በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው)፤. . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።
በክርስቶስ
ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።
ብፅዕት፥
ንጽሕት እና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ሁለንተናዋ የሚሰብከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤» ሲል እንደተናገረ፥ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየሰበከች ያለችው በደሙ የዋጃትን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳፪-፳፫፣ የሐዋ ፳፥፳፰።