ከደብረ ሊባኖስ ወደ አብተ ማርያም ገዳም ለመድረስ በእግር ጉዞ መሄድ ግድ ይላል። የመድረሻ ሰዓት፥ እንደ እግር ተገዦች (እንደሰዎች) ፍጥነት ይለያያል። እኛ ግን ወደ አንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ አካባቢ ፈጅቶብን ደረስን።
በዛም፥ በአብተ ማርያም ገዳም አካባቢ ከሚኖሩ አበው ዘንድ ጎራ በማለት አባ ፍስሐ አገኘናቸው። እርሳቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበቁ አባት ናቸው። አባ ፍስሐ፥ ምክራቸው፣ ተግሳፃቸው፣ ትምህርታቸው፤ እጅግ እጹብ ድንቅ ነው።
ከአንደበታቸው በሚወጣው ፍጹም መንፈሳዊ ምግብ፦ ነፍስህ ሐሴት ስታደርግ ታስተውላለህ፣ ሕይወት ትማረካለች፤ ተመስጧቸው፥ ህሊናን ወደ መንፈሳዊ ተመስጦ ውስጥ ይመራዋል፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎዋቸው የሕይወታቸው ምርኮኛ እንድትሆን አንዳች የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ያነሳሳሃል። እድሜያቸውን በሙሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የገበሩ አባት ናቸው።