

·        በመኪና ውስጥ አደገኛ የጥፋት መንፈስ ልጆች ከመንገደኞች ጋር አብረው ተሳፍረው ሲገኙ፤ በእነርሱ ላይ ያደሩት ክፉ መንፈሶች በሾፌሩ ላይ አዚም ሆነው ስለሚገቡ፤ የመኪናወው አደጋ ቅርብ ይሆናል ማለት ነው።

ከዚህ፥ ለየት ያለው ሌላው ጥቃት ደግሞ፤ አዲስ መኪና ሲገዛ ወይም አገልግሎት እየሰጠ ያለም ቢሆን፤ የመኪናው ሞተር፣ የነዳጅ፣ የኤሌክትሪክ መስመር ወዘተ ... ላይ የሚያርፍና የሚቀመጥ የምቀኛ መተት መንፈሰስ ተልኮበት፤ በክፉው መንፈስ ኃይል አስገዳጅነት ተሸከርካሪው እንዳይንቀሳቀስ ሊያደርገው ሁሉ ይችላል።

በአጠቃላይ ስለ ማንኛውም ነገር ሆነ ስለ አውሮፕላን አብራሪዎች፣ የመርከብ ካፒቴኖች፣  የባቡርና የመኪና ሹፌሮች፤ ኃላፊነታቸው የመክበዱን ያህል፤ የማይጸልዩና መንፈሱን በጸሎት አስረው የማይነቀሳቀሱ ከሆነ፤ የመናፍስቱ ጥያቄዎች የማያቋርጥ የመንገድ ላይ ጦርነት ይሆንባቸዋል።

ዋቢ መጽሐፍ፦ “በማለዳ መያ’ዝ” ገፅ ከ45-47

No comments:

Post a Comment