Friday, March 13, 2015

እንደገና ወደ ግብጽ መኼድ፦ ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ



በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የተከሰቱትን የሃይማኖት ትምህርትና የሥርዓት መበላሸት በማስመልከት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ችግሩ ሥር ሳይሰድ ገና ከጅምሩ እንዲታረም ማሳሰቢያና ተማጽኖ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ ተማጽኖ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ጥያቄአቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ በቸልታ በመታየቱ ምክንያት፤ አለቃ አያሌው ታምሩ ባላቸው ከፍተኛ ሥልጣንና ኃላፊነት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ዐመጽ የሚፈጽሙትን ፓትርያርኩንና ተከታዮቻቸውን ማውገዛቸው ይታወቃል። ቃለ ግዝታቸው በመጀመሪያ የወጣው ሰኔ ፳፯ ቀን ፲፱፻፹፰ / «መብሩክ» ጋዜጣ ላይ ነበር። ሙሉውን ቃለ ውግዘት ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ

አባታችን ይህን ቃለ ውግዘት ካስተላለፉበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከምእመናንና ከተለያዩ ክፍሎች ውግዘቱን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች በቃልና በጽሑፍ፥፣ እንዲሁም በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የቀረቡላቸው ሲሆን፤ ለቀረቡት ጥያቄዎችም ተገቢ የሆኑ ምላሾችን ሰጥተዋል ሰጥተዋል። በተለያዩ ጊዜዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በ፲፱፻፺ / ብዙ ምእመናን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው በጋራ ያቀረቡላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ "በዚህ ውግዘት መካከል በእርስዎ ወይም በሳቸው መካከል የመለየት ባሕርይ ቢኖር ውግዘቱ እንደ ታሰረ ነው ወይስ እንደ ተፈታ ነው የሚቆየው? ውግዘቱን ማን ይፈታዋል? እስከ መቼ ድረስ ነው ውግዘቱ የሚቆየው?" የሚል ሲሆን፤ ክቡር አባታችን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተው ነበር።