Friday, January 23, 2015

"በርታ ሠውም ሁን"፦ (፩ኛ መጽ ነገ ፪፥፫) አስራ ኹለቱ ምክረ ዘ መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ


በርቱ፥ ሠውም ሁኑ! ሠው ለመኾን የሚከተሉትን መንገዶች እንኺድ

፩፤ አምልኮታችንን፦ እናክብር።

፪፤ እግዚአብሔር ቃል፦ ምግባችንን እናድርግ።

፫፤ የአሕዛብን መንፈስ፦ ከኅሊናችን ውስጥ እናውጣ።

፬፤ የሎጂክ ኑሮዎቻችንና የሎጂክ የእውቀት ጠባዮቻችንን፦ እግዚአብሔር አምላክ መንገድ ላይ እንጣለው።

፭፤ የአባቶቻችንን መንፈሳዊ ታሪክ፦ እንደገና ለመገመትና ለማንሳት እንሞክር።

፮፤ የቤተ-እግዚአብሔር መንፈስን፦ በፍቅርና በጸጋ የምንመላለስበትን ጉልበት እንድናገኝ፥ እንበርታ፤ እንጸልይ።

፯፤ በንስሐና በቅዱስ ቁርባን፦ የተባረከ ትውልድ፣ ጊዜ፣ ዘመን እንዲኖረን፤ ዕቅድ (ፕሮግራም) እናውጣ።

፰፤ የዘወትር ዕቅዶቻችን፦ እግዚአብሔር መንፈስ የተመራ እንዲኾን፥ በጸሎት እግዚአብሔር መንገዳችንን አደራ እንስጥ።

፱፤ የዕውቀታችንን ግማሽ፦ እግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንዲኾን ለማድረ፥ እንደገና አዕምሮዎቻችን ወደ አምላክ እንመልስ፤ የነፍስ ትምህርት እንዲኖረን፥ እንዘጋጅ።

፲፤ የዚህን ዓለም ሃብት፦ እንደ ዕለት እንጀራ እንጂ እንደ ዘላለማዊነት አስበን፣ በክፉ ምትአታዊ አኗኗርና ዲያብሎሳዊ ስሜትና ሐሳብ ውስጥ ገብተን የሟርት ኑሮን አንያዝ።

፲፩፤ እግዚአብሔር ክብርና ጸጋ የተሞላ ኑሮ እንዲኖረን፦ ዕለት ዕለት ሠማያዊ ምስክነት ይኑረን።

፲፪፤ መንፈስ ቅዱስ መግለጫ እንድንኾን፦ ዘወትር በአካኼዳችን፥ እግዚአብሔር ግርማ ሞገስ የተላበስን፣ በእምነቱና በቅዱስ ቁርባን ፊታችን የተባረከና የተሻሸ፣ ሠማያዊ ወዝ ያላቸው ልጆች እንዲፈጠሩና እንዲወለዱ፤ እግዚአብሔር አምላክን፥ እንማጸን።


እነዚህ ሂደቶች በሕይወታችን ውስጥ ካሉ፦ ሠው የመኾን ብርታትና እድላችን ሠፊ ነው።

 -----------------------------------------------------------------------------------------------
(ምንጭ፦ ሬዲዮ አቢሲኒያ፥  መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ መንፈሳዊ ትምህርት፤ ክፍል ፳፫)
 ----------------------------------------------------------------------------


Monday, January 19, 2015

እኛ የምንጠመቀው ጥምቀት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

እኛ የምንጠመቀው ጥምቀት በኹለት ታላላቅ ክፍል ይከፈላል፦

፩ኛ፦ ጥምቀተ ኦሪት (ጥምቀተ ንስሐ)
፪ኛ፦ ጥምቀተ ወንጌል (ጥምቀተ ክርስቶስ)

፩ኛ፥ ጥምቀተ ንስሐ

የኦሪት ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር፤ አንድ ሠው የኦሪትን ሕግ ተላልፎ ኃጢአት የሰራ  እንደኾነ ሲመለስ በውኃ ይጠመቅ ነበር። (ዘሌ ፲፭፥፰)። አንድ አሕዛብ በኦሪት ወደ አይሁዳዊነት ሲገባ ይህን የንስሐ ጥምቀት ይጠመቅ ነበር፤ (ማቴ ፫፥፲፩)። እሥራኤል ባሕረ ኤርትራን መሻገራቸው ጥምቀታቸው ነበር። (፩ኛ ቆሮ ፲፥፪)።

መጥምቁ ዮሐንስ ሲያጠምቀው የነበረው ጥምቀት የኦሪቱ የንስሐ ጥምቀት ነበር (ማቴ ፫፥፲፩)። የጌታም ደቀ መዝሙርት ይህን የንስሐ ጥምቀት አልፈው አልፈው አጥምቀዋል፤ በዚህ ጥምቀተ ንስሐ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ቄደር ገብቷል። አሁንም ይሠራበታል በማለት ይቻላል፤ አላማው ያው ጥምቀተ ንስሐ ነው። አዲሶች አማንያን ለዐቅመ አዳምና ሔዋን ከደረሱ በኋላ ንስሐ ገብተው፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ለመጠመቅ ሲፈልጉ፣  በመጀመርያ  የሚጠመቁት ይህን ጥምቀተ ቄደር (የንስሐ ጥምቀት) ነው። ያለፈው ኃጢአታቸው በዚህ ጥምቀተ ቄደር እንዲነፃ ነው። ሕፃናት ግን ኃጢአት ስለሌለባቸው የንስሐ ጥምቀት ሳይጠመቁ፣ የልጅነት ጥምቀት ብቻ ይጠመቃሉ። ከአመኑ፥ ከተጠመቁ በኋላ ብዙ ኃጢአት ሲሠሩ የኖሩ፣ ክርስቶስን ክደው በአረማዊነት፣ በእሥልምና፣ በአምልኮ ጣዖት የቆዩ  ሠዎች እንደገና አምነው በንስሐ ሲመለሱ ጥምቀተ ቄደር ይጠመቃሉ፤ ይህም ጥምቀተ ቄደር ይደገማል።

ኃጢአተኞች ይህን ጥምቀት የሚጠመቁት ፣ ለቀሳውስት ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ነው። ይህም ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ሲያጠምቅ ሕዝቡ ከእሱ የሚጠመቁት፥ በመጀመርያ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙለትና እየተናገሩት ስለነበር ነው። (ማቴ ፫፥፩-፯፣ ፫፥፲፩) ሐዋርያትም ሲያጠምቁ፥ የሚያጠምቋቸውን ሠዎች እንዲያምኑ፣ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ንስሐ እንዲገቡ ይጠይቋቸው ነበር። (ዮሐ ፩፥፳፰፤ ሐዋ ፳፮፥፳)።

፪ኛ፥ ጥምቀተ ክርስቶስ

ጥምቀተ ክርስቶስ ወይም የልጅነት ጥምቀት የሚባለው፦ ክርስቶስ ለሊቆዲሞስ ያስተማረው፣ ሐዋርያት እንዲጠመቁ ያዘዛቸው፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። (ማቴ ፫፥፲፩፤ ዮሐ ፫፥፩-፲፪)።

ይህ የክርስቶስ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን ያሰጣል (ያስገኛል)፣ መንግሥተ ሠማያትን ያስገባል፣ ኃጢአት ያስተሰርያል፤ (ሐዋ ፪፥፴፰)። ይህ የልጅነት ኹለተኛ ልደት ተብሎ  ተተርጉሟል፤ (ዮሐ ፫፥፭-፯፤ ቲቶ ፫፥፭)። ይህ የክርስቶስ ጥምቀት እንደ ጥምቀተ ቄደር አይደለም፤ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚፈጸመው። ምክንያቱም፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <<ጥምቀት አንዲት ናት>> ስለ አለና መቅዶንዮስን በቁስጥንጥንያ ጉባኤ ያወገዙት ፩፻፶ ሊቃውንትም <<ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት /በአንዲት ጥምቀት እናምናለን>> ብለው ስለወሰኑ ነው። (ኤፌ ፬፥፭-፮) ዮሐንስ አፍወርቅም በ፲፫ኛው ተግሣጹ ጥምቀት አንዲት ናት እንጂ ኹለተኛ ጥምቀት የለም ብሎ የጻፈው ስለ ልጅነት ጥምቀት አለመደገም ሲያስረዳ ነው።
 ----------------------------------------------------------------------
 ምንጭ፦ በየጥቂቱ (ጥቂት በጥቂ) አደገ በ፴ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ገፅ ፴፩-፴፪፤ አዲስ አበባ ጥር ፲ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ከታተመ መጽሐፍ
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ፦ "በዓለ ጥምቀት፤ ምሳሌውና ምስጢሩ" በሚል (ሰባኪ ወንጌል ዘ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው የተሰጠ መንፈሳዊ ትምህርተ ወንጌል ሰምተውና አዳምጠው ስጋዎትንና ነፍሶትን ይመግቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዘዋል።