Showing posts with label ታሪክ. Show all posts
Showing posts with label ታሪክ. Show all posts

Wednesday, April 22, 2015

“የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው” (ጠርጠሉስ)



ጠርጠሉስ የተባለውና 2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (160 AD - 220 AD) የነበረው ታላቅ ፀሐፊና የክርስትና ጠበቃ ስለ ሰማዕታት ደም በተናገረበት ሥፍራ ያስቀመጠው ነው። ተርቱሊያን/ Tertullian ወይም በእኛ አጠራር ጠርጠሉስ የሚባለው ሊቅ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አባቶች ጋር የሚቆጠር እንዲያውም የላቲኖች (በላቲን የምትናገረው፣ የምትጽፈው) ቤተ ክርስቲያን ወይም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ መጠራት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ሊቅ ነበር። በእኛ በኦርቶዶክሳውያንም ሆነ በካቶሊኮቹ ዘንድ ብዙም ስሙ ሲጠቀስ የማይሰማው ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጡ ስላሉበት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ሊቅ በዚህ ሥፍራ መጥቀስ የፈለግኹት አገሩና ምንጩ የሰሜን አፍሪካ (የዛሬዋ ቱኒዚያ) አካል በሆነችው በካርቴጅ የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነው። []

እንዴት ዓይነት መከራ ይቀበሉ እንደነበረ፣ እንዴት ዓይነት ሰማዕታት ይቀበሉ እንደነበረ፣ በነገሥታቱ ፊት፥ ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ አሉ፦ አውግዙን፣ አሰቃዩን፣ ስቀሉን፥፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ክፋት ለእኛ እውነተኝነት ምስክርነት ነው! የእናንተ እንዲህ ክፉ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ አረመኔ መኾን፣ የእናንተ እንዲህ ደካማ መኾን፤ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። []

አሰቃዩን፥ ስቀሉን፣ ግደሉን፣ አጥፉን፤ የእናንተ ይኼ ክፋታችሁ፥ የእኛ እውነተኝነት ይመሰክራል። በእናንተ በተሰቃየን ቁጥር፥ እየበዛን እንኼዳለን፤ የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው። ባሰቃያችሁን ቁጥር እየበዛን እንኼዳለን። የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው። እኛ ሁላችን በሰማዕታት ደም የተዘራን ነን! []

Monday, April 20, 2015

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው? ‹ሰማዕታተ ዘ ሊቢያ› ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት



በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብ ነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑን በወጉ መግለጥ ነው፡፡


ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችን ግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነት ኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮ ፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡ የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?

Sunday, April 19, 2015

ጭንብል ለባሽ

ራሱን የሶርያና ኢራቅ እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው (ISIS) በዓለም ላይ ከሱኒ እስልምና ውጭ ያሉትን፤ እንዲኹም ደግሞ የሱኒ ሙስሊም ተከታይ ቢሆን እንኳን ዘግናኝና አስጸያፊውን ድርጊቱን የሚቃወሙትን የሱኒ ሙስሊም ተከታዮችን፤ አጠቃላይ ሃይማኖት ባለውም በሌለውም በማንኛውም የሠው ልጅ ፍጥረት ላይ ደም የሚጠጣበት ካራውን ካነሳ ቆይቷል።

ይኼ ጭንብል ለባሽ፦ ደም መጣቹ፣ ጽንፈኛና አክራሪ እስላማዊ ቡድን (ISIS) በምዕረት የለሹ ሠይፉ፥ ለክርስትና ያለውን ጥላቻ ከቃላት በላይ ነው! ለክርስትናም ብቻ አይደለም ለሌሎችም ጭምር እንጂ! ጭንብል ለባሹ፦ ደም መጣቹ፥ የክርስትና ሃይማኖት ተቋሟትንና የእምነቱን ተከታዮችን አንገት እየቀላ፣ ደም እየጠጣ፤ ክቡር ሠውን በአሰቃቂ ግድያ እየገደሉ፤ ጭንብል አጥልቀው፥ "አላህ ወክበር" የሚሉት የተለመደ ነገር ነው።

ነገር ግን ልበ አምላክ እንዲህ ይላል፦ «ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፣ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፤ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም። ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።» (መዝ ፲፬፥፮-)


ጭንብል ለባሽ፦

ማንነቱን ደብቆ፤
ጭንብል አጥልቆ፤
ሠይፍ ጎመድ ታጥቆ፤
የሠው አንገት አንቆ።

ጭንብሉ ቢገለጥ እኒያ የተከበሩ፤
እነማን እንደኾነ ይለዩ ነበሩ።

ጭንብል ትመቻለች፤
ማንነትን ትሸፍናለች፤
"አላህ ወክበር" ታሰኛለች፤
የሠው አንገት ታስቀላለች።

----------------------------------------------------------------------------
መሪር ዕንባችንና ኃዘናችን ከባድ ነው!

«ድንግል ሆይ፦ ከዓይኖችሽ የፈሰሰውን፥ በተወደደው ልጅሽ ፊት የወረደውን፣ መሪር የሆነ እንባሽን፣ ኃዘንሽን፤ አሳስቢ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ።» (ኤር ፴፩፥፲፭፤ ማቴ ፪፥፲፯-፲፰፤ /አባ ሕርያቆስ)

፲፩//፳፻፯ /
-----------------------------------------------------------------------------