Showing posts with label ነገረ ክርስቶስ. Show all posts
Showing posts with label ነገረ ክርስቶስ. Show all posts

Saturday, April 30, 2016

የመስቀሉ ምስጢር፦

(እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!)

ድንቅ ሥነ ስዕል
ክርስቶስ ክርስትና ፋና ፈንጣቂ፤
ሃይማኖቴ ተዋሕዶ ነሽ እጅግ ድመቂ።

የሠማዕታት ተጋድሎ የጻድቃን ክብር፤
አንድም በምሳሌ አንድም በምስጢር፤
በፍቅር ሁነን በአንድነት እንድንመሰክር፤
ይሄ ነው ታላቁ የመስቀሉ ምስጢር።

ኃያሉ አምላክ ድንቅ መካር አማኑኤል የእኛ ጌታ፤
ድንግል ተወልዶ ዓለሙን ሁሉ በፍቅሩ የረታ።

ክርስቶስን የምንወድ ትዕዛዙን እንጠብቅ፤
ስለ ጻድቃን ስለ ሠማዕታት እንድንጠነቀቅ፤
ይልቅ ተጋድሏቸውን በአርምሞ እንድናደንቅ፤
ተናግሯል የእኛ ጌታ መስክረን እንድንመረቅ።

የዓለሙ በግ የመስቀሉ ምስጢር፤
ተቤዥቶ ወደደን ሰጠን ፍፁም ፍቅር፤

ድንግል ያን ጊዜ ያን ጊዜ ከአጠገቡ፤
ዐይኖቿ አረፈ ወደ ልጇ ጣምራ እያነቡ፤
ልቧ ተከፈለ በአምስቱ ኅዘናት ተመታ፤
ልጇ ወልደ አምላክ በስቃይ ሲንገላታ።

እንዴት ቻለቺው ያን የአንጀት መንሰፍሰፍ፤
የተንቢቱን ፍፃሜ የኅዘኗ ታላቅ ሠይፍ።

ጻድቅ ዮሴፍ ዕንባውን ረጨ ወደ አዶናይ፤
እጅግ ተደነቀ መልአከ ዑራኤል ከሠማይ፤
ወልድ ዋሕድ የፍቅሩ ጥጉ እንዲታይ፤
አፉን አልከፈተም በሸላቾቹ ስቃይ።

የመስቀሉ ምስጢር እንደተጻፈ ተፈፀመ፤
ተፈጥሮ ተናገረ ዓለም በፍቅሩ ተደመመ።

ስለ ሠውነቱ የሦስት ቀን ቀጠሮ፤
በአዲስ መቃብር አካሉ ተቀብሮ፤
ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን መዝብሮ፤
ሠላምን አውጀ ሰይጣንን አስሮ፤

በእባብ ገላ የገባው ዲያብሎስ ተሽሮ፤
ትንሣኤን አሳየን የሞት ሞትን ሽሮ፤
ለአዳም ልጆች ሠላምን ተናግሮ፤
እውነት ትመስክር ትናገር ተፈጥሮ።



(ማስታወሻነቱ፦ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያገለገሉና ለቤተክርስቲያን ብዙ መምህራንን ያፈሩ፣ በጣሊያን ሀገር በፊሬንዜ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ፅዋ ማሕበርን በማጠናከር ብዙ ለደከሙ ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዲያቆን አምሳሉ ተፈራ  ይሁንልኝ። /ኃይለ ኢየሱስ፤ ፳፪/፰/፳፻፰ ዓ/ም)

Saturday, April 11, 2015

ትንሣኤ ዘክርስቶስ /የክርስቶስ ትንሳኤ/ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

፩፥፩፤ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፦                  ፩፥፯፤ በኲረ ትንሣኤ፦
፩፥፪፤ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?     ፩፥፰፤ ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
፩፥፫፤ እንዴት ተነሣ?                                                   ፩፥፱፤ ለምን አትንኪኝ አላት?
፩፥፬፤ ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?                                ፩፥፲፤ ተስፋ ትንሣኤ፦
፩፥፭፤ እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?                                  ፩፥፲፩፤ ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
፩፥፮፤ መቃብሩን ማን ከፈተው?                                       ፩፥፲፪፤ የትንሣኤ ጸጋ፦

ጌታችን  አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየበመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውምበእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

፩፥፩፦ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤» የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ ሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነውእርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል) እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆሴ ÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።