Tuesday, January 6, 2015

ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ (በምሥጢረ ሥጋዌ አስተምህሮ)


                 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

      ተሠገወ፡- ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህሥጋዌሰው መሆንን፣ መገለጽን (በተአቅቦ) መግዘፍን፣ መወሰንን፣ መዳሰስን ያመለክታል። ቀድሞ ምን ነበር? ወይም ማን? ለሚለው ጥያቄ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልበመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ.11) ሰው የሆነም አካላዊ ቃል እንደሆነቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ።በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐ.114) ሰው የሆነውም በተዋሕዶ ነው። ይኸውምአንድ ጊዜ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነውበማለት ነው። ምሥጢረ ሥጋዌ የአብ አካላዊ ቃል ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል ሰው የሆነበት፤ ሰውንም ያዳነበት መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ማለት ነው።
 
      ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) የለም። ሞትን በቀመሰ ጊዜም መለኮት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም። በዚህም ምክንያት ሞቱ እንደሌሎች ፍጡራን ወይም እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የማይታይ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስእርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፤ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።ሲል ገልጦልናል። (ዕብ. 214) በመሆኑም ሲራብም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲተኛም፣ ሲነሳም፣ ተዓምራት ሲያደርግም፤ በአንድ ባሕርይ ጸንቶ እንጂ እንደ ማየ ግብጽ በሚጠት አንድ ጊዜ አምላክ አንድ ጊዜ ሰው እየሆነ አይደለም።

        ሰው የሆነውም እንደ ወይነ ቃና እና እንደ ብእሲተ ሎጥ (የሎጥ ሚስት) በውላጤ (በመለወጥ) እንደ መስኖ ውኃ በኅድረት፤ ሳይሆን ተአቅቦ ባልተለየው ተዋሕዶ ነው።የሰውን ሥጋ ነሥቶ ቢዋሐድ እንጂ ሥጋንማ ባይነሳ እንደምን ሰው በሆነ ነበር፤ ነፍስን ሥጋን መዋሐዱም መለወጥ፤ መቀላቀል ፤መለየት በሌለበት የሁለቱን ባሕርያት አንድነት እነደፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ አንድ አደረገ። ሥጋ ሥጋ ነውና፤ መለኮት አይደለም። እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ቢሆንም ቃልስ አሁን አምላክ ነው። ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም። ሥጋን ለራሱ ገንዘብ ቢያደርግም፤ በዚህም ደግሞ ከተዋሕዶ በምንም በምን አይናወጥም። ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም። መከፈል የሌለበትን አንዱን ሁለት እናደርገው ዘንድ አንከፍለውም። አንድ ወልድ አንድ ባሕርይ ነው ብለው እንደተናገሩት። ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር በልቡናችን እንደምናውቅ በነፍሳችን ዓይንም እንደምናይ መጠን ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋልና አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ገዢ፣ አንድ ወልድ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ እግዚአብሔር ቃል ነው እንላለን። 

"በዓለ ልደት" ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ

                                                                              (ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም) ያስተማሩት።

 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

                         የተወደዳችሁ ምእመናን! እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ።

ጋድ (ገሃድ) እና ገና፥ ልደቱ ለእግዚእነ። (ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ/ም)

            «ጾመ ገሃድ (ጋድ)፦ የቃሉ ትርጕም «ገሃድ» ሲል መገለጥ፥ «ጋድ» ሲል ለውጥ ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት፦ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ በዓል በሳምንት ሁለት ቀን በምንጾምባቸው ጾም በተሠራባቸው በረቡዕና በዓርብ የዋለ እንደ ሆነ የጾሙ ሥርዓት ሳይጠበቅ፤ ፩ኛ፤ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ለ፳፱ አጥቢያ፤ ፪ኛ፤ ጥር ፲ ቀን ለ፲፩ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ቅዳሴ እንዲፈጸምና ምእመናን በትንሣኤው የአከባበር ሥርዐት ዐይነት በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ አዝዘዋል። ስለዚህ ሁለቱም ማለት የልደት፥ የጥምቀት ዋዜማ በጾም እንዲታሰብ ሆኗል።

           በአንድ በኩል የጌታን መገለጥ የምናስብበት ነው። መገለጥ ሲባልም እንደ በዓላቱ ጠባይ ሁለት ነው። በልደት መገለጥ ሲባል ሰው ሆኖ የማያውቅ አምላክ በሥጋ ሰው ሆኖ በአጭር ቁመት፥ በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለ ተገለጠና ሰዎች ሊያዩት ሊዳስሱት ስለ ቻሉበት ነው።

        በጥምቀት መገለጥ መባሉ፤ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ ፴ ዓመት ዕድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲሕ፥ ሰው የሆነው አምላክ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኋላ በ፴ ዓመት ዕድሜው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፤ አብ፤ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት፤» ብሎ በሰጠው ምስክርነት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት የተነበዩለት የሰው ልጆች መድኃኒት ሥግው አምላክ ማለት ሰው የሆነ አምላክ እሱ መሆኑ ስለ ተገለጠበት ነው። ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ ቅዳሜ፥ እሑድ ቢሆን በሰንበት ጾም ስለ ሌለ ሥርዓተ ጾሙ ከጥሉላት ምግብ በመከልከል ብቻ ይፈጸማል።» [የጽድቅ በር፤ ፲፱፻፸፱ ዓ ም፤ ገጽ ፳፯ - ፳፱።]

        «ልደቱ ለእግዚእነ። ይህ በዓል ሰውን በመልካችን በምሳሌአችን እንፍጠር ብሎ በጥንተ ፍጥረት የተናገረ እግዚአብሔር ቃል የሰውን ልጆች ለማዳን፤ «አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ።» «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ እመጣለሁ፤» ሲል በሰጠው ተስፋ፤ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ያለ አባት የተወለደበት ነው። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ግዚአብሔር ቃል ወልደ አብ ድኅረ ዓለም ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም መወለዱና ወልደ ማርያም መባሉ ለሰው ልጆች ክብርና ሕይወት ስለ ሆነ፤ ሥጋ ቃልን ተዋሕዶ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ከሰማያውያን መላእክት፥ ከምድራውያን ኖሎት (እረኞች) ምስጋናን በግልጥ የተቀበለበትን፥ ለሰው ልጆች ዕርቅ የተመሠረተበትን ይህንን ታላቅ በዓል ኢትዮጵያ ከዓለም ክርስቲያኖች ጋራ በመተባበር ታከብረዋለች። (ዘፍ፤ ፲፰፥ ፲። ሉቃ፤ ፪፥ ፲፫ - ፲፱።)

       መሠረቱም፤ «እነሆ በኤፍራታ በጎል ተጥሎ፥ በጨርቅ ተጠቅልሎ አገኘነው፤ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው፤ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተን የጌታችን እግር ከቆመበት እንሰግዳለን፤» የሚለው ትንቢታዊ ቃል ነው። (መዝ ፻፴፪፥ ቍ ፮ እና ፰።) [የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤ ገጽ ፪፻፴፭]

(ክቡር አባታችን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ በዓለ ልደትን በማስመልከት ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ያስተላለፉንት መንፈሳዊ ትምህርት ነው። በተጨማሪም፦ በስማቸው የተሰየመውን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩን መንፈሳዊ መጦመርያ ይጎብኙ (ለአባታችን፥ ለሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ፦ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፤ ጸጋ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!!!)

Saturday, December 20, 2014

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፩) መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው). . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።

በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።

ብፅዕት፥ ንጽሕት እና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ሁለንተናዋ የሚሰብከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤» ሲል እንደተናገረ፥ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየሰበከች ያለችው በደሙ የዋጃትን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳፪-፳፫፣ የሐዋ ፳፥፳፰።

Friday, December 19, 2014

የሰይጣን አመሉና ጉዞ



  የሰይጣን አመሉ

ሰይጣን አምላክ እንዳለ ያምናል ይንቀጠቅጥማል፤
ቢኾንም ግን፥ የጌታን ቸርነቱንና ኃይሉን ይክዳል፤
ሰይጣን ለአመሉ፥ ከቅዱስ ቃሉ ጥቅስ ይጠቅሳል፤
የብርሃን መልአክ እንዲመስል፥ ራሱን ይለውጣል።

የሰይጣን ጉዞ

ክርስቶስን፥ የባህሪይ አምላክነት ያስክድሃል፤
ድንግል ማርያም ፍቅር፥ ሊያርቅህ ይኳትናል፤
ከቅዱስ መልአክት ተራዳኢነት እቅፍ ያስርቅሃል፤
በመንፈሳዊ ሕይወት፥ እንዳትጎለብት ይጎስምሃል።

የቅዱሳን አበው ተጋድሎ፦ እንደ-ኢምኒት አድርጎ ያሳይሃል፤
ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ አምላክህን ያስክድሃል፤

የቅዱሳን ምልጃ፥ እንኳን በአጸደ ነፍስ በአጸደ ሥጋ የለም ይልሃል፤
ለምዕመናን ተስፋ አስቆራጭ እንድትኾን በቅዱስ ስፍራ ይሾምሃል፤
ከእውነታኛው የሃይማኖት መንገድና ኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር ያስርቅሃል፤
አንዴ ከመንገዱ ፍቅቅ ስላደረገኽ በዓለማዊ ዕይታና ምኞት ይዘፍቅሃል።

ፆም ፀሎት ሥግደት እንዳታደርግ ይወተውትሃል፤
በሥጋ ወደሙ እንዳትከብር እንከን ይፈጥርብሃል።

በመጨረሻም፥ በራስህ እንድትታበይ ያደርግሃል፤
በአንድ ምላስ፦ እውነተኛው ቃልህን ያሳጥፍሃል፤
እኔስ ከማንና ከማን አንሳለው እንድትል ያነሳሳሃል፤
ባደፈ ልብስ እግዚአብሔር ፊት ሊከስህ ይቆማል።

(ኃይለ ኢየሱስ //፳፻፯)

Wednesday, December 10, 2014

«ወዮልኝ» መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው



        በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
                              «ወዮልኝ»

እግዚአብሔር ሰዎች «ወዮልኝ፤» እያሉ ራሳቸውን ገሥጸው ይኖራሉ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ፊት ለፊት ስላየው ፥ ቃል በቃል ስላነጋገረው፡- «አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፡- «ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥ አትሞትም፤» ብሎታል። (መሳ ፮፥፳፪)። ነቢዩ ኤርምያስም፡- «በሆድ ሳልሠራ አውቄሃለሁ፥ ከማኀፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሐዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» በተባለ ጊዜ፡- «ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤» ብሏል። (ኤር ፩፥፬)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤ » ብሏል። (፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮)።

          እነዚህ «ወዮልኝ፤» ማለታቸው ለእኛ አብነት ነው። ታላላቆቹ እንዲህ ካሉ ከእኛ ከታናናሾቹ የብዙ ብዙ ይጠበቃል። ዕለት ዕለት «ወዮልኝ፤» እያልን ደረታችንን ልንደቃ፥ እንባችንን ልናፈስስ ይገባል። ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በስተቀር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን አናውቅምና። ሰውን ደስ ለማሰኘት በሰውም ዘንድ ለመወደድ (ለውዳሴ ከንቱ) እግዚአብሔርን እናሳዝናለንና። እንኳን መንፈሳዊ መሆን መምሰሉ እንኳ አቅቶናልና። ሃያ፥ ሠላሳ ዓመት ቃለ እግዚአብሔር ዘር ተዘርቶብን፡- ሠላሳ ስድሳ መቶ ማፍራት የተሳነን ዘረ ቆርጥሞች ነንና። መቁረባችን ማቁረባችን መቀደሳችን ማስቀደሳችን ማሳለማችንመሳለማችን መናዘዛችን ማናዘዛችን መዘመራችን ማዘመራችን መስበካችን መሰበካችን ሁሉ ከንቱ ሆኖብናልና። ስለሆነም «እገሌ ሳይገባው ነው፤» የሚለውን ትተን፡- «እኔ ሳይገባኝ ነውና ወዮልኝ፤» እንበል። የእግዚአብሔር ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ አይጠብቁምና።

Monday, December 1, 2014

ሕይወታችሁን አጣፍጡ!



የሕይወት ውኃው ለማግኘት፥ ከእንስቶች የለያት፣
የሕይወት ውኃ ኾነና፥ እርሷን ምንጩ አደረጋት፣
ማንም ለመርካት ቢፈልግ፣ ድንግልን ንጉሥ ሾማት፣
በእቅፏ እንድታቅፈው፥ እናቱ እንድትኾን የመረጣት።

ክርስቶስን ለማግኘት፥ እስኪ ቅዱና ጠጡ፤
ከድንግል ዘር፥ ሕይወታችሁን አጣፍጡ!

ከምንጩ አጥልቁ፥ መቅጃችሁን ከጉድጓዱ፤
ይገባችኋል የእናቱን ፍቅር፥ የናቃት ሲሰግድ፣
የእርሱን እፎይታ ታገኛላችሁ ከጥልቁ ስትቀዱ፣
ያኔ ሕይወታችሁን ስታጣፍጡ በፍቅሯ ስትነዱ።

(ህዳር ፳፪/ ፳፻፯ /)