በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ተሠገወ፡- ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ “ሥጋዌ” ሰው መሆንን፣ መገለጽን (በተአቅቦ)፣ መግዘፍን፣ መወሰንን፣ መዳሰስን ያመለክታል። ቀድሞ ምን ነበር? ወይም ማን? ለሚለው ጥያቄ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል “በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ተብሎ ተገልጿል። (ዮሐ.1፥1) ሰው የሆነም አካላዊ ቃል እንደሆነ “ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ም ተመልቶ በእኛ አደረ።” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐ.1፥14) ሰው የሆነውም በተዋሕዶ ነው። ይኸውም “አንድ ጊዜ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው” በማለት ነው። ምሥጢረ ሥጋዌ የአብ አካላዊ ቃል ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል ሰው የሆነበት፤ ሰውንም ያዳነበት መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ማለት ነው።
ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) የለም። ሞትን በቀመሰ ጊዜም መለኮት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም። በዚህም ምክንያት ሞቱ እንደሌሎች ፍጡራን ወይም እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የማይታይ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ “እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፤ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።” ሲል ገልጦልናል። (ዕብ. 2፥14) በመሆኑም ሲራብም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲተኛም፣ ሲነሳም፣ ተዓምራት ሲያደርግም፤ በአንድ ባሕርይ ጸንቶ እንጂ እንደ ማየ ግብጽ በሚጠት አንድ ጊዜ አምላክ አንድ ጊዜ ሰው እየሆነ አይደለም።
ሰው የሆነውም እንደ ወይነ ቃና እና እንደ ብእሲተ ሎጥ (የሎጥ ሚስት) በውላጤ (በመለወጥ) እንደ መስኖ ውኃ በኅድረት፤ ሳይሆን ተአቅቦ ባልተለየው ተዋሕዶ ነው። “የሰውን ሥጋ ነሥቶ ቢዋሐድ እንጂ ሥጋንማ ባይነሳ እንደምን ሰው በሆነ ነበር፤ ነፍስን ሥጋን መዋሐዱም መለወጥ፤ መቀላቀል ፤መለየት በሌለበት የሁለቱን ባሕርያት አንድነት እነደፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ አንድ አደረገ። ሥጋ ሥጋ ነውና፤ መለኮት አይደለም። እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ቢሆንም ቃልስ አሁን አምላክ ነው። ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም። ሥጋን ለራሱ ገንዘብ ቢያደርግም፤ በዚህም ደግሞ ከተዋሕዶ በምንም በምን አይናወጥም። ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል ፤ አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም። መከፈል የሌለበትን አንዱን ሁለት እናደርገው ዘንድ አንከፍለውም። አንድ ወልድ አንድ ባሕርይ ነው ብለው እንደተናገሩት። ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር በልቡናችን እንደምናውቅ በነፍሳችን ዓይንም እንደምናይ መጠን ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋልና አንድ ክርስቶስ፣ አንድ ገዢ፣ አንድ ወልድ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ እግዚአብሔር ቃል ነው እንላለን።