Showing posts with label ብሒለ አበው. Show all posts
Showing posts with label ብሒለ አበው. Show all posts

Sunday, July 24, 2016

«ምን እናድርግ?» (ሉቃ ፫፥፲፬)

ልጆቼ ሆይ «ምን እናድርግብላችሁ ራሳችሁን ስትጠይቁ በመጽፍ ቅዱስ ላይ በመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ የተነገረውን ቃል አስቡ! ይህን ኃይለ ቃልም ታገኛላችሁ፦ «ጭፍሮችም ደግሞ፥ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ» እንደተባሉ ልብ በሉ!

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ይህ እውነተኛና የታመነ ቃል ነው የምነግራችሁ! በማንም ላይ ግፍ አለመሥራት፣ በማንም ላይ በሐሰት አለመመስከርና አለመክሰስ፣ በማንም ላይ ያልተገባ ጉቦና የተለየ ጥቅማ-ጥቅም አለመጠየቅ፣ በማንም ላይ በሥልጣንህ ተመክተህ ፍርድ አለማጓደል፣ በማንም ላይ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደህ ራስህንም ሌሎች ሠዎችንም በገንዘብ አለመደለል፤ ለሀገርህና ከአንተ አገልግሎት ለሚጠብቅህ ሕዝብ ታማኝ መሆንን አለመዘንጋት፤ በላብህ ዋጋ ሕይወትህን ማጣጣም እንዳለብህም ተረዳ፤ ግፍን፣ ተንኮል፣ ሸርን፣ አሻጥርን፣ ሤራን፣ ምቀኝነትን፣ ከሕይወትህ አስወግድ፤ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ የዋህነትን፣ መልካምነትን፣ ሠናይ ምግባርን፣ አርቆ አሳቢነትን፣ ልበ ሠፊነትን፣ ገርነትን፤ ገንዘብህ አድርግ።

ልጆቼ ሆይ፦ ምን እንደምታደርጉ ልንገራችሁ? ከትንሹ እስከ ትልቁ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሕግ አውጪ እስከ ሕግ አርቃቂ፣ ከወታደር እስከ ባለሥልጣናት ድረስ፤ ከቀራጮች እስከ ጭፍሮች፣ አጠቃላይ ሕዝቡ ሁሉ ይሄ አማናዊ ቃል ለራሱ ገንዘብ ሊያደር ይገባል፤ ከላይ የተጠቀሱ እኒህን ነገሮች ስትፈፅሙ የመጥምቀ ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ሕይወታችሁን በሐሴት ያረሰርሰዋል፤ እናንተም «ምን እናድርግብላችሁ ለጠየቃችሁት ጥያቄም እግዚአብሔር ምላሽ ይሄ ነው።

(ኃይለ ኢየሱስ ፲፯/፲፩/፳፻፰ /)

Friday, January 23, 2015

"በርታ ሠውም ሁን"፦ (፩ኛ መጽ ነገ ፪፥፫) አስራ ኹለቱ ምክረ ዘ መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ


በርቱ፥ ሠውም ሁኑ! ሠው ለመኾን የሚከተሉትን መንገዶች እንኺድ

፩፤ አምልኮታችንን፦ እናክብር።

፪፤ እግዚአብሔር ቃል፦ ምግባችንን እናድርግ።

፫፤ የአሕዛብን መንፈስ፦ ከኅሊናችን ውስጥ እናውጣ።

፬፤ የሎጂክ ኑሮዎቻችንና የሎጂክ የእውቀት ጠባዮቻችንን፦ እግዚአብሔር አምላክ መንገድ ላይ እንጣለው።

፭፤ የአባቶቻችንን መንፈሳዊ ታሪክ፦ እንደገና ለመገመትና ለማንሳት እንሞክር።

፮፤ የቤተ-እግዚአብሔር መንፈስን፦ በፍቅርና በጸጋ የምንመላለስበትን ጉልበት እንድናገኝ፥ እንበርታ፤ እንጸልይ።

፯፤ በንስሐና በቅዱስ ቁርባን፦ የተባረከ ትውልድ፣ ጊዜ፣ ዘመን እንዲኖረን፤ ዕቅድ (ፕሮግራም) እናውጣ።

፰፤ የዘወትር ዕቅዶቻችን፦ እግዚአብሔር መንፈስ የተመራ እንዲኾን፥ በጸሎት እግዚአብሔር መንገዳችንን አደራ እንስጥ።

፱፤ የዕውቀታችንን ግማሽ፦ እግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንዲኾን ለማድረ፥ እንደገና አዕምሮዎቻችን ወደ አምላክ እንመልስ፤ የነፍስ ትምህርት እንዲኖረን፥ እንዘጋጅ።

፲፤ የዚህን ዓለም ሃብት፦ እንደ ዕለት እንጀራ እንጂ እንደ ዘላለማዊነት አስበን፣ በክፉ ምትአታዊ አኗኗርና ዲያብሎሳዊ ስሜትና ሐሳብ ውስጥ ገብተን የሟርት ኑሮን አንያዝ።

፲፩፤ እግዚአብሔር ክብርና ጸጋ የተሞላ ኑሮ እንዲኖረን፦ ዕለት ዕለት ሠማያዊ ምስክነት ይኑረን።

፲፪፤ መንፈስ ቅዱስ መግለጫ እንድንኾን፦ ዘወትር በአካኼዳችን፥ እግዚአብሔር ግርማ ሞገስ የተላበስን፣ በእምነቱና በቅዱስ ቁርባን ፊታችን የተባረከና የተሻሸ፣ ሠማያዊ ወዝ ያላቸው ልጆች እንዲፈጠሩና እንዲወለዱ፤ እግዚአብሔር አምላክን፥ እንማጸን።


እነዚህ ሂደቶች በሕይወታችን ውስጥ ካሉ፦ ሠው የመኾን ብርታትና እድላችን ሠፊ ነው።

 -----------------------------------------------------------------------------------------------
(ምንጭ፦ ሬዲዮ አቢሲኒያ፥  መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ መንፈሳዊ ትምህርት፤ ክፍል ፳፫)
 ----------------------------------------------------------------------------